ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ልጄ ሆይ፥ የበደልኸው በደል የሳትኸውም ነገር ቢኖር፥ እንዳትደግም ተጠንቀቅ፥ ስለ ቀደመው ኀጢአትህም ንስሓ ግባ። 2 ከክፉ አውሬ እንደሚሸሽ እንዲሁ ከኀጢአት ሽሽ፥ ከአገኘችህ ግን አትለቅህም፤ ጥርሷ እንደ አንበሳ ጥርስ ነው፤ የሰውንም ነፍስ ታጠፋለች። 3 ሁለት አፍ እንዳለው የተሳለ ሰይፍ ኀጢአት ሁሉ እንዲሁ ናት፤ ካቈሰለችም ለቍስሏ ፈውስ የለውም። 4 መመካትና መኵራት፥ ትዕቢትም ባለጸግነትን ያጠፏታል፤ እንደዚሁም የትዕቢተኞችን ቤት ያጠፋሉ። 5 ድሃ በሚለምንበት ጊዜ አፉን እስከ ዦሮው ይከፍታል፤ ጩኸቱም ፈጥኖ ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል። 6 ምክርን የሚጠላ ሰው ኀጢአተኞችን ይከተላቸዋል፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን በመከሩት ጊዜ ልቡናውን ይመልሳል። 7 ንግግርን የሚችል ሰው ከሩቁ ይታወቃል፤ ለብልህ ሰውም የተሳተው ኀጢአቱ ይታወቀዋል። 8 በብድር ገንዘብ ቤቱን የሚሠራ ሰው፥ ሕንጻው እንደ ክረምት ግንብ ነው። 9 የኀጢአተኞችም አንድነታቸው እንደ ገለባ ክምር ነው፤ ፍጻሜያቸውም ለእሳት ነበልባል ይሆናል። 10 የኀጢአተኞች መንገድ ጐፃጕፅ ነው፤ መውጫዋም ገደል ነው። 11 ልቡናውን ያጸና ሰው የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቃል። እግዚአብሔርን የመፍራትም መጨረሻዋ ጥበብ ነው። 12 ያልተማረ ሰው ጠቢብ አይሆንም፤ ተምሮም ውርደት የሚበዛበት አለ። 13 የብልህ ሰው ዐሳቡ እንደ ክረምት ውኃ ብዙ ነው፤ ምክሩም እንደ ሕይወት ውኃ ይመነጫል፤ 14 ያላዋቂ ሰው ልብ እንደ ሰባራ ማድጋ ነው፤ የሰማውን ነገር ሁሉ መጠበቅ አይችልምና። 15 አስተዋይ ሰው የጥበብን ነገር በሰማ ጊዜ ያደንቃታል፤ ዳግመኛም በእርስዋ ላይ ይጨምራል፤ አላዋቂ ልቡና ግን ከሰማ በኋላ ይተፋል፤ ወደ ኋላም ይመልሰዋል። 16 የአላዋቂ ሰው ነገሩ በራቀ ጎዳና እንዳለ እንደሚከብድ ሸክም ነው፤ የብልህ ሰው አንደበት መወደድ ግን መልካም ነው። 17 የብልህ ሰው ነገሩ በጉባኤ ይሰማል፤ ነገሩም ወደ ልብ ይገባል። 18 ጥበብ በአላዋቂዎች ሰዎች ዘንድ እንደ ፈረሰች ቤት ናት። ያላዋቂ ሰው ምክርም የማይወደድ ነገር ነው። 19 ያላዋቂዎች ትምህርት እንደ ታሰረ እግር ነው። ያላዋቂዎችም ልቡና ቀኝ እጁን እንደ ታሰረ ሰው ደካማ ነው። 20 አላዋቂ ሰው በሳቀ ጊዜ ቃሉን ከፍ ያደርጋል፤ ብልህ ሰው ግን በጭንቅ ከንፈሩን ፈገግ ያደርጋል። 21 ጥበብ በአስተዋይ ሰው ዘንድ እንደ ወርቅ ጌጥ ናት፥ በቀኝ እጅ እንዳለ አምባርም ናት። 22 ያላዋቂ ሰው እግር ፈጥና ወደ ቤት ትገባለች፤ በትምህርት የተፈተነ ሰው ግን የሰውን ፊት ያፍራል። 23 አላዋቂ ሰው በደጃፍ ሆኖ የሰው ቤትን ይመለከታል፤ ዐዋቂ ሰው ግን በውጭ ይቆማል። 24 ለሰው በበር ተጠግቶ ማድመጥ አላዋቂነት ነው፤ በዐዋቂ ሰው ዘንድ ግን ይህን ነገር ማድረግ እጅግ አሳፋሪ ነው። 25 የለፍላፊ ከንፈር የማይመለከተውን ይናገራል፤ የጠቢባን ቃል ግን በሚዛን የተመዘነች ናት። 26 ያላዋቆች ልባቸው ባፋቸው ነው፤ የኣዋቂዎች አፍ ግን በልባቸው ነው። 27 ኀጢአተኛ ሰው ሰይጣንን ቢረግመው ራሱን መርገሙ ነው። 28 ሐሜተኛ ሰው ሰውነቱን ያረክሳል፤ ባደረበትም ቦታ ራሱን ያስጠላል። |