መዝሙር 34 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ የሚበድሉኝን በድላቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። 2 ጋሻና ጦር ያዝ፥ እኔንም ለመርዳት ተነሥ። 3 ሰይፍህን ምዘዝ፥ የሚከብቡኝንም ክበባቸው ነፍሴን፦ ረዳትሽ እኔ ነኝ በላት። 4 ነፍሴን የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይጐሳቈሉም፤ ክፋትን በእኔ ላይ የሚመክሩ ይፈሩ፥ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ። 5 በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፥ የእግዚአብሔርም መልአክ ያስጨንቃቸው። 6 መንገዳቸው ዳጥና ጨለማ ትሁን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ ያሳድዳቸው። 7 በከንቱ ያጠፉኝ ዘንድ ወጥመዳቸውን ሸሽገውብኛልና፥ ነፍሴን በከንቱ አበሳጭተዋታልና። 8 ያላወቋት ወጥመድ ትምጣባቸው፥ የሸሸጓትም ወጥመድ ትያዛቸው፤ በዚህችም ወጥመድ ውስጥ ይውደቁ። 9 ነፍሴ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፥ በማዳኑም ሐሤት ታደርጋለች። 10 አጥንቶች ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ “አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? ድሃውን ከሚቀማው እጅ ድሃውንና ችግረኛውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ።” 11 የዐመፃ ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀንም በእኔ ላይ ተናገሩ። 12 ስለ በጎ ፋንታ ክፉን መለሱልኝ፥ ሰውነቴንም ልጆችን አሳጡአት። 13 እኔስ ባሠቃዩኝ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ። 14 ለወዳጆቼና ለወንድሞቼ እንደማደርግ አደረግሁ፤ እንደሚያለቅስና እንደሚተክዝ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ። 15 በእኔ ላይ ተሰበሰቡ፥ ደስም አላቸው፤ ይገርፉኝ ዘንድ ተማከሩ፥ እኔ ግን አላወቅሁም። ተሰበሩ፥ አልደነገጡምም። 16 ፈተኑኝ፥ በእኔ ላይም ዘበቱብኝ፥ ሣቁብኝም፤ ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቀጩ። 17 አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ትፈርድልኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው፥ ብቸኝነቴንም ከአንበሶች አድናት፥ 18 አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ። 19 በግፍ የሚጠሉኝ በላዬ ደስ አይበላቸው፥ በከንቱ የሚጠሉኝና በዐይናቸው የሚጠቃቀሱብኝም። 20 ለእኔስ ሰላምን ይናገሩኛልና፥ በግርፋትም ያጠፉኝ ዘንድ ይመክራሉ። 21 አፋቸውንም በእኔ ላይ አላቀቁ፤ እሰይ፥ እሰይ፥ በዐይናችን አየነው ይላሉ። 22 አቤቱ፥ አንተ እይ፥ ዝምም አትበል፤ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ። 23 አቤቱ ተነሥ፥ ፍርዴንም አድምጥ፥ አምላኬ ጌታዬም፥ በክርክሬ ጊዜ ተነሥ፥ 24 አቤቱ፥ አምላኬ፥ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፥ በእኔም ላይ ደስ አይበላቸው። 25 በልባቸውም በሰውነቴ ላይ፥ “እሰይ እሰይ፥” አይበሉ፤ “ዋጥነውም” አይበሉ። 26 በመከራዬ ደስ የሚላቸው ይፈሩ፥ ይጐስቍሉም፤ በእኔ ላይ ነገርን የሚያበዙ እፍረትንና ጕስቍልናን ይልበሱ። 27 ጽድቄን የሚወድዱአት ደስ ይበላቸው፥ ሐሤትንም ያድርጉ፤ የባሪያህን ሰላም የሚወዱ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ታላቅ ነው ይበሉ። 28 ምላሴ ጽድቅህን፥ ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል። |