ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ለበጎ ነገር ሳይሆን የሚገሥጽ ሰው አለ፤ ዐዋቂ ሆኖ ሳለም ዝም የሚል ሰው አለ። 2 ነገር ግን ከመንቀፍ መገሠጽ ይሻላል። 3 ስሕተቱን የሚያምን ከጥፋት ይድናል። 4 ፍርድን ያደላ ዘንድ የሚወድ ሰው፥ ቆንጆ ልጅን እንደሚመኝ ጃንደረባ ነው። 5 እያወቀ ዝም የሚል ሰው አለ፥ ንግግር በማብዛትም ራሱን የሚያስጠላ ሰው አለ። 6 የሚመልሰውን አያውቅምና ዝም የሚል ሰው አለ፤ ጊዜውንም እስኪያገኝ ድረስ ዝም የሚል ሰው አለ። 7 ብልህ ሰውም ጊዜውን እስኪያገኝ ድረስ ዝም ይላል፤ አላዋቂና ደፋር ሰው ግን እንዳገኘ ይናገራል። 8 ነገርን የሚያበዛ ሰውን ይቈጡታል፤ ራሱንም የሚያኰራ ሰውን ይጠሉታል። 9 ችግሩ የሚያዋርደው ሰው አለ፤ ገንዘብም አግኝቶ የማይበረክትለት ሰው አለ። 10 የማይጠቅምህን የሚሰጥህ ሰው አለ፤ ሰጥቶም እጥፍ አድርጎ የሚቀበልህ ሰው አለ። 11 እየተቸገረ ራሱን የሚያኰራ አለ፤ ራሱን በማዋረዱም የሚከብር አለ። 12 በጥቂት ብዙ የሚገዛ አለ፤ ሰባት እጥፍ ያደርገውም ዘንድ ይፈልጋል። 13 ብልህ ሰው በቃሉ ራሱን ያስወድዳል፤ የአላዋቂዎች ስጦታም ተወዳጅነት የላትም። 14 አላዋቂ ሰው ጥቅምና ተወዳጅነት የሌለውን ገንዘብ ይሰጥሃል፤ ጥቂት ቢሰጥህም ለልቡ ብዙ የሰጠህ ይመስለዋል። 15 ጥቂት ቢሰጥህ ብዙ እንደ ሰጠህ ይላገድብሃል፤ በአንተም ላይ ነገሩን ያበዛል፤ የሰጠህንም ይናገርብህ ዘንድ በአደባባይ ይዞራል፤ ዛሬ ቢሰጥህ ነገ ይከፈልሃል፥ እንዲህ ያለው ሰው የሚያስጠላ ነው። 16 አላዋቂ ሰው ግን “ወዳጅ አልፈልግም ምን ይጠቅመኛል? በጎ ነገር ያደረግሁለት እኔ ዋጋን አላገኝምና፤ እህሌንም የሚመገቡ ሰዎች በእኔ ክፉ ነገር ይናገራሉ። 17 ሁሉም ሁልጊዜ ያሙኛል፤ በእኔም ይስቃሉ” ይላል። የማይገባ ንግግር 18 በአንደበትህ አድጦህ ከምትወድቅ፥ በምድር ላይ አድጦህ ብትወድቅ ይሻልሃል፤ እንዲሁ የክፉ ሰው አወዳደቅ ፈጥኖ ይመጣል። 19 እንዳገኘ የሚናገር ሰው ራሱን ያስነውራል፤ ለቃሉም መወደድ የለውም፤ በአላዋቂዎች አንደበትም ነገር ይጠላል። 20 በጊዜው አይናገረውምና፥ በአላዋቂ ሰው አንደበት ምሳሌ ይጠላል። 21 በተቸገረ ጊዜ እግዚአብሔርን ወደ መፍራት የሚመለስ ሰው አለ፤ ሰውነቱም በመልካም ታርፋለች። 22 በማፈርም ሰውነቱን የሚያጠፋ አለ፤ በአላዋቂነቱም ሰውነቱን ያጠፋል። 23 በማፈር ላይሰጠው ለወዳጁ ተስፋ የሚሰጠው አለ። ስለዚህም ነገር በከንቱ ጠላት ይሆነዋል። 24 የሐሰተኛ ሰው ውርደቱ ክፉ ነው፤ የአላዋቂዎች ነገራቸው የተጠላ ነው። 25 ከሐሰተኛ ሌባ ይሻላል፤ ነገር ግን የሁለቱም ፍጻሜያቸው ሞትና ውርደት ነው። 26 ሐሰተኛ ሰው ፈጽሞ ይዋረዳል፥ ያፍራልም። 27 በቃሉ ብልህ የሆነ ሰው ነገሩ ይሰማል፤ ብልህ ሰው መኳንንቱን ደስ ያሰኛል። 28 ምድርን የሚያርሳት የእህሉን ክምር ያበዛል፤ መኳንንቱንም የሚያገለግል ራሱን ይጠቅማል። 29 እጅ መንሻና መማለጃ የጠቢባንን ዐይን ያሳውራል፤ አፋቸውን ይዘጋል፤ ቃላቸውንም ያስለውጣል። 30 የተሰወረ ጥበብ እንደ ተቀበረ ወርቅ ነው፤ እንግዲህ የሁለቱስ ጥቅማቸው ምንድን ነው? 31 ጥበቡን ከሚሰውር ብልህ ሰው፤ አለማወቁን የሚሰውር አላዋቂ ሰው ይሻላል። |