መዝሙር 57 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ አታጥፋ። የዳዊት ቅኔ። 1 በእውነት ጽድቅን ብትናገሩስ፥ የሰው ልጆች ሆይ፥ በቅን ትፈርዳላችሁ፤ 2 በልባችሁ በምድር ላይ ኀጢአትን ትሠራላችሁና፥ እጆቻችሁም ሽንገላን ይታታሉና። 3 ኀጥኣን ከማኅፀን ጀምረው ተለዩ፤ ከሆድም ጀምረው ሳቱ፥ ሐሰትንም ተናገሩ። 4 ቍጣቸው እንደ እባብ መርዝ ነው፥ ጆሮዋም እንደ ደነቈረ እባብ፥ 5 ዐዋቂ ሲደግምባት የአስማተኛውን ቃል እንደማትሰማ። 6 እግዚአብሔር ጥርሳቸውን በአፋቸው ውስጥ ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የአንበሶቹን መንጋጋቸውን ያደቅቃል። 7 እንደሚፈስስ ውኃ ይቀልጣሉ፤ እስከሚያደክማቸው ድረስ ፍላጻቹን ይገትራል። 8 እንደሚቀልጥ ሰም ያልቃሉ፤ እሳት ወደቀች፥ ፀሐይንም አላየኋትም። 9 እሾኻችሁ ሳይታወቅ በትር ሆነ፤ ሕያዋን ሳላችሁ በመዓቱ ይውጣችኋል። 10 ጻድቅ በቀልን ባየ ጊዜ ደስ ይለዋል፤ በኀጢአተኛው ደምም እጁን ይታጠባል። 11 ሰውም፥ “በእውነት ለጻድቅ ፍሬ አለው፤ በእውነት በምድር ላይ የሚፈርድ አምላክ አለ” ይላል። |