ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ሰካራም ሠራተኛ አይበለጥግም፥ ጥቂቱን የሚያቃልል ብዙውን ያጠፋል። 2 መጠጥና ሴት ጠቢባንን ያስትዋቸዋል፥ ጋለሞታን የሚከተላት በደለኛ ነው። 3 የዚህም ፍጻሜው ትልና ጥፋት ነው። ደፋር ሰውነት ከመከራ አትጠበቅም። 4 ፈጥኖ የሚያምን ልቡናው ቀሊል ነው፥ ኀጢአትን የሚሠራም ራሱን ይበድላል። 5 ልቡናውን ደስ የሚያሰኝ ሰው ይደነቃል። 6 ብዙ መናገርንም የሚጠላ ኀጢአቱን ያሳንሣል። 7 የሰማኸውን ቃል አታውጣ፥ አትድገመውም፥ ለዘለዓለሙም የባሰ አያገኝህም። 8 በወዳጅና በጠላት ዘንድ የምትናገረው ነገር አይኑር፥ ስተህ የሠራኸው ኀጢአትህንም አትናገር። 9 ቢሰማ አይሰውርልህምና፥ እስክትሞትም ድረስ ይጠብቅሃል። 10 የሰማኸውን ቃል አታውጣ፥ ከዚህም በኋላ የሚያገኝህ ክፉ ነገር እንደሌለ እመን። 11 አላዋቂ ሰው የሰማውን ነገር እስከሚያወጣ ድረስ ይቅበዘበዛል፥ ልጅ የምትወልድ ሴትም በምጥ እንደምትጨነቅ ይጨነቃል። 12 የተወጋ ሰውም ጦሩን ከላዩ ይነቅል ዘንድ እንደሚቸኩል፥ አላዋቂ ሰው የሰማውን ቃል ያወጣ ዘንድ ይቸኩላል። 13 ወዳጅህን አላደረገ እንደ ሆነ ወይም አድርጎ እንደ ሆነ እንዳይደግም ገሥጸው። 14 ወዳጅህን፥ አልተናገረ እንደ ሆነ ወይም ተናግሮ እንደ ሆነ እንዳይደግም ገሥጸው። 15 ወዳጅህን በጥላቻ ነገር ተሠርቶበት ይሆናልና ገሥጸው፤ ከልቡ ሳይፈቅድ የሚሳሳት ሰው አለና የነገሩህን ነገር ሁሉ አትመን። 16 በአንደበቱ የማይሳሳት ማን ነው? 17 ቍጣ ሳይበዛ ወዳጅህን ገሥጸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሕግም ቍጣን አሳልፋት። 18 ጥበብ ሁላ እግዚአብሔርን መፍራት ናትና፥ ጥበብም ሁላ ሕጉን ታስጠብቃለችና። እውነተኛና ሐሰተኛ ጥበብ 19 ክፉን የሚያስተምር ጥበብ የለም፥ ለኃጥኣንም ምክር ጥበብ የላትም። 20 ከሁሉ የምትረክስ ክፋት አለች፥ አእምሮ የጐደለው አላዋቂም አለ። 21 ነገር ግን ከሚራቀቅ፥ የእግዚአብሔርንም ሕግ ከሚክድ ይልቅ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ አላዋቂ ይሻላል። 22 እየበደለ የሚራቀቅና የሚጠነቀቅ አለ፥ ለባልንጀራው የሚያደላ፥ ለወዳጁም ፍርድን የሚያቀና መስሎ ፍርድን የሚለውጥ ሰው አለ። 23 እያመሰገነ ለክፉ ነገር የሚያደላ ሰው አለ፥ ልቡናው ግን ሽንገላን ተሞልትዋል። 24 በልቡናው ሌላ ነገር እያለ ፊት አይቶ የሚያዳላ አለ፥ ባላሰብኸውም ነገር ይመጣብሃል። 25 ኀይሉ ቢደክም፥ በአንተም ላይ ክፉ ማድረግ ቢሳነው፥ ያስትህ ዘንድ መከራን በግድ ያመጣብሃል። 26 ሰው በመልኩ ይታወቃልና፥ ጠቢብም በገጹ ይታወቃል። 27 ካለባበሱና ካካሄዱ፥ ከአሳሣቁም የተነሣ፥ የሰው ጠባዩ ይታወቃል። |