ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የጥበብ ክብር 1 ጥበብ ራስዋን ታመሰግናለች፤ በአሕዛብም መካከል ትመካለች። 2 በልዑልም ጉባኤ ትናገራለች፤ በኀይሉም ፊት ትመካለች። 3 እንዲህም አለች፦ እኔ ከልዑል አፍ ወጣሁ፤ ምድርንም እንደ ጉም ሸፈንኋት። 4 እኔ በሰማይ ኖርሁ፤ ዙፋኔንም በደመና ዐምድ ላይ ዘረጋሁ። 5 ብቻዬንም በሰማይ ዳርቻ ዞርሁ፤ በውቅያኖስ መካከልም ተመላለስሁ፤ 6 በባሕርም ማዕበል ላይ በየብስም መካከል ሁሉ፥ በሕዝቡና በአሕዛቡ ሁሉ ጥሪትን አደረግሁ። 7 ከዚህም ሁሉ በኋላ ዕረፍትን ፈለግሁ፤ እንግዲህ በማን ርስት አድራለሁ? 8 ከዚህም በኋላ ሁሉን የፈጠረ አዘዘኝ፤ ፈጣሪም ማደሪያዬን አዘጋጀልኝ፤ እንዲህም አለኝ፦ “በያዕቆብ እደሪ፤ ርስትሽም በእስራኤል ይሁን።” 9 ዓለም ሳይፈጠር ወለደኝ፥ ለዘለዓለሙም ከእርሱ አልለይም። 10 በተቀደሰ ማደሪያውም በፊቱ አገለገልሁ፤ በጽዮንም አደርሁ። 11 እንዲሁም በተወደደችው ከተማ ዐረፍሁ፤ ግዛቴም ባስገዛኝ በኢየሩሳሌም ነበር። 12 በእግዚአብሔር ርስት ዕድል ፋንታ፥ በከበረ ሕዝብ መካከል ሥር ሰደድሁ። 13 በሊባኖስ እንዳለ ዝግባ ከፍ ከፍ አልሁ፤ በኤርሞን ተራራ እንዳለ ዋንዛም ገነንሁ። 14 በውኃ ዳር እንዳለ ዘንባባም ረዘምሁ፤ በኢያሪኮ እንዳለ ጽጌረዳ፥ በምድረ በዳ እንዳለች እንዳማረች የዘይት እንጨትም መዓዛዬ የተወደደ ሆነ፤ እንደ ዋርካ ዛፍም ገነንሁ። 15 መዓዛዬም እንደ ቀናንሞስና እንደ ደርሶኒ ሽቱ የተወደደ ሆነ፤ መዓዛዬም እንዳማረ የሽቱ መዓዛ ሆነ፤ እንደ ልባንጃና እንደ ጥርኝ፥ ሰጡቃጤ እንደሚባል ሽቱም፥ በደብተራ ኦሪት እንዳለ እንደ ነጭ ዕጣን መዓዛም የተወደደ ሆነ። 16 ቅርንጫፎች እንደ ቡጥም ረዘሙ፤ ቅርንጫፎችም የክብርና የጌትነት ቅርንጫፎች ናቸው። 17 እኔስ እንደ ተወደደ የወይን ሐረግ መወደድን አስገኘሁ። 18 አበባዬም የክብርና የባለጸግነት ፍሬ ነው። 19 የምትወዱኝ ሰዎች ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ ከፍሬዬም ትጠግባላችሁ። 20 ስም አጠራሬ ከማር፥ ርስትነቴም ከሸንኮር ይልቅ ይጣፍጣልና። 21 የሚመገቡኝም አይጠግቡኝም፤ የሚጠጡኝም አይሰለቹኝም። 22 የሚሰማኝም አያፍርም፤ ለእኔ የሚገዙ ሰዎች አይስቱም። 23 ይህ ሁሉ ነገር የልዑል የሕጉ መጽሐፍ ነው፤ ስለ ያዕቆብም ወገኖች ርስት ሙሴ ያዘዘበት ሕግ ነው። 24 በእግዚአብሔር የሚጸና አይደክምም፤ እርሱ ያጸናችሁ ዘንድ ተከተሉት፤ ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ አዳኝ የለም። 25 ጥበብን እንደ ኤፌሶን ፈሳሽ፥ በሚያዝያም ወራት እንደሚመላ እንደ ጤግሮስ ፈሳሽ የሚመላት እርሱ ነው። 26 ምክርንም እንደ ኤፍራጥስ ፈሳሽ፥ ባዝመራም ወራት እንደ ዮርዳኖስ ፈሳሽ የሚመላት እርሱ ነው። 27 ጥበብን እንደ ብርሃን፥ በወይን አዝመራ ወራትም እንደ አባይ ፈሳሽ የሚገልጣት እርሱ ነው። 28 የመጀመሪያው አላወቃትም፤ የመጨረሻውም ፍለጋዋን አላገኘም። 29 ምሥጢሯ ከባሕር ውኃ ይልቅ ይበዛል፤ ምክሯም ከባሕሩ ጥልቀት ይልቅ ይጠልቃል። 30 ከወንዝ እንደሚፈስስ ውኃ ሆንሁ፤ እንደ መስኖ ውኃም ወደ ተክል ቦታ ገባሁ፤ 31 እንዲህም አልሁ፥ “የተክል ቦታዬን ላጠጣት፤ የጎመን ቦታዬን ላጠጣት፤” ፈፋዬ እንደ ወንዝ ሆነልኝ፤ ወንዜም እንደ ባሕር ሆነልኝ። 32 ዳግመኛም ጥበብን እንደ ጥዋት አበራታለሁ፤ እስከ ሩቅም ድረስ ብርሃንዋን አሳያለሁ። 33 ትምህርትን እንደ ትንቢት አፈስሳታለሁ፤ ለዘለዓለምም ለልጅ ልጅ አጸናታለሁ። 34 እነሆ፥ የደከምሁ ለሚፈልጉኝ ሰዎች ሁሉ ነው እንጂ፥ ለእኔ ብቻ እንዳይደለ እዩ። |