ዘሌዋውያን 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከሰውነቱ ፈሳሽ ስለሚፈስሰው ሰው የመንጻት ሕግ 1 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፥ 2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው፦ ከሰውነቱ ዘር የሚፈስሰው ሰው ቢኖር ስለሚፈስሰው ነገር ርኩስ ነው። 3 ከሰውነቱ ፈሳሽ ለሚፈስሰው ሰው የርኵሰቱ ሕግ ይህ ነው፤ ፈሳሽ የሚፈስሰው ሰው ፈሳሹ እየፈሰሰው በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ፈሳሹ ያረክሰዋል። 4 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው፤ የሚቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 5 መኝታውንም የሚነካ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ በውኃም ሰውነቱን ይታጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 6 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በተቀመጠበት ነገር ላይ የሚቀመጥበት ሰው ልብሱን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 7 ፈሳሽ ነገር ያለበትን የሰውን ሥጋ የሚነካ ልብሱን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 8 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው በንጹሕ ሰው ላይ ቢተፋ ልብሱን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 9 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ነው። 10 ከበታቹም ያለውን ነገር የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ እነዚህንም ነገሮች የሚያነሣ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 11 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው እጁን በውኃ ሳይታጠብ የሚነካው ሁሉ ልብሶቹን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 12 ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው የሚነካውን የሸክላ ዕቃ ይስበሩት፤ የዕንጨቱንም ዕቃ ሁሉ በውኃ ይጠቡት፤ ንጹሕም ይሆናል። 13 “ፈሳሽ ነገር ያለበት ሰው ከፈሳሹ ነገር ሲነጻ ስለ መንጻቱ ሰባት ቀን ይቈጥራል፤ ልብሶቹንም ያጥባል፤ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠባል፤ ንጹሕም ይሆናል። 14 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዞ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣል፤ ለካህኑም ይሰጠዋል። 15 ካህኑም አንዲቱን ለኀጢአት መሥዋዕት፥ አንዲቱንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ፈሳሹ ነገር ሁሉ ያስተሰርይለታል። 16 “ማንም ሰው ዘር ከእርሱ ቢወጣ፥ ገላውን ሁሉ በውኃ ይታጠባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 17 ዘር የነካው ልብስ ሁሉ፥ ቍርበትም ሁሉ በውኃ ይታጠባል፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 18 ሴት ፈሳሽ ከአለበት ወንድ ጋር ብትገናኝ ሁለቱም በውኃ ይታጠባሉ፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩሳን ናቸው። 19 “ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት፥ በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በግዳጅዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው። 20 በግዳጅም ሳለች የምትተኛበት ነገር ሁሉ ርኩስ ነው፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 21 መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሶቹን ያጥባል፤ በውኃም ሰውነቱን ይታጠባል፤ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ነው። 22 የምትቀመጥበትንም ነገር ሁሉ የሚነካ ሁሉ ልብሶቹን ያጥባል፤ በውኃም ሰውነቱን ይታጠባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 23 በመኝታዋም ላይ ወይም በምትቀመጥበት ነገር ላይ ቢሆን ሲነካው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው። 24 ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ፥ ግዳጅዋም ቢነካው፥ ሰባት ቀን ርኩስ ነው፤ የሚተኛበትም መኝታ ሁሉ ርኩስ ነው። 25 “ሴትም ከግዳጅዋ ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፥ ወይም ደምዋ ከግዳጅዋ ወራት በኋላ ቢፈስስ፥ በግዳጅዋ ወራት እንደ ሆነች እንዲሁ በፈሳሽዋ ርኩስነት ወራት ትሆናለች፤ ርኵስት ናት። 26 ደምዋም በሚፈስስበት ወራት ሁሉ የምትተኛበት መኝታ ሁሉ በግዳጅዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ያለ ይሆንባታል፤ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ እንደ ግዳጅዋ ርኩስነት ርኩስ ነው። 27 እነዚህንም ነገሮች የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ልብሱንም ያጥባል፤ በውኃም ይታጠባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 28 ከፈሳሽዋም ብትነጻ ሰባት ቀን ትቈጥራለች፤ ከዚያም በኋላ ንጽሕት ትሆናለች። 29 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዛ ወደ ካህኑ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ታመጣቸዋለች። 30 ካህኑም አንዲቱን ለኀጢአት መሥዋዕት፥ አንዲቱንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ ርኩስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል። 31 “እንዲሁም በእነርሱ መካከል ያለችውን ድንኳኔን ባረከሱ ጊዜ፥ በርኩስነታቸው እንዳይሞቱ የእስራኤልን ልጆች ከርኩስነታቸው አንጹአቸው። 32 “ፈሳሽ ነገር ላለበት ሰው፥ ይረክስም ዘንድ ዘሩ ለሚወጣበት ሰው፥ 33 በግዳጅዋም ደም ለሚፈስሳት፥ ፈሳሽም ነገር ላለባቸው ለወንድም ለሴትም፥ ከረከሰችም ሴት ጋር ለሚተኛ ሰው ሕጉ ይህ ነው።” |