ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በሠላሳ ሦስተኛውም ኢዮቤልዩ መጀመሪያ እንዲህ ሆነ፤ ለካምና ለሴም ለያፌትም ርስት ልትሆናቸው ከአንደኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ወደ እነርሱ ከተላክን ከእኛ አንዱ ባለበት ምድርን ሦስት አድርገው ከፈሉአት፤ ልጆቹንም ጠራ፤ እነርሱና ልጆቻቸውም ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ሦስቱ ልጆቹም የሚይዙትን ምድር በዕጣ ከፈለ። 2 እጃቸውንም ዘርግተው ከአባታቸው ከኖኅ እጅ መጽሐፉን ተቀበሉ። ርስት አድርጎ የሚይዘው የሴም ዕጣም ለልጆቹና ለልጅ ልጆቹ ለዘለዓለም በመጽሐፍ የምድር መካከል ወጣ። ከአርበኞች ተራራ መካከል ከውኃውም መውጫ ጀምሮ እስከ ጢና ወንዝ ድረስ ወጣ። 3 ክፍሉም በዚህ ወንዝ መካከል ወዳለ ወደ ምዕራብ ይደርሳል፤ ይህም ወንዝ ከእርስዋ እስከሚወጣበት እስከ ጥልቁ ውኃ እስኪቀርብ ድረስ ወደዚያ ይሄዳል። ውኃውም ወደ ሚኦት ባሕር ይፈስሳል፤ ይህም ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሄዳል፤ በደቡብም በኩል ያለው ሀገር ሁሉ ለያፌት ደረሰ፤ በሰሜን በኩል ያለውም ሀገር ሁሉ ለሴም ደረሰ። 4 ወደ ኮራሶ እስኪቀርብ ድረስ ይሄዳል። ይኸውም ወደ ሰሜን የሚመለከት ሕፅነ ልሳን ነው። ክፍሉም ወደ ታላቁ ባሕር ይደርሳል። ይህች ባሕር ልሳነ ባሕረ ግብፅ ትባላለችና ወደ ሰሜን ወደምታሳይ ወደ ልሳን መግቢያ እስኪቀርብ ድረስ አቅንቶ ይሄዳል። 5 ከዚያም ወደ ሰሜን ታዘነብላለች፤ ወደ ታላቁ ባሕር መግቢያ ወደ ውኃውም ዳርቻ ትደርሳለች፤ ወደ አፍራም ግራ ትደርሳለች፤ ግዮን ወደሚባል ፈሳሽ ውኃም እስክትቀርብ ድረስ ትደርሳለች፤ ወደ ግዮንም ውኃ ቀርባ ወደዚህ ፈሳሽ ዳርቻ ትደርሳለች። 6 ወደ ኤደን ገነት ወደ ሰሜንም ቀኝ እስክትቀርብ ድረስ ወደ ምሥራቅ ትሄዳለች፤ ከኤዶም ምድር ሁሉ ምሥራቅ፥ ከሀገሩም ሁሉ ምሥራቅ ወደ ምሥራቅ ይመለሳል። ስሙ ራፋ ወደሚባል ተራራ ምሥራቅ እስኪቀርብ ድረስ ይመጣል፤ ወደ ጢና ወንዝ መውጫ ዳርቻም ይወርዳል። 7 ይህችም ክፍል ለዘለዓለም ሊይዙአት ለሴምና ለልጆቹ፥ ለልጅ ልጆቹም እስከ ዘለዓለም ድረስ በዕጣ ወጣች። 8 ኖኅም ይህ ክፍል የሴምና የልጆቹ ዕጣ ነውና ደስ አለው። “የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፥ እግዚአብሔርም በሴም ማደሪያ ይደር” ብሎአልና በአፉ በትንቢት የተናገረውን ነገር ሁሉ ዐሰበ። የኤዶም ገነት ከከበሩ የከበረች፥ የእግዚአብሔርም ማደሪያ እንደ ሆነች ዐውቆአልና። ደብረ ሲና በምድረ በዳ መካከል ናት፥ ደብረ ጽዮንም በምድር ዕንብርት መካከል ናት፥ እነዚህ ሦስቱ ሁሉ አንዱ በአንዱ አንጻር ለቅድስና ተፈጠሩ። 