መዝሙር 25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ እኔ በየዋህነቴ እኖራለሁና ፍረድልኝ፤ እንዳልደክም በእግዚአብሔር አመንሁ። 2 አቤቱ፥ ፈትነኝ መርምረኝም፤ ኵላሊቴንና ልቤን ፈትን። 3 ምሕረትህ በዐይኔ ፊት ነው፥ በማዳንህም ደስ አለኝ፤ 4 በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥሁም፥ ከዐመፀኞችም ጋር አልገባሁም። 5 የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፥ ከከዳተኞች ጋር አልቀመጥም። 6 እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ፤ አቤቱ፥ መሠዊያህን እዞራለሁ፥ 7 የምስጋናህን ቃል እሰማ ዘንድ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግር ዘንድ። 8 አቤቱ፥ የቤትህን ጌጥ የክብርህንም ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። 9 ከኀጢአተኞች ጋር ነፍሴን፥ ከደም ሰዎችም ጋር ሕይወቴን አትጣላት። 10 በእጃቸው ተንኮል አለባቸው፥ ቀኛቸውም መማለጃን ተሞልታለች። 11 እኔ ግን በየዋህነቴ እኖራለሁ፤ አቤቱ፦ አድነኝ ይቅርም በለኝ። 12 እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና፤ አቤቱ፥ በማኅበር አመሰግንሃለሁ። |