ፊልጵስዩስ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከትዕቢት ስለ መራቅ 1 አሁንም በክርስቶስ ደስታ፥ ወይም በፍቅር የልብ መጽናናት፥ ወይም የመንፈስ አንድነት፥ ወይም ማዘንና መራራትም በእናንተ ዘንድ ካለ፦ 2 እርሱን ብቻ ታስቡ ዘንድ፥ አንድ ልብና አንድ ምክርም ሆናችሁ፥ በፍቅር ትኖሩ ዘንድ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። 3 በክርክርና ከንቱ ውዳሴን በመውደድ አትሥሩ፤ ትሕትናን በያዘ ልቡና ከራሳችሁ ይልቅ ባልንጀራችሁን አክብሩ እንጂ አትታበዩ። 4 ለባልንጀራችሁም እንጂ ለየራሳችሁ ብቻ አታስቡ። 5 ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንደ አደረገልን ይህን አስቡ። 6 ይኸውም የእግዚአብሔር መልኩ ነው፤ ቀምቶ እግዚአብሔር የሆነ አይደለም። 7 ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ፥ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ። 8 እንደ ሰውም ሆኖ ራሱን አዋረደ፤ ለሞት እስከ መድረስም ታዘዘ፤ ሞቱም በመስቀል የሆነው ነው። 9 ስለዚህም እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስምንም ሰጠው። 10 ይህም በሰማይና በምድር በቀላያትና ከምድር በታች ያለ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰግድ ዘንድ ነው። 11 አንደበትም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር ጌታ እንደ ሆነ ያምን ዘንድ ነው። 12 አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ ዘወትር እንደምትሰሙኝ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፥ ሳልኖርም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ሆናችሁ ለድኅነታችሁ ሥሩ። 13 ለሚወደው ሥራ የሚረዳችሁ እርሱ እግዚአብሔር ይቅርታውን ይፈጽምላችሁ። 14 የምትሠሩትን ሁሉ ያለ ማንጐራጐርና ያለ መጠራጠር በፍቅርና በስምምነት ሥሩ። 15 እንደ እግዚአብሔር ልጆች ንጹሓንና የዋሃን ትሆኑ ዘንድ፥ በማያምኑና በጠማሞች ልጆች መካከል ነውር ሳይኖርባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፤ 16 የሕይወትን ቃል እያስተማራችሁ፤ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን እኔ እንድመካ፤ የሮጥሁ በከንቱ አይደለምና፤ የደከምሁም በከንቱ አይደለምና። 17 ስለ ሃይማኖታችሁም የአምልኮ መሥዋዕትን እሠዋለሁ። እነሆም እኔ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ 18 እናንተም በእኔ ደስ ይበላችሁ። ከእኔም ጋር ሐሤት አድርጉ። ስለ ጢሞቴዎስና አፍሮዲጡ መላክ 19 ጢሞቴዎስን እንድልክላችሁ፥ እኔም ዜናችሁን ሰምቼ ደስ እንዲለኝ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋ አደርጋለሁ። 20 ከእርሱ በቀር፥ እንደ እኔ ሆኖ በማስተዋል ግዳጃችሁን የሚፈጽም የለኝምና። 21 የክርስቶስን ያይደለ፥ ሁሉም የራሱን ጉዳይ ያስባልና። 22 ልጅ አባቱን እንደሚያገለግል፥ በወንጌል ትምህርት እንደ አገለገለኝ፥ የዚህን ሰው ጠባዩን ታውቃላችሁ። 23 እንግዲህ እንዴት እንደ አለሁ በዐወቅሁ ጊዜ፥ እርሱን በቶሎ እንደምልከው ተስፋ አደርጋለሁ፤ 24 እኔም ፈጥኜ እንደምመጣ በጌታችን አምናለሁ። 25 አሁንም አብሮኝ የሚሠራውን ወንድማችንን አፍሮዲጡን ወደ እናንተ ልልከው አስቤአለሁ፤ እርሱም የክርስቶስ ሎሌ ነው፤ ለእናንተም መምህራችሁ ነው፤ ለእኔም ለችግሬ ጊዜ መልእክተኛዬ ነው። 26 እንደ ታመመ፥ ለሞትም እንደ ደረሰ መስማታችሁን ዐውቆ ሊያያችሁ ይሻልና። 27 ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፤ በኀዘን ላይ ኀዘን እንዳይጨመርብኝ ለእኔም እንጂ ለእሱ ብቻ አይደለም። 28 እንድታዩትና ደስ እንዲላችሁ፥ እኔም እንዳላዝን በቶሎ እልከዋለሁ። 29 እንግዲህ በጌታችን በፍጹም ደስታ ተቀበሉት፤ እንደዚህ ያሉትንም ሁሉ አክብሩአቸው። 30 የእግዚአብሔርን ሥራ ስለ መሥራት እስከ ሞት ደርሶአልና፥ ከእኔ መልእክትም እናንተ ያጐደላችሁትን ይፈጽም ዘንድ ሰውነቱን አሳልፎ ሰጥቶአልና። |