ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከጓደኛ ስለ መጠበቅ 1 አደሮ ማር የዳሰሰ ሰው በእርሱ ይያዛል፤ ትዕቢተኛ ሰውንም ወዳጅ ያደረገ እንደ እርሱ ይሆናል። 2 የከበደ ሸክምን አንሥተህ በራስህ አትሸከም፥ ገንዘብህንም ከሚበረታብህና ከባለጸጋ ገንዘብ ጋራ አትጨምር፥ የሸክላ ድስት ከብረት ድስት ጋር በየት አንድ ይሆናል? እርስዋ መትታ እርስዋ ትጮኻለችና፥ እርስዋም ትሰብራለችና። 3 እንደዚሁ ሁሉ ባለ ጸጋ እርሱ ይበድላል፥ እርሱም ይቈጣል፤ ድሃ ግን እርሱ ይገፋል፥ እርሱም ይለማመጣል። 4 የምትጠቅመው ነገር ቢኖር ወደ እርሱ ያቀርብሃል፤ ብትቸገር ግን ከዚያ በኋላ አያይህም። 5 ገንዘብ ቢኖርህ ከአንተ ጋራ አንድ ይሆናል፥ ያንተንም ይጨርስልሃል፤ ዳግመኛም አያመሰግንህም። 6 አንተን የሚፈልግበት ግዳጅ ቢኖረው ያባብልሃል፤ ብዙ ተስፋም ይሰጥሃል፤ ይሥቅልሃል፤ በጎ ነገርም ይናገርሃል፤ ምን ትፈልጋለህም ይልሃል። 7 በመብሉም ይሸነግልሃል፤ አንድ ጊዜ፥ ሁለት ጊዜ፥ ሦስት ጊዜም ያስትሃል፤ ከዚህም በኋላ እንደማይሰማህ ወደ ኋላ ይመለሳል፤ ቢያይህም ይሥቅብሃል፤ ራሱንም ይነቀንቅብሃል። 8 እንዳያስትህና እንዳያታልልህ ከእንዲህ ያለ ሰው ተጠበቅ፥ በደስታህም መካከል ኀዘን አታግባ። 9 ባለጸጋ ያዘዘህን ለጊዜው እሽ በለው፥ ቢጠራህም እንቢ አትበለው፤ ፈጽሞም ይወድሃል። 10 አትራቅ አትሳትም፥ ነገር ግን እንዳይዘነጋህ ፈጽመህ አትራቀው። 11 ከእርሱ ጋር ነገርን አታብዛ፤ በነገሩ ብዛት ይፈትንሃልና፤ ከአንተም ጋራ የሚሥቅ መስሎ ይመረምርሃልና በነገሩ ብዛት አትመነው። 12 መታሰሩና ጥፋቱ አያሳዝነውምና፥ የባልንጀራውን ምሥጢር ለሚያወጣ ሰው ይቅርታ የለውም። 13 ከገዳይህ ጋር ትሄዳለህና ዕወቅ፤ አጥብቀህም ተጠበቅ። 14 ከብት ሁሉ ዘመዱን ይወድዳል፤ ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ይወድዳል። 15 ፍጥረቱ ሁሉ እንደ እርሱ ካለ ፍጥረት ጋራ አንድ ይሆናል፤ ሰውም የሚመስለውን ይከተላል። 16 ተኵላ ከበግ ጋር በየት ወዳጅ ይሆናል? ኀጢአተኛ ሰውም ከጻድቅ ሰው ጋራ እንዲሁ ነው። 17 ውሾችን ከጅቦች ጋር ማን ያስማማቸዋል? ድሃውንስ ከባለጸጋው ጋራ ማን ወዳጅ ያደርገዋል? 18 የሜዳ አህዮች የአንበሶች አደን ናቸው፤ እንደዚሁም ሁሉ ባለጸጋው ድሃውን ይቀማዋል። 19 ትዕቢተኛ ሰው ራሱን የሚያዋርደውን ሰው ይጸየፈዋል፤ እንዲሁም ሁሉ ባለጸጋው ድሃውን ይጸየፈዋል። 20 ባለጸጋ ቢፍገመገም ወዳጆቹ ይደግፉታል፤ ድሃ ግን ቢወድቅ ባልንጀሮቹ ይረግጡታል። 21 ባለጸጋ ቢያድጠው ብዙ ሰዎች ያነሡታል፥ ክፉ ቢናገርም ነገሩን ያቀኑለታል፤ ድሃ ግን ቢስት ይረግሙታል፤ በጎ ነገርም ቢናገር አያደምጡትም። 22 ባለጸጋ ቢናገር ሁሉ ዝም ይላል፤ ቃሉንም ያደንቁለታል፥ ነገሩንም እስከ ደመና ያደርሱለታል፤ ድሃ ግን ምንም በጎ ነገር ቢናገር ይህ ምንድን ነው? ይሉታል፤ ቢሰነካከልም ያዳፉታል። 23 ኀጢአት ሳትሠራ ባለጸግነት መልካም ነው፤ ኃጥእ ድህነቱን ባፉ ያክፋፋታል። 24 ደስ ቢለው፥ ቢያዝንም የሰው ልቡ ፊቱን ይለውጠዋል። 25 ደስ ያለው ልቡና ምልክቱ ብሩህ ገጽ ነው፥ ደክመህ የጥበብን ምክር ታገኛለህ። |