ሉቃስ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ስብከት 1 ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በዐሥራ አምስት ዓመት ጴንጤናዊው ጲላጦስ የይሁዳ ገዢ ሆኖ ሳለ፥ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዢ ሳለ፥ ወንድሙ ፊልጶስም የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ አራተኛ ክፍል ገዢ፥ ሊሳንዮስም የሳብላኒስ አራተኛ ክፍል ገዢ ሆነው ሳሉ፥ 2 ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት በነበሩበት ወራት የእግዚአብሔር ቃል በምድረ በዳ ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ መጣ። 3 ስለ ኀጢአት ስርየት ለንስሓ የሚያበቃ ጥምቀትን እየሰበከ በዮርዳኖስ አውራጃ ዞረ። 4 በምድረ በዳ የሚጮኽ የአዋጅ ነጋሪ ድምፅ በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ ቃል እንደ ተጻፈ፥ እንዲህ ሲል፥ “የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ። 5 ጐድጓዳው ሁሉ ይምላ፤ ተራራውም፥ ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ሰንከልካላውም የቀና ጥርጊያ ይሁን፤ ወጣ ገባው መንገድም ይስተካከል። 6 ሰውም ሁሉ የእግዚአብሔርን ትድግና ይይ።” 7 ዮሐንስም ሊያጠምቃቸው የመጡትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፥ “እናንት የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው መቅሠፍት ታመልጡ ዘንድ ማን ነገራችሁ? 8 እንግዲህ ለንስሓ የሚያበቃችሁን ሥራ ሥሩ፤ አብርሃም አባታችን አለን በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆችን ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁ። 9 እነሆ፥ ምሳር በዛፎች ላይ ተቃጥቶአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራውንም ዛፍ ሁሉ ይቈርጡታል፤ ወደ እሳትም ይጥሉታል።” 10 ሕዝቡም፥ “እንግዲህ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። 11 እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌለው ይስጥ፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ያድርግ።” 12 ቀራጮችም ሊያጠምቃቸው መጡና፥ “መምህር፥ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት። 13 እርሱም፥ “ከታዘዛችሁት አትርፋችሁ አትውሰዱ” አላቸው። 14 ጭፍሮችም መጥተው፥ “እኛሳ ምን እናድርግ?” አሉት፤ “በደመወዛችሁ ኑሩ እንጂ በማንም ግፍ አትሥሩ፤ ማንንም አትቀሙ፤ አትበድሉም” አላቸው። 15 ሕዝቡም ሁሉ በልባቸው ዐሰቡ፤ ዮሐንስም ክርስቶስ እንደ ሆነ መሰላቸው። 16 ዮሐንስም መልሶ ሁሉንም እንዲህ አላቸው፥ “እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ግን የሚበልጠኝ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ልፈታለት የማይገባኝ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ፥ በእሳትም ያጠምቃችኋል። 17 መንሹ በእጁ ነው፤ የዐውድማውንም እህል ያጠራል፤ ስንዴውንም በጎተራው ይሰበስባል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥላል።” 18 ሕዝቡንም ይገስጻቸውና በሌላም በብዙ ነገር የምሥራች ይነግራቸው ነበር። ስለ ዮሐንስ መጥምቅ መታሰር 19 ዮሐንስም የአራተኛው ክፍል ገዢ ሄሮድስን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ስለማግባቱና ሄሮድስ ያደርገው ስለነበረው ክፉ ነገር ሁሉ ይገሥጸው ነበር። 20 ደግሞም ከዚህ ሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐንስን ተቀየመውና በግዞት ቤት አስገባው። ጌታችን ስለ መጠመቁ 21 ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ጌታችን ኢየሱስም ተጠመቀ፤ ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ። 22 መንፈስ ቅዱስም የርግብ መልክ ባለው አካል አምሳል በእርሱ ላይ ወረደ፤ ከሰማይም፥ “የምወድህ፥ በአንተም ደስ የሚለኝ ልጄ አንተ ነህ” የሚል ቃል መጣ። ሉቃ. 9፥35። ስለ ጌታችን ትውልድ መጽሐፍ 23 የጌታችን ኢየሱስም ዕድሜዉ ሠላሳ ዓመት ያህል ነበር፤ የዮሴፍ ልጅም ይመስላቸው ነበር። 24 የኤሊ ልጅ፥ የማቲ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የሜልኪ ልጅ፥ የዮና ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ 25 የማታትዩ ልጅ፥ የአሞጽ ልጅ፥ የናሆም ልጅ፥ የኤስሎም ልጅ፥ የናጌ ልጅ፥ 26 የማአት ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ፥ የሴሜይ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮዳ ልጅ፥ 27 የዮናን ልጅ፥ የሬስ ልጅ፥ የዘሩባቤል ልጅ፥ የሰላትያል ልጅ፥ የኔሪ ልጅ፥ 28 የሜልኪ ልጅ፥ የሐዲ ልጅ፥ የዮሳ ልጅ፥ የቆሳም ልጅ፥ የኤልሞዳም ልጅ፥ የኤር ልጅ፥ 29 የዮሴዕ ልጅ፥ የአልዓዛር ልጅ፥ የዮራም ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ 30 የስምዖን ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የኤልያቄም ልጅ፥ 31 የሜልያ ልጅ፥ የማይናን ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የናታን ልጅ፥ የዳዊት ልጅ፥ 32 የዕሤይ ልጅ፥ የኢዮቤድ ልጅ፥ የቦዔዝ ልጅ፥ የሰልሞን ልጅ፥ የነዓሶን ልጅ፥ 33 የአሚናዳብ ልጅ፥ የአራም ልጅ፥ የኦርኒ ልጅ፥ የኤስሮም ልጅ፥ የፋሬስ ልጅ፤ የይሁዳ ልጅ፥ 34 የያዕቆብ ልጅ፥ የይስሐቅ ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የታራ ልጅ፥ የናኮር ልጅ፥ 35 የሴሩኅ ልጅ፥ የራግው ልጅ፥ የፋሌቅ ልጅ፥ የኤቦር ልጅ፥ የሳላ ልጅ፥ 36 የቃይናን ልጅ፥ የአርፋክስድ ልጅ፥ የሴም ልጅ፥ የኖኅ ልጅ፥ የላሜሕ ልጅ፥ 37 የማቱሳላ ልጅ፥ የሄኖክ ልጅ፥ የያሬድ ልጅ፥ የመላልኤል ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥ 38 የሄኖስ ልጅ፥ የሴት ልጅ፥ የአዳም ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ። |