መዝሙር 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ብንያማዊ ሰው ስለ ኩዝ ቃል ለእግዚአብሔር የዘመረው የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፥ አትጣለኝም፤ ከሚከብቡኝ ሁሉ አድነኝና አውጣኝ፥ 2 ነፍሴን እንደ አንበሳ እንዳይነጥቋት፥ የሚያድንና የሚታደግ ሳይኖር። 3 አቤቱ አምላኬ፥ እንዲህስ ካደረግሁ፥ ዐመፃም በእጄ ቢኖር፥ 4 ክፉ ላደረጉብኝም ክፉን መልሼላቸው ብሆን፥ ጠላቶቼ ዕራቁቴን ይጣሉኝ። 5 ጠላት ነፍሴን ያሳድዳት፤ ያግኛትም፥ ሕይወቴን በምድር ላይ ይርገጣት፤ ክብሬንም በትቢያ ላይ ያዋርደው። 6 አቤቱ፥ በመዓትህ ተነሥ፤ በጠላቶቼ ላይ ተነሣባቸው፤ አቤቱ፥ አምላኬ፥ ባዘዝኸው ሥርዐት ተነሥ። 7 የአሕዛብም ጉባኤ ይከብብሃል፤ ስለዚህም ወደ አርያም ተመለስ። 8 እግዚአብሔር በሕዝብ ላይ ይፈርዳል፤ አቤቱ አምላኬ፥ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፤ እንደ የዋህነቴም ይሁንልኝ። 9 የኃጥኣን ክፋት ያልቃል፥ ጻድቃንን ግን ታቃናቸዋለህ፤ እግዚአብሔር ልቡናንና ኵላሊትን ይመረምራል። 10 እግዚአብሔር በእውነት ይረዳኛል ልበ ቅኖችን የሚያድናቸው እርሱ ነው። 11 እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው፤ ኀይለኛም ታጋሽም ነው፤ ሁልጊዜም ጥፋትን አያመጣም። 12 ባትመለሱ ግን ሰይፉን ይመዝዛል፥ ቀስቱን ገተረ አዘጋጀም፤ 13 የሚገድል መርዝንም አዘጋጀበት፤ ፍላጻዎቹንም የሚቃጠሉ አደረገ። 14 እነሆ፥ ዐመፀኛ በዐመፁ ተጨነቀ፤ ጭንቅን ፀነሰ፤ ኀጢአትንም ወለደ። 15 ጕድጓድንም ማሰ፥ ቈፈረም። ባደረገውም ጕድጓድ ይወድቃል። 16 ጉዳቱ በራሱ ይመለሳል፥ ዐመፃውም በአናቱ ላይ ትወርዳለች። 17 እግዚአብሔርን እንደ ጽድቁ መጠን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔርም ስም እዘምራለሁ። |