ዘኍል 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)መጀመሪያው የእስራኤል ሕዝብ ቈጠራ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ፥ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን፥ ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ድምር፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ በየስማቸው ቍጥር፥ ወንዱን ሁሉ እያንዳንዱን ቍጠሩ። 3 ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጡትን ሁሉ፥ አንተና አሮን በየሠራዊቶቻቸው ቍጠሩአቸው። 4 እንደ እየአባቶቻቸው ቤት ከየነገዱ አለቆች አንድ አንድ ሰው ከእናንተ ጋር ይሁን። 5 ከእናንተም ጋር የሚቆሙት ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ከሮቤል የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር፥ 6 ከስምዖን የሴሩሳዴ ልጅ ሰላምያል፥ 7 ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፥ 8 ከይሳኮር የሰገር ልጅ ናትናኤል፥ 9 ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፥ 10 ከዮሴፍ ልጆች ከኤፍሬም የኤምዩድ ልጅ ኤሊሳማ፥ ከምናሴ የፈዳሱር ልጅ ገማልያል፥ 11 ከብንያም የጋዲዮን ልጅ አቢዳን፥ 12 ከዳን የአሚሳዲ ልጅ አክያዚር፥ 13 ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋጋኤል፥ 14 ከጋድ የራጉኤል ልጅ ኤልሳፍ፥ 15 ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አኪሬ። 16 ከማኅበሩ የተመረጡ የእስራኤል ነገድ አለቆችና መሳፍንት በየወገናቸው እነዚህ ናቸው።” 17 ሙሴና አሮንም እነዚህን በየስማቸው የተጠሩትን ሰዎች ወሰዱአቸው፤ 18 በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበሩን ሁሉ ሰበሰቡአቸው፤ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ወንድ ሁሉ በየራሱ፥ በየወገኑም፥ በየአባቶቻቸውም ቤቶች፥ በየስማቸው ቍጥር ትውልዳቸውን ተናገሩ። 19 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በሲና ምድረ በዳ ቈጠሩአቸው። 20 የእስራኤል በኵር የሮቤል ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 21 ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩት አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 22 የስምዖን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 23 ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። 24 የይሁዳ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 25 ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 26 የይሳኮር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 27 ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 28 የዛብሎን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 29 ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 30 ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 31 ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 32 የምናሴ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች- እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 33 ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 34 የብንያም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 35 ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 36 የጋድ ልጆች በየትውልዳቸው- በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 37 ከጋድ ነገድ የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ። 38 የዳን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደእየ ስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 39 ከዳን ነገድ የተቈጠሩት ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 40 የአሴር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 41 ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 42 የንፍታሌም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 43 ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 44 ሙሴና አሮን ዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል አለቆች እነርሱን የቈጠሩበት ቍጥር ይህ ነው። 45 ከእያንዳንዱ ነገድ ከየአባቶቻቸው ቤቶች አንድ አንድ አለቃ ነበረ። ከእስራኤልም ልጆች የተቈጠሩት ሁሉ፥ በየሠራዊታቸው፥ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 46 የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ። 47 ሌዋውያን ግን በየአባቶቻቸው ነገድ ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም። 48 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 49 “የሌዊን ነገድ እንዳትቈጥራቸው፥ ቍጥራቸውንም ከእስራኤል ልጆች ጋር እንዳትቀበል ዕወቅ፤ 50 ነገር ግን በምስክሩ ድንኳንና በዕቃዎችዋ ሁሉ፥ በውስጥዋም ባለው ነገር ሁሉ ላይ ሌዋውያንን አቁማቸው። ድንኳንዋንና ዕቃዎችዋን ሁሉ ይሸከሙ፤ ያገልግሉአትም፤ በድንኳንዋም ዙሪያ ይስፈሩ። 51 ድንኳንዋም ስትነሣ ሌዋውያን ይንቀሉአት፤ ድንኳንዋም ስታርፍ ሌዋውያን ይትከሉአት፤ ሌላ ሰው ግን ለመንካት ቢቀርብ ይገደል። 52 የእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ሰው በየሰፈሩ፥ እያንዳንዱም ሰው በየአለቃው፥ በየጭፍራውም ይሰፍራሉ። 53 ነገር ግን በእስራኤል ልጆች ላይ ዕዳ እንዳይሆንባቸው ሌዋውያን በምስክሩ ድንኳን ዙሪያ ፊት ለፊት ይስፈሩ፤ ሌዋውያን የምስክሩን ድንኳን ሕግ ይጠብቁ።” 54 የእስራኤል ልጆችም እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን ያዘዛቸውን ሁሉ አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ። |