ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በእነዚህ በሦስቱ ነገሮች ያማርሁ ሆንሁ፤ በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ያማርሁ ሆኜ ቆምሁ፥ እነዚህም በአንድ ልብ የሚተባበሩ ወንድማማቾች፥ የባልንጀሮች ፍቅር፥ የባልና ሚስትም ስምምነት ናቸው። 2 ሦስት ዐይነት ሰዎችን ሰውነቴ ፈጽማ ጠላቻቸው፤ ኑሯቸውም እጅግ አበሳጨኝ፤ እነዚህም ትዕቢተኛ ድሃ፥ ንፉግ ባለጸጋና አእምሮ የሌለው ሴሰኛ ሽማግሌ ናቸው። 3 ከሕፃንነትህ ጀምረህ ያልተመከርህ፥ በእርጅናህ ጊዜ እንዴት ብልህ ትሆናለህ? 4 ሺበት ፍርድ ሊሰጥ ይገባዋል፤ ሽማግሎችም መምከር ይገባቸዋል። 5 ለሽማግሎችም ጥበብ ይገባቸዋል፤ ለታላላቅ ሰዎችም ጥበብን መማር ይገባቸዋል። 6 የትምህርት ብዛት የሽማግሎች ዘውዳቸው ነው፤ መመኪያቸውም እግዚአብሔርን መፍራት ነው። 7 በልቤ ያደነቅኋቸው ዘጠኝ ናቸው፤ ዐሥረኛውን ግን በቃሌ እናገራለሁ፤ እነርሱም በልጆቹ ደስ የሚለው ሰው፥ በሕይወቱም ሳለ የጠላቱን ውድቀት የሚያይ ሰው ናቸው። 8 ልባም ሴትን ያገባ ብፁዕ ነው፤ በአንደበቱም ያልሳተ ሰው ብፁዕ ነው፤ ከእርሱ ላነሰ ሰው ያላደረ ብፁዕ ነው፤ 9 ዕውቀትና ጥበብን ያገኛት ሰው፥ የሚታዘዝለትንም ያገኘ ሰው ብፁዕ ነው። 10 ጥበብን ያገኘ ሰው እንዴት ታላቅ ነው! ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚፈራ ይህን ይበልጠዋል። 11 እግዚአብሔርን መፍራት ከሁሉ ትበልጣለች። 12 እርሷንም የጠበቀ ሰውን የሚመስለው የለም። 13 ከቍስል ሁሉ ይልቅ የልብ ቍስል ይከፋል፤ ከክፋትም ሁሉ የሴት ክፋት ትከፋለች። 14 በሁሉም ብትወድቅ በጠላትህ እጅ አትውደቅ፤ ሁሉ ቢበቀልህ ጠላትህ አይበቀልህ። 15 ከእባብ ራስ የሚከፋ ራስ የለም፤ ከጠላትም ቂም የሚከፋ ቂም የለም። የክፉ ሴት ተግባር 16 ከክፉ ሴት ጋራ ከምትኖር፥ ከአንበሶችና ከምድር አውሬዎች ጋር መኖር ይሻላል። 17 ክፋትዋ መልኳን ይለውጠዋል፤ ፊትዋንም እንደ ድብ መልክ ያጠቍረዋል። 18 ባሏንም በባልንጀሮቹ መካከል ይንቁታል፤ መራራ ኀዘንንም ያሳዝኑታል፤ አስጨንቀውም ይይዙታል። 19 ክፋት ሁሉ ከሴት ክፋት ታንሳለች፤ እርስዋም ወደ ኀጢአት ዕድል ታደርሳለች። 20 የአሸዋ ዐቀበት የሽማግሌዎችን እግራቸውን እንደሚያደክም፥ እንዲሁ ቀባጣሪ ሴት የዋህ ባልን ታደክመዋለች። 21 የሴት መልኳ አያስትህ፤ ሀብቷም አያስጐምጅህ። መቅሠፍትና ጥፋት ጽኑ ውርደትም ናትና፤ 22 ሴት ባሏን ብትመግበው፥ ቍጣን፥ አለማክበርንና ብዙ ዘለፋን የተሞላች ትሆናለች። 23 ለልብ ቍስል ናት፥ ለፊትም ጥቁረት ናት፥ ለነፍስም ኀዘን ናት፤ እንዲሁ ባሏን የማታከብር ሴት እንደ ሽባ እጅና ልምሾ እንደ ሆነ እግር ናት። 24 በመጀመሪያም ኀጢአት ከሴት ተገኘች፤ በእርስዋም ምክንያት ሁላችን እንሞታለን። 25 ለውኃ መፍሰሻ አታብጅለት ለሴትም የልብህን ምሥጢር አታውጣላት። 26 እንደ ጠባይህ ካልሆነች ፍታት፤ ከሰውነትህም ለያት። |