9 በአፉ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲናገር ያደረገውን የአማልክት አምላክ እግዚአብሔርን እስከ ዘለዓለም ድረስ አመሰገነው፤ የተባረከ ክፍልና በረከት ለሴምና ለልጆቹ፥ ለልጅ ልጆቹም እስከ ዘለዓለም ድረስ እንደ ደረሳቸው ዐወቀ። 10 የኤዶም ምድር ሁሉ፥ የኤርትራ ባሕር ዳርም ሁሉ፥ የምሥራቅ ምድር ሁሉ በኤርትራና በተራሮቹ በኩል ያለው ሕንድ፥ የባሳን ሀገር ሁሉና የሊባኖስም ሀገር ሁሉ፥ የካፍቱር ደሴቶችና የሳኔር ተራራ ሁሉ፥ አማናና የደቡባዊው አሱር ተራራ፥ የኤላም ሀገር ሁሉ፥ አሱርና ባቢል፥ ሱሳንም ማእዳይና የአራራት ሀገር ሁሉ፥ በደቡብ በኩል ከአለው ከአሱር ተራራ ማዶ የባሕሩ ወደብ እንደ ደረሱት ዐወቀ። የተባረከችና ሰፊ የሆነች፥ በውስጥዋም ያለ ሁሉ እጅግ ያማረ ምድር፤ 11 ሁለተኛውም ዕጣ ወደ ግዮን ማዶ በገነት ቀኝ በሰሜን በኩል ለካም ወጣ፥ ወደ ሰሜንም ይደርሳል። ዋዕይ ወደ ጸናበት ተራራም ሁሉ ይደርሳል፤ በአጤል አንጻር ወዳለ ወደ ምዕራብ ይደርሳል። ወደ ማዕከክ ባሕር እስኪቀርብ ድረስም ወደ ምዕራብ ይደርሳል። ይህችውም የሚጠፋው ሁሉ ወደ እርስዋ የሚወርድባት ሀገር ናት። ወደ ደቡብ ወደ ጋዴት ዳርቻ ይወጣል። ወደ ግዮን ወንዝም እስኪቀርብ ድረስ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወደ ታላቁ ባሕር ይመጣል። 12 ግዮን የተባለው ወንዝም በኤዶም ገነት ቀኝ እስኪቀርብ ድረስ ይሄዳል። ለዘለዓለም ለሚይዛት ለካምና ለልጆቹ፥ ለወገናቸውም እስከ ዘለዓለም ድረስ በዕጣ የወጣች ሀገር ይህች ናት። 13 ለያፌትም ሦስተኛው ዕጣ ወጣ። ጢና ወደሚባል ወንዝ ማዶ ወደ ፈሳሾች መውጫ ወደ ደቡብ ወጣ። ወደ ደቡብ ምሥራቅ፥ ወደ ጎግ አውራጃም ሁሉና ወደ ምሥራቃቸው ሁሉ ይደርሳል፥ ከደቡብም ወደ ደቡብ ይደርሳል። ወደ ቄልጥ ተራራና ወደ ደቡብ፥ ወደ ማሉቅም ባሕር ይደርሳል። እስከ ባሕሩ መውጫ ዳርቻ ድረስ ወደ ጋዴት ምሥራቅም ይመጣል። ወደ ፋራ መግቢያም እስኪቀርብ ድረስ ይሄዳል። ወደ ምሥራቅ ወደ ማኡታ ባሕር ወደሚሄደው ወደ አፌራግም ይመለሳል፤ ወደ ውኃው ዳርቻ ወደ ራፋ ተራራ እስኪቀርብም ድረስ ጢና ወደተባለው ወንዝ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ይሄዳል። ደቡብንም ይዞራል። 14 ለዘለዓለሙ በርስትነት ዕጣ የሚይዛት፥ ለያፌትና ለልጆቹ፥ ለወገኖቹም የወጣችለት ምድር ይህች ናት። ታላላቅ ደሴቶችዋም አምስት ናቸው። በደቡብ በኩል ያለችውም ሀገር ሰፊ ናት። ነገር ግን የያፌት ሀገር ቀዝቃዛ ናት፤ የካምም ሀገር በረሃ ናት፤ የሴም ሀገር ግን ከውርጭና ከዋዕይ ጋር የተቀላቀለች ናትና ቆላም ደጋም አይደለችም። 