መዝሙር 40 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር። 1 ለድሃና ለምስኪን የሚያስብ ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል። 2 እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፥ በጠላቶቹ እጅ አሳልፎ አይሰጠውም። 3 እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል። 4 እኔስ፥ “አቤቱ፥ ይቅር በለኝ፤ አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ። 5 ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ፦ “መቼ ይሞታል? ስሙስ መቼ ይሻራል?” ይላሉ። 6 ከንቱን የሚናገር ይግባና ይይ፤ ልቡ በላዩ ላይ ኀጢአትን ሰበሰበ፤ ወደ ሜዳ ይወጣል ይናገራልም፥ በእኔም ላይ ይተባበራል። 7 ጠላቶቼም ሁሉ ይጠቃቀሱብኛል፥ በእኔ ላይም ክፋትን ይመክራሉ። 8 የበደልን ነገር በእኔ አወጡ። የተኛ ሰው ከእንግዲህ ወዲህ አይነቃምን? 9 ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንሁበት፥ እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ። 10 አንተ ግን አቤቱ፥ ይቅር በለኝ፥ እመልስላቸውም ዘንድ አስነሣኝ። 11 ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ ዐወቅሁ። ጠላቶቼ በእኔ ደስ አላላቸውም። 12 እኔን ግን ስለ የዋህነቴ ተቀበልኸኝ፥ በፊትህም ለዘለዓለም አጸናኸኝ። 13 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ይሁን፥ ይሁን። |