ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እግዚአብሔር ሰውን ከምድር ፈጠረው፥ ዳግመኛም ወደ ምድር ይመልሰዋል። 2 ዓመታትንና ቀናትን በቍጥር ሰጣቸው፤ በውስጧም ያለውን ሁሉ አስገዛቸው። 3 ለእየራሳቸው ኀይልን አሳደረባቸው፤ በምሳሌውም ፈጠራቸው። 4 ፍጥረቱ ሁሉ እንዲፈሩአቸው አደረገ። 5 አውሬዎችንና ወፎችንም እንዲገዟቸው አደረገ። 6 ቃልንና አንደበትን፥ ዐይንና ጆሮን፥ የሚያስቡበት ልቡናንም ሰጣቸው። 7 ጥበብን ማወቅንም አጠገባቸው፤ ክፉንና በጎንም አሳያቸው። 8 የሥራውን ገናናነትና መፈራቱንም ያሳያቸው ዘንድ፥ በልቡናቸው ፍርሀትን አሳደረባቸው። 9 ቅዱስ ስሙን ያመሰግኑት ዘንድ። 10 የሥራውንም ገናናነት ይናገሩ ዘንድ፥ 11 ጥበብን ሰጣቸው፤ የሚያድናቸው ሕጉንም አወረሳቸው። 12 የዘለዓለም መሐላንም ተማማላቸው፤ ፍርዱንም ነገራቸው። 13 ዐይኖቻቸውም የጌትነቱን ገናናነት አዩ። 14 የጌትነቱንም ቃል ጆሮቻቸው ሰሙ፥ 15 ከኀጢአት ሁሉ ተጠበቁ አላቸው፤ ሁሉንም ባልጀራችሁን ውደዱ ብሎ አዘዛቸው። 16 መንገዳቸውም ሁልጊዜ በፊቱ ነው፥ ከዐይኖቹም የሚሰወሩበት የላቸውም። 17 ለአሕዛብ ሁሉ ነገሥታትን አነገሠላቸው። 18 እስራኤል ግን የእግዚአብሔር ክፍል ሆነ። 19 ሥራቸውም ሁሉ በፊቱ እንደ ፀሐይ ነው፤ ዐይኖቹም ሁልጊዜ መንገዳቸውን ያያሉ። 20 ኀጢአታቸውም ከእርሱ አልተሰወረችም፤ በደላቸውም ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ነው። 21 የሰው ምጽዋቱ ከእርሱ ጋራ እንደ ማኅተም ነው። 22 የሰው ዋጋው እንደ ዐይን ብሌን ትጠበቅለታለች። 23 ኋላ ተመልሶ ዋጋቸውን ይሰጣቸዋል፤ የኀጢአታቸውንም ፍዳ ወደ ራሳቸው ይመልሳል። 24 ነገር ግን ንስሓ የሚገቡበትን መንገድ ሰጣቸው፤ ተስፋ የቈረጡ ሰዎችንም ደስ ያሰኛቸዋል። የንስሓ ጥሪ 25 ወደ እግዚአብሔር ተመለስ፥ ኀጢአትንም ተዋት በፊቱም ጸልይ፥ ለበደልህም ንስሓ ግባ፤ 26 ከበደልህም ወደ እግዚአብሔር ተመለስ፤ ኀጢአትን ሁሉ ጥላ ፈቃዱንም አድርግ። 27 በሕይወት ሳሉ እንደሚገዙለት ሰዎች፥ ልዑልን በመቃብር የሚያመሰግነው ማንነው? 28 የሞተ ሰውን ግን ንስሓ እንደ ኢምንት አለፈው፤ በሕይወትህ ደስ እያለህ እግዚአብሔርን አመስግነው። 29 የእግዚአብሔር ቸርነቱ ታላቅ ነውና፤ የሚገዙለትን ሰዎች ይቅር ይላቸዋል። 30 ሰው ሟች ስለ ሆነ፥ ሁሉ በሰው ዘንድ ሊሆን አይችልም። 31 ከፀሐይ የሚበራ ምን አለ? እርሱም እንኳ ያልፋል። ደማዊና ሥጋዊም ክፉ ነገርን ያስባል። 32 እርሱ የሰማይን ምጥቀት ኀይል ያውቃል፥ ሰው ሁሉ ግን አመድና ትቢያ ነው። |