መዝሙር 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር። 1 በመከራህ ቀን እግዚአብሔር ይስማህ፤ የያዕቆብ አምላክ ስምም ይቁምልህ። 2 ከመቅደሱ ረድኤትን ይላክልህ፥ ከጽዮንም ይቀበልህ። 3 መሥዋዕትህን ያስብልህ፤ ቍርባንህንም ያለምልምልህ። 4 እግዚአብሔር እንደ ልብህ ይስጥህ ፈቃድህንም ሁሉ ይፈጽምልህ። 5 በማዳንህ ደስ ይለናል፤ በእግዚአብሔር በአምላካችን ስም ከፍ ከፍ እንላለን፤ ልመናህን ሁሉ እግዚአብሔር ይፈጽምልህ። 6 እግዚአብሔር የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ ዐወቅሁ፤ ከሰማይ መቅደሱ ይመልስለታል በቀኙ የማዳን ኀይል። 7 እነዚያ በፈረሶችና በሰረገላዎች ይታመናሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ከፍ ከፍ እንላለን። 8 እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፤ እኛ ግን ተነሣን፥ ጸንተንም ቆምን። 9 አቤቱ፥ ንጉሥን አድነው፥ በምንጠራህም ቀን ስማን። |