መዝሙር 91 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር። 1 በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም መዘመር፤ 2 በማለዳ ምሕረትህን፥ በሌሊትም እውነትህን መናገር፥ 3 ዐሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ። 4 አቤቱ፥ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፤ በእጆችህም ሥራ ደስ ይለኛልና። 5 አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፥ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው። 6 ሰነፍ ሰው አያውቅም፥ ልብ የሌለውም ይህን አያስተውለውም። 7 ኃጥኣን እንደ ሣር በበቀሉ ጊዜ፥ ዐመፃን የሚያደርጉም ሁሉ በለመለሙ ጊዜ፥ ለዘለዓለም ዓለም እንደሚጠፉ ነው። 8 አቤቱ፥ አንተ ግን ለዘለዓለም ልዑል ነህ፤ 9 አቤቱ፥ እነሆ፥ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፥ ዐመፃንም የሚሠሩ ሁሉ ይበተናሉና። 10 ቀንዴ አንድ ቀንድ እንዳለው ከፍ ከፍ ይላል፥ ሽምግልናዬም በዘይት ይለመልማል። 11 ዐይኔም በጠላቶቼ ላይ አየች፥ ጆሮዬም በእኔ ላይ በቆሙ በክፉዎች ላይ ሰማች። 12 ጻድቅ ግን እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ይበዛል፥ 13 በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የተተከሉ ናቸው፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ። 14 ያንጊዜ በመልካም ሽምግልና ይበዛሉ፤ ዕረፍት ያላቸውም ሆነው ይኖራሉ። 15 አምላካችን እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ ይናገራሉ፥ በእርሱም ዘንድ ዐመፃ የለም። |