ሉቃስ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ስምዖንና ስለ ዘብዴዎስ ልጆች መጠራት 1 ብዙ ሰዎችም በእርሱ ዘንድ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ይሰሙ ነበር፤ እርሱ ግን በጌንሴሬጥ ባሕር ወደብ ቁሞ ነበር። 2 በባሕሩም ዳር ሁለት ታንኳዎች ቁመው አየ፤ ከእነርሱም ውስጥ ዓሣ አጥማጆች መረባቸውን ሊያጥቡ ወረዱ። 3 ከሁለቱ ታንኳዎች ወደ አንዲቱ ታንኳ ወጣ፤ ይቺውም ታንኳ የስምዖን ነበረች፤ “ከምድር ጥቂት እልፍ አድርጋት” አለው፤ በታንኳዪቱም ውስጥ ተቀምጦ ሕዝቡን አስተማራቸው። 4 ትምህርቱንም ከፈጸመ በኋላ ስምዖንን፥ “ወደ ጥልቁ ባሕር ፈቀቅ በል፤ መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ” አለው። 5 ስምዖንም መልሶ፥ “መምህር፥ ሌሊቱን ሁሉ ደክመናል፤ የያዝነውም የለም፤ ነገር ግን ስለ አዘዝኸን መረቦቻችንን እንጥላለን” አለው። 6 እንዳዘዛቸውም ባደረጉ ጊዜ፥ መረቡ እስኪቀደድ ድረስ ብዙ ዓሣ ተያዘ። 7 መጥተውም ይረዱአቸው ዘንድ በሌላ ታንኳ የነበሩትን ባልንጀሮቻቸውን ጠሩ፤ መጥተውም እስኪጠልቁ ድረስ ሁለቱን ታንኳዎች ሞሉ። 8 ስምዖን ጴጥሮስም ይህን አይቶ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር በታች ሰገደና፥ “እኔ ኀጢአተኛ ሰው ነኝና አቤቱ ከእኔ ፈቀቅ በል፤” አለው። 9 እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ስለ ተያዘው ዓሣ ተደንቀው ነበርና። 10 እንዲሁም የስምዖን ባልንጀራዎች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ተደነቁ፤ ጌታችን ኢየሱስም ስምዖንን፥ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህስ ሰውን ታጠምዳለህ” አለው። 11 ታንኳዎቻቸውንም ወደ ምድር አወጡና ሁሉን ትተው ተከተሉት። ለምጻሙን ስለ ማዳኑ 12 በአንዲት ከተማ ሳለም ሁለመናው ለምጻም የሆነ ሰው መጣ፤ ጌታችን ኢየሱስንም ባየው ጊዜ በፊቱ ወድቆ ሰገደለትና፥ “አቤቱ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” እያለ ማለደው። 13 እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፥ “እወዳለሁ ንጻ” አለው፤ ያንጊዜም ለምጹ ለቀቀው። 14 ለማንም እንዳይናገር ከለከለው፤ “ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አስመርምር፤ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ ነጻህ ሙሴ እንደ አዘዘ መባህን አቅርብ” ብሎ አዘዘው። 15 ዜናውም በሁሉ ተሰማ፤ ብዙ ሰዎችም ትምህርቱን ሊሰሙ፥ ከደዌአቸውም ሊፈወሱ ይመጡ ነበር። 16 እርሱ ግን ወደ ምድረ በዳ እየወጣ ይጸልይ ነበር። ስለ መጻጒዕ መፈወስ 17 ከዚህም በኋላ፥ ከዕለታት በአንድ ቀን ሲያስተምራቸው እንዲህ ሆነ፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች፥ ከኢየሩሳሌምም የመጡ ፈሪሳውያንና የኦሪት መምህራን ነበሩ፤ እርሱም ይፈውስ ዘንድ የእግዚአብሔር ኀይል ነበረ። 18 እነሆ፥ ሰዎች በአልጋ ተሸክመው ሽባ የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እንዲፈውሰውም ወደ እርሱ ሊያስገቡት ወደዱ። 19 ሰውም ተጨናንቆ ነበርና የሚያስገቡበት አጡ፤ ወደ ሰገነትም ወጡ፤ ጣራውንም አፍርሰው ወደ ቤቱ ውስጥ በጌታችን በኢየሱስ ፊት ከነአልጋው አወረዱት። 20 እምነታቸውንም አይቶ ያን ሰው፥ “ኀጢአትህ ተሰረየልህ” አለው። 21 ጻፎችና ፈሪሳውያንም፥ “የሚሳደብ ይህ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአትን ማስተስረይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር። 22 ጌታችን ኢየሱስም የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው፥ “በልባችሁ ምን ታስባላችሁ? 23 ኀጢአትህ ተሰረየልህ ከማለትና ተነሥተህ ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? 24 ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤ ያን ሽባ፦ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ ብዬሃለሁ” አለው። 25 ያንጊዜም ተነሥቶ ተኝቶበት የነበረውን አልጋ በፊታቸው ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። 26 ሁሉም ተደነቁ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፤ እጅግም እየፈሩ፥ “ዛሬ ድንቅ ነገር አየን” አሉ። ስለ ቀራጩ ሌዊ መጠራት 27 ከዚህም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ ሰው በቀረጥ መቀበያው ቦታ ተቀምጦ አየና፥ “ተከተለኝ” አለው። 28 ሁሉንም ተወና ተነሥቶ ተከተለው። 29 ሌዊም በቤቱ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፤ ብዙ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ ከእርሱም ጋር ለምሳ ተቀምጠው የነበሩ ቀራጮችና ኀጢአተኞች፥ ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ። 30 ጻፎችና ፈሪሳውያንም፥ “ከቀራጮችና ከኃጥኣን ጋር ለምን ትበላላችሁ? ትጠጡማላችሁ?” ብለው በደቀ መዛሙርቱ ላይ አንጐራጐሩ። 31 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ባለ መድኀኒትን በሽተኞች እንጂ ጤነኞች አይሹትም። 32 ኃጥኣንን ወደ ንስሓ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም።” ስለ ጾም 33 እነርሱም፥ “የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለምን በብዙ ይጾማሉ? ጸሎትስ ስለምን ያደርጋሉ? የፈሪሳውያን ወገኖች የሆኑትም ስለምን እንዲሁ ያደርጋሉ? ያንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን ይበላሉ? ይጠጣሉም?” አሉት። 34 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ መጾም አይችሉም። 35 ነገር ግን ሙሽራውን ከእነርሱ የሚወስዱበት ቀን ይመጣል፤ ያንጊዜም ይጾማሉ።” 36 በምሳሌም እንዲህ አላቸው፥ “በአሮጌ ልብስ ቀዳዳ ላይ የአዲስ ልብስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ያለዚያ ግን አዲሱ አሮጌውን ይቀድደዋል፤ አዲሱ እራፊም ከአሮጌው ጋር አይስማማም። 37 አዲስ ጠጅንም በአሮጌ ረዋት የሚያደርግ የለም፤ ያለዚያ ግን ይቀድደዋል፤ ወይኑም ይፈስሳል፤ ረዋቱም ይቀደዳል። 38 ነገር ግን አዲሱን ጠጅ በአዲስ ረዋት ያደርጉታል፤ እርስ በርሳቸውም ይጠባበቃሉ። 39 የከረመውን የወይን ጠጅ ሊጠጣ ወድዶ አዲሱን የሚሻ የለም፤ የከረመው ይሻላል ይላልና።” |