ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ጠቢብ ንጉሥ ሕዝቡን ይመክራል፥ አስተዋይ ዳኛም ሥርዐትን ይሠራል። 2 ሎሌውም እንደ ሕዝቡ አለቃ ነው፤ የከተማው ገዥ እንደሚሠራው በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች ይሠራሉ። 3 አላዋቂ ንጉሥ ሕዝቡን ያጠፋል፤ ሀገርም በሽማግሌዎች ጥበብ ትጸናለች። 4 የምድር ግዛት በእግዚአብሔር እጅ ነው፥ በጊዜውም የሚጠቅመውን ሰው በእርስዋ ላይ ያስነሣል። 5 የሰው በረከቱ በእግዚአብሔር እጅ ነው፥ በጸሓፊም ሰውነት ክብሩን ያኖራል። በትዕቢት የሚመጣ ኀጢአት 6 ባልንጀራህን በሳተበት ሁሉ አትንቀፈው፥ በነቀፋህም ምንም ክፉ ነገር የምታደርግበት አይኑር። 7 ትዕቢት በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ የተጠላ ነው፥ ከሁሉም ዐመፅ ትከፋለች። 8 መንግሥትም ስለ ዐመፅና ክርክር፥ ስለ ገንዘብም፥ ካንዱ ወገን ወደ ሌላው ወገን ትፈልሳለች። 9 እንግዲህ ትቢያና ዐመድ የሚሆን፥ በሕይወትም ሳለ ሰውነቱ የሚተላ ሰው ለምን ይታበያል? 10 የሰፋ ቍስልን ባለ መድኀኒት ያድነዋል፤ ንጉሥ መባል ግን ለዛሬ ብቻ ነው፥ ነገም ይሞታል። 11 ሰውም ከሞተ በኋላ የትል ዕድል ፋንታ ይሆናል። 12 የትዕቢት መጀመሪያ ሰውን ከእግዚአብሔር ትለየዋለች፤ ልቡናውንም ከፈጣሪው ታርቀዋለች። 13 ትዕቢት የኀጢአት መጀመሪያ ናት፤ በአጸናትም ሰው ላይ ርኵሰትን ታበዛበታለች፥ ስለዚህም እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ፍዳ ይገልጣል፥ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል። 14 እግዚአብሔር ያለቆችን ዙፋን ያፈርሳል፤ በእነርሱም ፋንታ የዋሃንን ይሾማል። 15 እግዚአብሔር የአሕዛብን ሥራቸውን ነቀለ፥ በእነርሱም ፋንታ ትሑታንን ተከለ። 16 እግዚአብሔር የአሕዛብን ሀገሮች አጠፋ፥ እስከ ምድር መሠረት ድረስ አጠፋቸው። 17 ፈጽሞም አጠፋቸው፥ ስም አጠራራቸውንም ከምድር ደመሰሰ። 18 ትዕቢት ለሰው የተፈጠረ አይደለም፥ ቍጣና ጥፋትም ከሴት ለሚወለድ ሰው አይደለም። ክብር ስለሚገባቸውና ስለማይገባቸው 19 የሰው ዘር የከበረ ዘር ነው፥ የከበረ ዘር ማንነው? እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ዘር አይደለምን? 20 የሰው ዘር የጐሰቈለ ዘር ነው፥ ጐስቋላው ዘር ማንነው? የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የማይጠብቁ ሰዎች ዘር አይደለምን? 21 ዳኛ ከባልንጀራው ይልቅ የከበረ ነው፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ግን ከእርሱ ይልቅ ይከብራሉ። 22 ለባለጸጋውና ለከበርቴው ለድሃውም ክብራቸው እግዚአብሔርን መፍራት ነው። 23 ድሃውን ስለ ድህነቱ ይንቁት ዘንድ አይገባም፥ ኀጢአተኛውንም ሰው ስለ ባለጸግነቱ ያከብሩት ዘንድ አይገባም። 24 ታላላቆችና አለቆች፥ መኳንንቱም ይከብራሉ፤ ከእነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውን የሚበልጠው የለም። 25 ጠቢብ ቤተ ሰብ በንጹሕ ያገለግላል፥ ዐዋቂ ሰውም አይነቅፈውም። 26 ሥራህን ስትሠራ አትራቀቅ፥ በችግርህም ወራት አትመካ። 27 ከሚዞርና ከሚመካ፥ ምግቡንም ከማያገኝ ሰው ይልቅ፥ የሚያርስና የሚቈፍር ይሻላል። 28 ልጄ ሆይ፥ በየዋህነትህ ሰውነትህን ደስ አሰኛት፥ የተቻለህንም ያህል አዘጋጃት። 29 ለራሱ የሚነፍግ ለማን ቸር ይሆናል? ሰውነቱን የማያዘጋጃትን ሰውስ ማን ያመሰግነዋል? 30 ድሃውን ስለ ጥበቡ ያመሰግኑታል፥ ባለጠጋውን ግን ስለ ባለጠግነቱ ያመሰግኑታል። 31 በተቸገረ ጊዜ የማያዝን ሰው፥ በተዘጋጀ ጊዜ እንዴት ደስ ይለው? |