ሮሜ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ መረጠ 1 በክርስቶስ እውነት እነግራችኋለሁ፤ ሐሰትም አልናገርም። ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልናል፤ 2 በጊዜው ሁሉ ብዙ ኀዘን፥ የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለ። 3 በሥጋ ዘመዶችና ወንድሞች ስለሚሆኑ እኔ ከክርስቶስ እለይ ዘንድ እጸልያለሁ። 4 እናህም ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው፥ ተስፋም የተሰጣቸው እስራኤላውያን ናቸው። 5 እነርሱም አባቶቻችን ናቸው፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን። 6 ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል አይታበልም፤ እስራኤል ሁሉ እስራኤላውያን አይደሉምና። 7 የአብርሃም ዘር ሁሉ ልጆቹ የሆኑት አይደለም፤ ከይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል አለው እንጂ። 8 ልጆች እንዲሆኑት ተስፋ ያናገረለት የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፤ እነዚህ ከሥጋ የተወለዱ ግን የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም። 9 “ከርሞ እንደ ዛሬ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ታገናለች፤” ብሎ ተስፋ ሰጥቶታልና። 10 ነገር ግን ለእርስዋ ብቻ አይደለም፤ ርብቃም ለአባታችን ለይስሐቅ መንታ በፀነሰች ጊዜ፥ 11 ሳይወለዱ፥ ክፉና መልካም ሥራም ሳይሠሩ የእግዚአብሔር መምረጡ በምን እንደ ሆነ ይታወቅ ዘንድ፥ 12 እርሱ የጠራው ነው እንጂ ሰው በሥራው የሚመረጥ አንዳይደለም ያውቁ ዘንድ፥ ለርብቃ፥ “ታላቁ ለታናሹ ይገዛል” አላት። 13 “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአልና። 14 እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያደላልን? አያደላም። 15 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፥ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ ይቅር የምለውንም ይቅር እለዋለሁ።” 16 አሁንም ለሮጠና ለቀደመ አይደለም፤ እግዚአብሔር ይቅር ላለው ነው እንጂ። 17 እግዚአብሔርም ለፈርዖን በመጽሐፍ እንዲህ አለው፥ “ኀይሌን በአንተ ላይ እገልጥ ዘንድ፥ ስሜም በምድር ሁሉ ይሰማ ዘንድ ስለዚህ አስነሣሁህ።” 18 እነሆ፥ የሚወድደውን ይምረዋል፤ የሚወድደውንም ልቡን ያጸናዋል። 19 እንግዲህ ምን ትላለህ? አንተ እግዚአብሔርን ትነቅፈዋለህን? ምክሩንስ የሚቃወማት አለን?። 20 ሰው ሆይ፥ እግዚአብሔርን የምትከራከረው አንተ ምንድን ነህ? ሥራ ሠሪውን እንዲህ አታድርገኝ ሊለው ይችላልን? 21 ሸክላ ሠሪ ከአንድ ጭቃ ግማሹን ለክብር፥ ግማሹንም ለኀሳር አድርጎ ዕቃን ሊሠራ አይችልምን? 22 እግዚአብሔርም ኀይሉን የሚገልጽበትን ቅጣቱን ሊያሳይ ቢወድ፥ ትዕግሥቱን ካሳየ በኋላ ለማጥፋት የተዘጋጁትን ቍጣውን የሚገልጽባቸውን መላእክት ያመጣል። 23 ዳግመናም የክብሩን ባለጠግነት ሊያሳይ ቢወድ አስቀድሞ ለወደዳቸውና ለጠራቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የምሕረት መላእክትን ያመጣል። 24 ወደ ክብሩ የጠራንና የሰበሰበንም እና ነን፤ ነገር ግን ከአሕዛብም ነው እንጂ ከአይሁድ ብቻ አይደለም። 25 ነቢዩ ሆሴዕ እንዲህ እንዳለ “ወገኔ ያልነበረውን ወገኔ አደርገዋለሁ፤ ወዳጄ ያልነበረችውንም ወዳጄ አደርጋታለሁ። 26 የእግዚአብሔር ወገኖች አይደላችሁም ይባሉ በነበሩበት ሀገርም የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ።” 27 ኢሳይያስም ድምፁን ከፍ አድርጎ ስለ እስራኤል እንዲህ አለ፥ “የእስራኤል ልጆች ቍጥራቸው እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም የተረፉት ይድናሉ። 28 እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ ያደርገው ዘንድ ያለውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ይናገራልና።” 29 ኢሳይያስም አስቀድሞ እንደ ተናገረ “እግዚአብሔር ጸባኦት ዘር ያስቀረልን ባይሆን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን፥ ገሞራንም በመሰልን ነበር።” በእምነት ስለ መጽደቅ 30 እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅን ያልፈለጉአት አሕዛብ ስንኳ ጽድቅን አገኙአት፤ በእምነትም ጸደቁ። 31 እስራኤል ግን ኦሪትን ሲከተሉ መጽደቅ ተሳናቸው፤ የኦሪታቸውን ሥራ አልፈጸሙምና። 32 ይህስ ስለምን ነው? ጽድቃቸው የኦሪትን ሥራ በመሥራት እንጂ በእምነት ስለ አልሆነ ነው፤ የእንቅፋት ድንጋይ አሰነካከላቸው። 33 መጽሐፍ እንዲሁ “በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይንና የማሰናከያ ዐለትን አኖራለሁ፤ ያመነባትም ለዘለዓለም አያፍርም” ብሎአልና። |