ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ለዘለዓለም ሕያው የሆነ እርሱ ሁሉን በአንድነት ፈጠረ። 2 እውነተኛ እግዚአብሔር ብቻ ነው። 3 ሥራውን ያውቅ ዘንድ ማንንም አላሰናበተውም፤ የገናናነቱንስ ፍለጋ ማን መርምሮ ያውቃል? 4 ከሀሊነቱንስ ማን መርምሮ ያውቃል? ቸርነቱንስ ማን ጠንቅቆ ይናገራል? 5 መጨመርም የለም፤ መቀነስም የለም፤ የእግዚአብሔርን የጌትነቱን ፍለጋ የሚያገኝ የለም። 6 ሰውን በፈጠረው ጊዜ ያንጊዜ ያዝዘዋል፤ ዘመኑንም ባስጨረሰው ጊዜ ያንጊዜ ያሳርፈዋል። 7 ሰው ምንድን ነው? ጥቅሙስ ምንድን ነው? 8 በጎነቱ ምንድን ነው? ክፋቱስ ምንድን ነው? የዘመኑም ቍጥር ቢበዛ መቶ ዓመት ነው፤ 9 በባሕር ውስጥ እንደ አንዲት የውኃ ጠብታ፥ ከአሸዋውም ሁሉ እንደ አንዲት የአሸዋ ቅንጣት፥ እንዲሁ በዘለዓለማዊነት ዓመታት ዘንድ የሰው ዘመኑ ጥቂት ነው። 10 ስለዚህ ነገር እግዚአብሔር ይታገሣቸዋል። ምሕረቱን አሳደረባቸው። 11 ፍጻሜያቸው ክፉ እንደ ሆነ አይቶ ዐወቃቸው፤ ምሕረቱን እንዲሁ አብዝትዋልና። 12 ሰው ባልንጀራውን ብቻ ይቅር ይላል፥ እግዚአብሔር ግን ፍጥረቱን ሁሉ ይቅር ይላል፤ 13 ይቈጣል፥ ይገርፋል፥ ይቅር ይላል፥ እረኛም መንጋውን እንዲመልስ ይመልሳል። በተግሣጹ የሚታገሡትን፥ ሕጉንም የሚከተሉትን ሰዎች ይቅር ይላቸዋል። የተወደደ ምጽዋት 14 ልጄ ሆይ፥ በደስታህ መካከል ኀዘንን አታስገባ፤ በምትስጠውም ሁሉ ክፉ ነገርን አትናገር። 15 ዝናም ዋዕይን የሚያቀዘቅዘው አይደለምን? እንዲሁ በጎ ቃል ከመስጠት ይሻላል። 16 እነሆ እንግዲህ ከመስጠት መልካም ቃል አይሻልምን? ሁለቱም ሁሉ በጻድቅ ሰው ዘንድ ይገኛሉ። 17 ንፉግ ልቡናውን ደስ ሳይለው ይሰጣል። ሰነፍም ይላገዳል አያመሰግንምም። 18 ሳትናገር ተረዳ፥ ሳትታመምም ዳን። 19 ሳይፈረድብህ ራስህን መርምር፤ በመከራህም ጊዜ ይቅርታን ታገኛለህ። 20 ሳትደክም ራስህን አዋርድ፥ በበደልህም ጊዜ ንስሓ ግባ። 21 ስእለትህን ፈጥነህ ስጥ፤ ሳትሞትም ጽድቅን ሥራት። 22 ሳትሳልም አስቀድመህ ስእለትህን አዘጋጅ፤ እግዚአብሔርን እንደሚፈታተነው ሰው አትሁን። 23 በተቈጣህም ጊዜ የሞትን ቀን ዐስብ፤ የፍዳህንም ቀን ዐስብ፤ ንስሓም ግባ ጸልይም። 24 በጥጋብህ ወራት የረኃብን ወራት ዐስብ። በተድላህም ወራት የችግርን ወራት ዐስብ። 25 ኑሮ ከጧት እስከ ማታ ድረስ ትለዋወጣለችና፥ ሁሉም በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ጊዜ ፈጥኖ ይደረጋልና። 26 ብልህ ሰው ግን ፈርቶ በሁሉ ይጠበቃል፤ ኀጢአት በሚሠራበትም ጊዜ ንስሓ ይገባል። 27 አስተዋይ ሰው ሁሉ ጥበብን ያገኛታል፤ ያገኛትንም ሰው ታስመሰግነዋለች፥ ታስከብረዋለችም፥ 28 ነገር ዐዋቂዎች ራሳቸው በልቡናቸው ይራቀቃሉ፤ የተረዳ ምሳሌንም ይናገራሉ። 29 አትሂድ፥ የኀጢአትንም ፈቃድ አትከተል፤ ከክፉ ፍትወትም ራቅ። 30 ለሰውነትህ የምትወድደውን ከሰጠኻት፥ ጠላትህን በአንተ የጨከነ ታደርገዋለች። 31 በተድላ ብዛት ደስ አይበልህ፤ ከእርስዋም ጋር ደስ ይልህ ዘንድ አትለምን። 32 እንዳትያዝ አንተ ድሃ ሳለህ፥ በከረጢትህም ምንም ሳይኖርህ አትበደር። |