ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰነፍና ስንፍና 1 ሰነፍ ሰው በተቀመጠበት ቦታ እንደ ዋሻ ድንጋይ ነው፤ በጽኑ ስንፍናው ሁሉን ያቦዝናል። 2 ሰነፍ ሰው በተኛበት ቦታ እንደ ተጣለ ፈርስ ነው። የነካውም ሰው ሁሉ እጁን ያራግፋል። 3 ያልተቀጣ ልጅ ለአባቱ ኀፍረት ነው፤ ያልተቀጣች ሴት ልጅም የጐሰቈለች ትሆናለች። 4 ብልህ ሴት ልጅ ባልዋን ትወርሳለች፤ የምታሳፍር ሴት ልጅ ግን ለአባቷ ኀዘን ናት። 5 አባትዋንም ታሳፍራለች፤ ባሏንም ታሳፍራለች፤ ደፋርም ናት፤ በሁለቱም ዘንድ እጥፍ ቷረዳለች። ጥበብና ሞኝነት 6 ባገኘበት ቦታ ነገሩን የሚናገር ሰው፥ በልቅሶ ቤት መሰንቆ እንደሚመታ ሰው ነው፤ ግርፋትና ተግሣጽ ሁልጊዜ ብልህ ያደርጋል። 7 ሰነፍ ሰውን የሚያስተምር ሰው፥ የተሰበረ ገልን እንደሚጠግን ሰው ነው፤ የተኛ ሰውንም ከጽኑ እንቅልፍ እንደ መቀስቀስ ነው። 8 ለሰነፍ ሰው የሚነግር በጽኑዕ እንቅልፍ ለተያዘ ሰው እንደሚነግር ነው፤ ነግረኸው ከጨረስህ በኋላ “ምን ተናገርኽ?” ይልሃል። 9 ብርሃኑ አልፏልና ለሞተ ሰው አልቅስለት፤ አእምሮውም ጠፍትዋልና ለሰነፍ ሰው አልቅስለት። 10 ከሞተ በኋላ አይመለስምና፥ ለሞተ ሰው ታለቅስለት ዘንድ አገባብ ነው። ከመሞቱ መኖሩ ይከፋበታልና ለሰነፍ ሰው በሕይወት ሳለ አልቅስለት። 11 ሰዎች ስለ ሞተ ሰው ሰባት ቀን ያለቅሱለታል፤ ለሰነፍና ለኀጢአተኛ ግን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አልቅስለት። 12 ከሰነፍ ሰው ጋራ ነገርን አታብዛ፤ አእምሮ ከሌለውም ሰው ጋራ አትሂድ፤ ወደ መከራ እንዳያገባህ፥ አንተም በእርሱ ስንፍና እንዳትነቀፍ ተጠበቅ። 13 ከእርሱ ራቅ፤ ሰውነትህም ታርፋለች፤ ይቀልሃልም፤ በእርሱም ስንፍና አንተ የምትጐዳው የለም። 14 ከአረር የሚከብድ ምን አለ? ሰነፍ ከመባልስ የሚከፋ ምን አለ? 15 ከሰነፍ ሰው ጋራ ከመኖር፥ ጨውና አሸዋ፥ ብረትንም ብትሸከም ይሻላል። 16 ማገሩ ያማረ፥ በግንብ የታሰረ ቤት በምድር መናወጥ ጊዜ እንደማይፈርስ፥ የብልህ ሰው ምክርም በጽኑዕ ልቡና እንዲሁ ነው። 17 ቅጥሩም ለዘለዓለም አይወድቅም፤ በዐዋቂ ሰው ምክር የጸና ልቡናም በግድግዳ ላይ እንዳለ የአሸዋ ምርግ ነው። 18 በነፋስ ፊት ያለ ገለባም ነፋስ በነፈሰ ጊዜ እንደማይቆም፥ ያላዋቂ ሰው ዐሳብም ያስፈራው ሰው ቢኖር በማይቆም በፈሪ ሰው ልቡና ዘንድ እንዲሁ ነው። ወዳጅነትን ጠብቆ ማቈየት 19 ዐይኑን የሚጠነቍል ሰው እንባውን ያወርዳል፤ ልቡናውንም የሚነካ ሰው ጥበብን ያሳያል። 20 በወፎች ድንጋይ የወረወረባቸው ሰው ያባርራቸዋል፤ በወዳጁም የሚዘብት ሰው ወዳጅነትን ያጠፋል። 21 በወዳጅህ ላይ ሰይፍን ብትመዝ፥ ተመልሶ ወዳጅህ ይሆን ይሆናልና ተስፋ አትቍረጥ። 22 ነገር ግን ብትላገድበት፥ አፍህንም በእርሱ ላይ ከፍና ዝቅ አድርገህ ብትናገር፥ ብትሰድበውም፥ ምክሩንም ብታወጣበት፥ ብትከዳውና፥ ብታሳዝነው በዚህ ነገር ወዳጅ ሁሉ ይሸሻል። 23 አንተም ድሃ ብትሆን በደስታው ጊዜ ከእርሱ ጋር ደስ ይልህ ዘንድ፥ ከባልንጀራህ ጋር ታማኝነትህን ጠብቅ። ቢቸገርም ርስቱን ባገኘ ጊዜ ከእርሱ ጋር ደስ ይልህ ዘንድ ከእርሱ ጋር ታገሥ። 24 የእሳትም የጭሱ ትነት ይቀድማል፤ እንደዚሁም ደም ከማፍሰስ ጠብና ክርክር ይቀድማል። 25 ወዳጄን መሰወር አላፍርም፤ ከፊቱም አልሰወርም። 26 ነገር ግን በእርሱ ምክንያት ክፋት ብታገኘኝ፥ የሰማ ሁሉ ከእርሱ ራሱን ይጠብቅ። 27 ለአንደበቴ ጠባቂ ማን ባኖረልኝ? በእነርሱ እንዳልወድቅ፥ አንደበቴም እንዳትገድለኝ፥ በከንፈሮች የጥበብን ቍልፍ ማን ባኖረልኝ! |