ሮሜ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የአብርሃም ምሳሌነት 1 እንግዲህ በሥጋ የቀድሞ አባታችን የሆነው አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? ይህን በሥራው አግኝቶአልን? 2 አብርሃም በሥራው ጸድቆስ ቢሆን ትምክሕት በሆነው ነበር፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም። 3 መጽሐፍስ ምን ይላል? አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት። 4 ለሚሠራ ዋጋው እንደሚገባው እንጂ በለጋስነት እንደ ሰጡት ሆኖ አይቈጠርበትም። 5 ለማይሠራ ግን ኀጢአተናውን በሚያጸድቀው ካመነ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርለታል። 6 የኦሪትን ሥራ ሳይፈጽም ማመኑ በእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅ ሆኖ የሚቈጠርለትን ሰው ዳዊት “ብፁዕ” በሚልበት አንቀጽ እንዲህ ይላል፦ 7 “መተላለፋቸው የቀረላቸው፥ ኀጢአታቸውም የተሰረየላቸው ብፁዓን ናቸው። 8 እግዚአብሔርም በደሉን የማይቈጥርበት ሰው ብፁዕ ነው።” 9 እንግዲህ ይህ ብፅዕና ስለ መገዘር ተነገረን? ወይስ ስለ አለመገዘር? እምነቱ ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት እንላለንና። 10 ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ የተቈጠረለት መቼ ነው? ተገዝሮ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገዘር? ሳይገዘር ነው እንጂ ተገዝሮ ሳለ አይደለም። 11 ሳይገዘር እግዚአብሔር አብርሃምን በእምነት እንደ አጸደቀው በእርሱ ላይ ይታወቅ ዘንድ ግዝረትን የጽድቅ ማኅተም ትሆነው ዘንድ ምልክት አድርጎ ሰጠው። ሳይገዘሩ ለሚያምኑ ሁሉ አባት ሊሆን፥ አብርሃም በእምነት እንደ ከበረ እነርሱም በእምነት እንደሚከብሩ ያውቁ ዘንድ ሰጠው። 12 ለተገዘሩትም አባት ይሆን ዘንድ ነው፤ ነገር ግን ለተገዘሩት ብቻ አይደለም፤ እርሱ አባታችን አብርሃም ሳይገዘር እንደ አመነ ሳይገዘሩ የአባታችን የአብርሃምን የሃይማኖቱን ፍለጋ ለሚከተሉ ደግሞ ነው እንጂ። ስለ አብርሃምና ስለ ዘሩ ተስፋ 13 አብርሃም፥ ዘሩም ዓለምን ይወርስ ዘንድ ተስፋ ያገኘ የኦሪትን ሥራ በመሥራት አይደለም፤ በእግዚአብሔር ቃል፥ እርሱንም በማመን በእውነተና ሃይማኖቱ ይህን አገኘ እንጂ። 14 የኦሪትን ሕግ የፈጸመ ብቻ ተስፋ የሚያገኝ፥ ዓለምንም የሚወርስ ቢሆን ኖሮ፥ ለአብርሃም እምነቱ ባልጠቀመውም ነበር፤ ተስፋውንም ባላገኘም ነበር። 15 የኦሪት ሕግ በአፍራሹ ላይ ቅጣትን ያመጣልና፤ የኦሪት ሕግም ከሌለ መተላለፍ የለም። 16 ስለዚህም እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የሰጠው ተስፋ የታመነ ይሆን ዘንድ፥ የሚጸድቁ በእምነት እንጂ የኦሪትን ሥራ በመፈጸም ብቻ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ጽድቅን በእምነት አደረገ። 17 “ለብዙዎች አሕዛብ አባት አደርግሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ሙታንን በሚያስነሣቸው፥ የሌሉትንም እንደ አሉ በሚያደርጋቸው በአመነበት በእግዚአብሔር ፊት አብርሃም የሁላችን አባት ነው። 18 አብርሃም “ዘርህ እንዲሁ ይሆናል” ብሎ እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠው ተስፋ ባልነበረ ጊዜ የብዙዎች አሕዛብ አባት እንደሚሆን አመነ። 19 አብርሃም የመቶ ዓመት ሽማግሌ ስለሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሣራ ማኅፀን ምውት መሆኑን እያየ በእምነት አልተጠራጠረም። 20 እግዚአብሔር ያናገረለትንም ተስፋ ይቀራል ብሎ አልተጠራጠረም፤ በእምነት ጸና እንጂ፤ ለእግዚአብሔርም ክብርን ሰጠ። 21 እግዚአብሔርም የሰጠውን ተስፋ ሊያደርግለት እንደሚችል በፍጹም ልቡ አመነ። 22 ስለዚህም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። 23 ነገር ግን “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው ቃል የተጻፈ ስለ እርሱ ብቻ አይደለም። 24-25 ስለ ኀጢአታችን የተሰቀለውን፥ ሊያስነሣንና ሊያጸድቀን የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ በአስነሣው ስለምናምን ስለ እናም ነው እንጂ። |