ዘኍል 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የአሮን በትር እንደ ለመለመች 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው፤ ከእነርሱም ከእያንዳንዱ ከየአባቶቻቸው ቤት አንድ አንድ በትር፥ ከአለቆቻቸውም ከየአባቶቻቸው ቤት ዐሥራ ሁለት በትሮች ውሰድ፤ የእያንዳንዱንም ስም በየበትሩ ላይ ጻፍ። 3 ለየአባቶቻቸው ቤት ወገን አንድ በትር ይሰጣሉና በሌዊ በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍ። 4 እኔ ለእናንተ በምገለጥበት በዚያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት አኑራቸው። 5 እንዲህም ይሆናል፤ የመረጥሁት ሰው በትር ትለመልማለች፤ በእናንተም ላይ የሚያጕረመርሙባችሁ የእስራኤልን ልጆች ማጕረምረም ከእኔ ዘንድ አጠፋለሁ።” 6 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው፤ አለቆቻቸውም ሁሉ አንድ አንድ በትር ሰጡት፤ ለአንድ አለቃ አንድ በትር፥ በየአባቶቻቸው ቤት ዐሥራ ሁለት በትሮች፤ የአሮንም በትር በበትሮቻቸው መካከል ነበረች። 7 ሙሴም በትሮቹን በእግዚአብሔር ፊት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ አኖራቸው። 8 እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴና አሮን ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገቡ፤ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፤ ለመለመችም፤ አበባም አወጣች፤ የበሰለ ለውዝም አፈራች። 9 ሙሴም በትሮቹን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፤ እያንዳንዱም በትሩን ወሰደ። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ነገረው፥ “ማጕረምረማቸው ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ፥ እነርሱም እንዳይሞቱ ለማይሰሙ ልጆች ምልክት ሆና ትጠበቅ ዘንድ የአሮንን በትር በምስክሩ ፊት አኑር።” 11 ሙሴና አሮንም፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ። 12 የእስራኤልም ልጆች ሙሴን አሉት፥ “እነሆ፥ እንሞታለን፤ እንጠፋለን፤ ሁላችንም እናልቃለን። 13 የእግዚአብሔርን ድንኳን የሚነካ ሁሉ ይሞታል። በውኑ ሁላችን ፈጽመን እንሞታለን?” |