ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በጎ ሥራ በሠራህ ጊዜ የበጎነትህን ዋጋ ታገኝ ዘንድ፥ በጎ ሥራ የምትሠራለትን ዕወቅ። 2 ለጻድቅ በጎ አድርግ፥ ዋጋህንም ታገኛለህ፤ በእርሱ ዘንድ ባታገኘው በፈጣሪው ዘንድ ታገኛለህ። 3 ኀጢአትን በሚሠራና ምጽዋትን በማይመጸውት ዘንድ፥ በጎ ሥራ የለም። 4 ኀጢአተኛ እንዳይወስድብህ ለጻድቁ ስጥ። 5 ለድሃ መልካም አድርግ፥ ለክፉ ግን አትስጥ፤ እርሱ እንዳይወስድብህና በገንዘብህ ድል እንዳያደርግህ እንጀራህን ከልክለው፥ በጎ ነገር ስላደረግህለት ፋንታ በእርሱ ዘንድ ክፋትን እጥፍ ሆና ታገኛታለህና። 6 እግዚአብሔር ኀጢአተኞች ሰዎችን ይጠላቸዋልና፤ ክፉ ሰዎችንም ይበቀላቸዋልና። 7 ለኀጢአተኛ ከምትሰጥ ለጻድቅ ስጥ፤ በደስታም ጊዜ ወዳጅህ አያምልጥህ። 8 በመከራህም ጊዜ ጠላትህ አይሰወርህ። 9 ደስታህ ጠላቶችህን ያሳዝናቸዋል፤ ችግርህም ወዳጆችህን አስወጥቶ ይሰድዳቸዋል። 10 የልቡናው ክፋት እንደ ብረት ዝገት ነውና፤ ጠላትህን ፈጽመህ አትመነው። 11 በተቸገርህም ጊዜ እያመሰገነ ያገለግልሃል፤ ሰውነትህን አጽናት፤ ከእርሱም ተጠበቅ፤ እንደዛገ መስታወት ትሆንበታለህ፤ ፈጽሞም አይችልህም። 12 እንዳይጎዳህ ባጠገብህ አታቁመው፥ በቦታህም አይቀመጥ፤ ሹመትህንም እንዳይወስድብህ በቀኝህ አታስቀምጠው። በመጨረሻም ቃሌን ታውቀው ዘንድ አለህ፥ ምክሬንም ታስበዋለህ። 13 በእባብ ለተነደፈ አስማተኛ፥ ወደ ክፉ አውሬም ለቀረበ ሁሉ ማን ያዝንለታል? 14 ከኀጢአተኛም ሰው ጋር የሚሄድ፥ በኀጢአቱም የሚተባበር እንዲሁ ነው። 15 ጠላትህ ከአንተ ጋር አንድ ጊዜ ይቆማል፥ ነገር ግን እስክትመለስ ድረስ አታየውም፥ ከአንተም ጋር አይታገሥም። 16 ጠላትህ በከንፈሩ ቃሉን ያጣፍጥልሃል፥ በልቡ ግን በጕድጓድ ውስጥ ይጥልህ ዘንድ ይመክራል። ጠላትህ በዐይኑ ያለቅስልሃል፥ ካሳተህ በኋላ ግን ከደምህ አይጠግብም። 17 ብትቸገርም ከሁሉ አስቀድሞ በፊትህ ታገኘዋለህ፤ እንደሚረዳህም ከጫማህ በታች ራሱን ዝቅ ያደርጋል። 18 በእጁ ያጨበጭባል፤ ራሱንም ይነቀንቃል፤ ከዚህ በኋላ ግን ፊቱን መልሶ ይጠቃቀስብሃል። |