ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለ መሆን 1 ልጄ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ትገዛ ዘንድ ብትሄድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ። 2 ልብህን አቅና፥ ታገሥ፥ አታወላውልም፥ ብትጨነቅም አትጠራጠር። 3 ነገር ግን ተከተለው፥ በፍጻሜህም ሕይወትህ ትበለጽግ ዘንድ አትተወው። 4 የደረሰብህን ሁሉ ተቀበል፥ በችግርህም ወራት ታገሥ። 5 ወርቅን በእሳት ይፈትኑታልና፥ ጻድቅንም ሰው በመከራ ይፈትኑታልና። 6 ነገር ግን እግዚአብሔርን እመነው፤ እርሱም ይረዳሃል፤ መንገድህንም አቅና፥ በእርሱም እመን። 7 እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ቸርነቱን ደጅ ጥኗት፥ በመከራም እንዳትወድቁ ከእርሱ አትራቁ። 8 እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ዋጋችሁን እንዳታጡ እመኑት። 9 እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ የዘለዓለም በጎነቱን ምሕረቱንና ደስታውን ተስፋ አድርጉ። 10 በዘመን የቀደሙ ሰዎችን ተመልከቱ፤ ዕወቁም፥ በእግዚአብሔር አምኖ ያፈረ ማንነው? እርሱን በመፍራት የታገሠና የተጣለ ማንነው? ጠርቶትስ ቸል ያለው ማንነው? 11 እግዚአብሔር መሓሪ ይቅር ባይም ነውና፥ ኀጢአትን ይቅር ይላል፥ በመከራ ቀንም ያድናል። 12 ለሚጠራጠር ልቡና ወዮለት! ለጠማሞች እጆችም ወዮላቸው! ሥራው ሁለት ለሆነ፥ በሁለትም መንገድ ለሚሄድ ኀጢአተኛ ወዮለት! 13 ለሚጠራጠርና ለማያምንም ልብ ወዮለት! ስለዚህም አያመልጥም። 14 ትዕግሥታቸውን ላጡ ሰዎች ወዮላቸው! እግዚአብሔር በተመለሰባቸው ጊዜ ምን ያደርጉ ይሆን? 15 እግዚአብሔርን የሚፈሩ ቃሉን አይረሱም፥ የሚወዱትም ትእዛዙንና መንገዱን ይጠብቃሉ። 16 እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ፈቃዱን ይሻሉ፤ የሚወዱትም በሕጉ ይረካሉ፤ 17 እግዚአብሔርን የሚፈሩ ልቡናቸውን ያዘጋጃሉ። በፊቱም ሰውነታቸውን ያዋርዳሉ። 18 በሰው እጅ ከምንወድቅ በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፥ እንደ ልዕልናው የቸርነቱ ብዛት እንዲሁ ነውና። |