ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንዲህ ያደርጋል፤ ሕጉንም የሚጠብቅ ሰው ጥበብን ያገኛታል። 2 እንደ እናቱ ትንከባከበዋለች፤ እንደ ቆንጆ ሴትም ትቀበለዋለች። 3 የጥበብን እህል ትመግበዋለች፤ የዕውቀትንም ውኃ ታጠጣዋለች። 4 በእርስዋ ይመረኰዛል፥ አይፍገመገምም፤ የሚታመንባትም አያፍርም። 5 ከባልንጀራው ይልቅ ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፥ በብዙ ሰዎች መካከልም አፉን ገልጦ ይናገራል። 6 ደስታን ትሰጠዋለች፥ የደስታ ዘውድንም ታቀዳጀዋለች፥ ስሙንም ለዘለዓለም ያስጠራል። 7 አላዋቂዎች ግን አያገኙአትም፤ ኀጢአተኞችም አያዩአትም። 8 ከትዕቢተኞች ሰዎችም የራቀች ናት፤ ሐሰተኞች ሰዎች አያስቧትም። 9 የኀጢአተኛ ሰው የቃሉ ነገር ያማረ አይደለም፥ እግዚአብሔርን በመፍራት የሚናገር አይደለምና። 10 ምሳሌን በጥበብ ይናገሯታል፤ እግዚአብሔርም የሚማራትን ሰው ይረዳዋል። 11 “ስለ እግዚአብሔር ብዬ ተከለከልሁ” አትበል፤ እርሱ የሚጠላውንም አታድርግ። 12 “እርሱ አሳተኝ” አትበል፤ እርሱስ ኀጢአተኛ ሰውን አይወድድም፤ 13 እግዚአብሔር የረከሰውን ሁሉ ይጠላልና፤ የሚፈሩትንም ሰዎች ይወዳቸዋል። 14 እርሱ አስቀድሞ ሰውን በንጽሕ ፈጠረው፥ እንደ ጠባዩም በወደደው እንዲሠራ ተወው። 15 ትእዛዙን ትጠብቅ ዘንድ፥ ሃይማኖቱንም ታጸና ዘንድ ብትወድ ግን ፈቃዱ ነው። 16 እጅህን በመረጥኸው ትጨምር ዘንድ፥ እነሆ፥ እሳትንና ውኃን አኖረልህ። 17 ሕይወትና ሞትም በሰው ፊት ናቸው፥ ከእነርሱም የመረጠውን ይሰጡታል። 18 የእግዚአብሔር ጥበቡ ታላቅ ነውና፥ ኀይሉም የጸና ነውና ሁሉን ያውቃል፥ ሁሉንም ያያል። 19 ዐይኖቹም የሚፈሩትን ሰዎች ይመለከታሉ፤ እርሱም የሰውን ሥራ ሁሉ ያውቃል። 20 እርሱስ ኀጢአትን ይሠራ ዘንድ ያዘዘው የለም፤ ይበድልም ዘንድ ማንንም አላሰናበተም፤ |