ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከኀጢአት ስለ መራቅ ጸሎት 1 አቤቱ፥ አባቴ፥ የሕይወቴም ፈጣሪ፥ በእነርሱ ምክር አትጣለኝ፥ በእነርሱም እንዳልጠፋ አትለየኝ፤ 2 ልቡናዬን ማን በመከረልኝ? ድንቍርናዬም ይተወኝ ዘንድ፥ በተናገሩብኝም ነገር ድል እንዳይነሱኝ፥ ለልቡናዬ ጥበብን ማን ባስተማራት? 3 በደሌ እንዳይበዛብኝ፥ ኀጢአቴም እንዳይበረክትብኝ፥ በጠላቶችም ፊት እንዳልወድቅ፥ ጠላቶችም በእኔ ጥፋት ደስ እንዳይላቸው፥ 4 ጌታዬ፥ አባቴ፥ የሕይወቴ ፈጣሪ ሆይ፥ ዐይኔን የሚያስታትን ነገር አታምጣብኝ። 5 መጐምጀትንም ከእኔ አርቅልኝ። 6 ጥጋብ አይምጣብኝ፤ ቍንጣንም አያቀናጣኝ፤ ለክፉ ሰውም አሳልፈህ አትስጠኝ። አንደበትን ስለ መግራት 7 ልጆች ሆይ፥ የአንደበቴን ምክር ስሙኝ፤ ቃሌን የጠበቀ አይሰነካከልም፤ አንደበቱንም የጠበቀ አይወድቅም። 8 ኀጢአተኛ በስንፍናው ይያዛል፤ ተሳዳቢና ትዕቢተኛም በዚሁ ይሰነካከላሉ። 9 ልጄ ሆይ፥ ለአፍህ መሐላን አታስለምደው፤ በማልህም ጊዜ የቅዱሱን ስም በሐሰት አትጥራ። 10 ሁልጊዜ እየተመረመረ የሚገረፍ ባሪያ ቍስሉ እንደማይደርቅ፥ እንደዚሁ ሲምል ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ስም በሐሰት የሚጠራ ሰው ከኀጢአት አይነጻም። 11 መሐላን የሚያበዛ ሰው ኀጢአቱ ብዙ ነው፥ ከቤቱም መቅሠፍት አይርቅም፤ ቢያረጅም ኀጢአቱ አይተወውም፤ ቸል ቢልም ኀጢአቱ እጥፍ ይሆንበታል፤ ፍዳው በቤቱ ሞልትዋልና ስለ ማለ እውነተኛ አይባልም። 12 ሞትን የምታመጣው ቃል አለች፤ በያዕቆብም ርስት አትኖርም፤ ይህ ሁሉ በጻድቃን ዘንድ የለም፤ በኀጢአትም አይሰነካከሉም። 13 በውስጡ ብዙ ኀጢአት አለና፥ ከአንደበትህ የመዘባበት ነገር አይውጣ። 14 አባትህንና እናትህን ዐስባቸው፥ መኳንንቶችህንም አገልግል፤ በፊታቸውም አትሳት፤ ባልተወለድሁ እንዳትል፥ የተወለድህበትንም ቀን እንዳትረግም በስንፍናህ እንዳትጠላ ሁን። 15 በሰው ላይ መሳለቅን የለመደ ሰው፥ መላ ሕይወቱን ብልህ አይሆንም። ስለ ዝሙት ኀጢአት 16 ኀጢአትን የሚያመጧት ሁለት ናቸው፤ ሦስተኛው ግን ሞትን ያመጣል፤ ቍጡ ሰውነት እንደሚቃጠል እሳት ናት፤ እስክታሰጥመውም ድረስ አትበርድም፤ በሰውነቱም የሚሰስን ሰው እሳትን እስኪያቀጣጥላት ድረስ አይተውም። 17 ለሴሰኛ ሰው እህሉ ሁሉ ይጣፍጠዋል፤ እስኪሞትም ድረስ አያርፍም። 18 ሚስቱን ትቶ የሚሄድ ሰው፥ በልቡ “ጊዜው ጨለማ ነው፤ የሚያየኝ የለም፤ አጥር ይጋርደኛል፤ ከዚህ በኋላ ምን እፈራለሁ? የሚያውቀኝም የለም፤ ልዑልም ኀጢአቴን ይዘነጋልኛል፤ አያስብብኝምም” ይላል። 19 ነገር ግን እንዳያየው የሰው ዐይንን ይፈራል፤ የእግዚአብሔርም ዐይን ከፀሐይ መቶ ሺህ ጊዜ እንዲበራ፥ የሰውንም ሥራ ሁሉ እንደሚያይ፥ ተሰውሮ የሚሠራንም ሥራ ሁሉ እንደሚያውቅ አያውቅም። 20 ሁሉም ከመፈጠሩ በፊት በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው፤ ከጨረሰም በኋላ እንዲህ ያደርገዋል። 21 በከተማም መካከል ይበቀለዋል፤ ባልጠረጠረበትም ቦታ ያጠፋዋል። 22 ባሏን ትታ የምትሄድ ሴት እንዲሁ ናት፤ ከሌላ ወንድ ልጅን ትወልዳለች። 23 በእግዚአብሔር አንዲት ክህደት አደረገች፤ ሁለተኛም ባሏን ከዳችው፥ ሦስተኛም በሴሰኝነትዋ ሰረቀች፤ ከሌላ ወንድም ልጅን ወለደች። 24 እንዲህ ያለችው ሴት ቷረዳለች፤ በልጆችዋም ትገረፋለች። 25 ዘሮችዋ ይጠፋሉ፤ ቅርንጫፎችዋም አያፈሩም። 26 ስም አጠራሯም የተረገመ ይሆናል፤ ለቤቷም መርገምን ታወርሳለች፤ መርገምዋና ውርደቷ ለዘለዓለሙ አይጠፋም። 27 ያያት ሁሉ እግዚአብሔርን ከመፍራት የሚበልጥ፥ የእግዚአብሔርንም ሕግ ከመጠበቅ የሚጣፍጥ እንደሌለ ያውቃል። |