Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ምሳሌ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)


ከጥበብ የሚገኝ በረከት

1 ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥

2 ጆሮህ ጥበብን ትሰማለች፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ልብህንም ልጅህን ለመምከር ታቀርባለህ፥

3 ጥበብን ብትጠራት፥ ቃልህንም ለማስተዋል ብትሰጥ፥ ዕውቀትንም በታላቅ ቃል ብትፈልጋት፥

4 እርስዋንም እንደ ብር ብትፈልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤

5 የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ አምላክን ማወቅንም ታገኛለህ።

6 እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከፊቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤

7 እርሱ ቅንነትን ለሚያደርጉ ደኅንነትን ያከማቻል፤ በመንገዳቸውም ይቆምላቸዋል።

8 የጽድቅን ጎዳና ይጠብቃል፤ የሚፈሩትንም መንገድ ያጸናል።

9 የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ታውቃለህ፤ መልካም መንገድንም ሁሉ ታቃናለህ።

10 ጥበብ ወደ ልብህ በመጣች ጊዜ፥ ዕውቀትም ለነፍስህ መልካምና ክብር በሆነች ጊዜ፥

11 መልካም ምክር ትጠብቅሃለች፤ የተቀደሰች ማስተዋልም ትጋርድሃለች።

12 አንተን ከክፉ መንገድ፥ ምንም የሚታመን ነገርን ከማይናገር ሰውም ታድንህ ዘንድ፥

13 እነርሱ በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና ለሚተዉ፥

14 ክፉ በመሥራት ደስ ለሚላቸው ክፋትንም በመመለስ ሐሤትን ለሚያደርጉ፥

15 መንገዳቸው ጐጻጕጽ፥ አካሄዳቸው ጠማማ ለሆኑ ወዮላቸው!

16 ከቀናች መንገድ እንዳያርቁህ፥ እውነትንም ከማወቅ የተለየህ እንዳያደርጉህ፤ ልጄ ሆይ፥ በሕፃንነትህ ትምህርትን የምታስተው፥ ክፉ ምክር አታግኝህ፤

17 ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ጠብቅ፥ ቃሏን ከምታለዝብ ከሌላዪቱ ክፉ ሴት፥ የሕፃንንነት ባልዋን ከምትተው፥ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከምትረሳ፤ ይጠብቅህ ዘንድ፤

18 ቤቷን በሞት አጠገብ አኖረች፥ አካሄድዋንም ከኀያላን ጋር ከምድር ወደ ሲኦል አቀናች።

19 ወደ እርስዋ የሚገቡ ሁሉ አይመለሱም፥ ቀና መንገዶችንም አያገኙም፥ ሕይወት በአለው ዘመንም አይገኙም።

20 ቀና መንገዶችን ቢሄዱ ለስላሳ የጽድቅ መንገዶችን ባገኙ ነበር።

21 ደጋግ ሰዎች በምድር ላይ ይቀመጣሉ፥ ጻድቃንም በእርስዋ ይኖራሉ፤

22 የክፉዎች መንገዶች ከምድር ላይ ይጠፋሉ፤ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይሰደዳሉ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች