መዝሙር 97 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት መዝሙር። 1 ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፥ የእግዚአብሔር ሥራ፥ የቀኙ ማዳን፥ የተቀደሰ ክንዱም ድንቅ ነውና። 2 እግዚአብሔር ማዳኑን አሳየ። በአሕዛብም ፊት ቃል ኪዳኑን ገለጠ። 3 ለያዕቆብ ይቅርታውን ለእስራኤልም ቤት እውነቱን አሰበ፤ የምድር ዳርቻዎች ሁሉ፥ የአምላካችንን ማዳን እዩ። 4 በምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ አመስግኑ፥ ደስም ይበላችሁ፥ ዘምሩም። 5 ለእግዚአብሔር በመሰንቆ፥ በመሰንቆና በዝማሬ ድምፅ ዘምሩ። 6 በነጋሪትና በመለከት ድምፅ፥ በንጉሡ በእግዚአብሔር ፊት እልል በሉ። 7 ባሕር በሞላዋ፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ ይናወጡ። 8 ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ፥ ተራሮች ደስ ይበላቸው፥ 9 ለምድር በዚያ ይፈረድላታልና። ለዓለምም በእውነት ይፈረድላታልና። ለአሕዛብም በቅንነት ይፈረዳል። |