ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ጥቅም የሌላቸው ብዙ ልጆችን አትመኝ፤ በክፉዎች ልጆችም ደስ አይበልህ። 2 በእነርሱ እግዚአብሔርን መፍራት ከሌለባቸው፥ ቢበዙም በእነርሱ ደስ አይበልህ። 3 በሕይወታቸውም አትተማመንባቸው፥ ብዛታቸውም ደስ አያሰኝህ። ከሺህ አንድ ደግ ይሻላል፥ ክፉን ከመውለድም ሳይወልዱ መሞት ይሻላል። 4 በአንድ ዐዋቂ ሀገር ትጸናለችና፥ በኀጢአተኞች ብዛት ግን ትጠፋለች። 5 ዐይኔ እንዲህ ያለ ብዙ ነገርን አየች። ጆሮዬም ከዚህ የሚበልጥ ሰማች። 6 በኀጢአተኞች ወገኖች እሳት ትነድዳለች፤ በወንጀለኞች ሕዝብ ላይም ጥፋት ትነድዳለች። 7 በኀይላቸው የታመኑ የቀደሙ አርበኞችም ራሳቸውን አላዳኑም። 8 ሎጥ ለኖረባቸው፥ ራሳቸውንም ላኮሩ፥ ሎጥንም ለተጸየፉት ሀገሮች አልራራላቸውም። 9 ኀጢአተኞች ሕዝቦችን ይቅር አላላቸውም፤ በኀጢአታቸው ጠፉ እንጂ። 10 እነዚህም የተሰበሰቡ፥ ልቡናቸውንም ያከፉ፥ ስድስት መቶ ሺህ እግረኞች ነበሩ። 11 ክሣደ ልቡናውን ያጸና አንድ ሰው ቢኖር እርሱ ቢድን ድንቅ ነው፥ ይቅርታም መቅሠፍትም ከእርሱ ዘንድ ነውና ይቅር ማለት ይችላል፤ መቅሠፍትንም ማምጣት ይችላል። 12 ቍጣው እንደ ቸርነቱ ብዛት መጠን ነው፥ ለሰውም እንደ ሥራው ይከፍለዋል። 13 ኀጢአተኛ ሰው ከዳፋ አያመልጥም፤ ጻድቅ ሰውም የትዕግሥቱን ዋጋ አያጣም። 14 ምጽዋት ሁሉ ይቅርታን ያመጣል፤ ሰውም ሁሉ እንደ ሥራው ያገኛል። 15 “ከእግዚአብሔር አመልጣለሁ፤ በሰማያትም የሚያገኘኝ የለም። 16 በብዙ አሕዛብም ዘንድ የሚያውቀኝ የለም። 17 የሰውነቴስ ቍጥሯ በዓለም ሁሉ ምንድን ነው?” አትበል። 18 እነሆ፥ ሰማይ፥ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ፥ ከሰማይም በታች ያለ ውቅያኖስ፥ ምድርም፥ በመዓት በጐበኛቸው ጊዜ ይህ ሁሉ ይነዋወጣል። 19 ተራሮችም፥ የምድርም መሠረቶች፥ በመዓት ባያቸው ጊዜ ይንቀጠቀጣሉ ይነዋወጣሉም። 20 ይህንም ልብ አያስበውም፤ መንገዶቹንስ ማወቅ ማን ይችላል? ገናናነቱንስ ጠብቆ መናገር ማን ይችላል? 21 ከሥራውም አብዛኛው ስውር ነው፥ ሰው የማያየው ዐውሎ ነፋስ ነውና። 22 እውነት ሥራ መሥራትን ማን ያስተምራል? የምሕረቱንስ ተስፋ ማን ደጅ ይጠናል? 23 አእምሮ የሌለው ሰው እንዲህ ያስባል፤ ሰነፍና በደለኛ ሰውም ስንፍናን ያስባል። የእግዚአብሔር ጥበብ በሥነ ፍጥረት 24 ልጄ ሆይ፥ ስማኝ፥ ጥበብንም ተማር፥ ነገሬንም ከልቡናህ አድምጠው። 25 በሚዛን መዝነህ ጥበብህን ግለጣት፤ የትምህርትህንም ነገሯን ተረዳ። 26 የእግዚአብሔር ሥራ ከጥንት ጀምሮ በሥልጣኑ ተፈጠረ። ሥርዐታቸውንም በየወገናቸው ለየ። 27 ዓለም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖር ዘንድ ሥራውን ሁሉ አዘጋጀ፥ ሠራዊታቸውንም በየወገናቸው አዘጋጀ፥ አይሠሩም፥ አይጠሙም፥ አይራቡምም፥ ሥራቸውም አይቋረጥም፤ 28 አንዱ ከሌላው ጋር አይጨናነቅም፤ ለዘለዓለሙም ከቃሉ አይወጡም። 29 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ምድርን ተመለከተ፤ ከበረከቱም አጠገባት። 30 በደማዊት ነፍስ ሕያው የሆነ ፍጥረት ሁሉ በምድር መላ፤ መመለሻቸውም ወደ ምድር ነው። |