15 ካም በልጆቹ መካከል አካፈለ። የመጀመሪያው ዕጣም ለኩሽ ወደ ምሥራቅ ወጣ፥ ምዕራቡ ለምጽራይም ወጣ፥ ምዕራቡም ለፉጥ ወጣ፤ ምዕራቡም ለከነዓን ወጣ፤ በምዕራቡም በኩል ባሕር ነበር። 16 ሴምም በልጆቹ መካከል አካፈለ። መጀመሪያው ዕጣ ለኤላምና ለልጆቹ እስከ ሕንደኬ ምድር ሁሉ ምሥራቅ እስኪቀርብ ድረስ ወደ ጤግሮስ ወንዝ ምሥራቅ ወጣ፤ ኤርትራም በእጁ ነበር። የዲዳን ውኃ፥ የሞብሪ ተራሮች፥ የኤላ ሀገር ሁሉ፥ የሱሳም ሀገር ሁሉ፥ በፊርኖክ በኩል ያለው ሁሉ፥ እስከ ኤርትራ ባሕርና እስከ ጢና ወንዝ። 17 ለአሶርም ሁለተኛው ዕጣ ወጣ፤ የአሱርና ነነዌ ሀገር ሁሉ፥ ሰናዖርም፥ ሳድም እስከ ሕንደኬ አቅራቢያ ድረስ። ወደ ወድፋ ፈሳሽም ይደርሳል። 18 ለአርፋክስድም ሦስተኛው ዕጣ ወጣ። የከላውዴዎን አውራጃ ሀገር ሁሉ፥ ለኤርትራ ባሕር የቀረበው የኤፍራጥስ ምሥራቅም፥ ወደ ግብፅ እስከምትመለከተው እስከ ልሳነ ባሕር አቅራቢያ ድረስ የምድረ በዳው ውኃ ሁሉ፥ የሊባኖስና የሳኔር ሀገር፥ አማናም፥ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ። 19 ለአራምም አራተኛው ዕጣ ወጣ፤ በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል የመስጴጦምያ ሀገር ሁሉ በከላውዴዎን ደቡብ ወዳለ እስከ አሱር አቅራቢያ ድረስ፥ የአራራትም ሀገር ሁሉ የእርሱ ነው። 20 ለሉድም አምስተኛው ዕጣ ወጣ፤ የአሱር ተራራ ሁሉ፥ ወደ ታላቁ ባሕር እስኪቀርብ ድረስ የእርሱ ዕጣ ነው። ወደ ወንድሙ ወደ አሶር ምሥራቅም ይደርሳል። 21 ያፌትም ምድረ ርስትን በልጆቹ መካከል ከፈለ። መጀመሪያውም ዕጣ ከደቡብ አንጻር ጀምሮ እስከ ጢና ወንዝ ድረስ በምሥራቅ በኩል ለሴሜር ወጣ። በደቡብም በኩል የደቡብ ዙሪያ ሁሉ ለሚአት ባሕር እስኪቀርብ ድረስ ለማጎግ ወጣ። 22 ከምዕራቡ ጀምሮ እስከ ደሴቶችና እስከ ደሴቶችም ዳርቻ ድረስ ለሁለቱ ወንድሞቹ ሁሉ ይይዝ ዘንድ ለማዳይ ደረሰ። 23 ለኢዮእያንም አራተኛው ዕጣ ወጣ፥ ደሴቱ ሁሉ፥ በሉድም አንጻር ያሉ ደሴቶች ሁሉ። 24 ለቶቤልም እስከ ሁለተኛዪቱ ልሳን ድረስ ወደ ሉድ ዕጣ በምትቀርብ በልሳን መካከል አምስተኛው ዕጣ ወጣ። የሁለተኛዪቱም ልሳን አውራጃ እስከ ሦስተኛዪቱ ልሳን ድረስ ነው። 25 ለሞሳክም ስድስተኛው ዕጣ ወጣ። እስከ ጋዴር ምሥራቅም እስኪቀርብ ድረስ የሦስተኛዪቱ ልሳን አውራጃ ሁሉ። 26 ለቲራስም ሰባተኛው ዕጣ ወጣ። በባሕር መካከል ያሉ፥ ለካም ዕጣ የሚቀርቡ ታላላቁ አራቱ ደሴቶች፤ የክማቱሪ ደሴቶችም በርስትነት ዕጣ ለአርፋክስድ ልጆች ወጡ፤ የኖኅም ልጆች ለልጆቻቸው በአባታቸው በኖኅ ፊት እንዲህ አድርገው ከፈሉ። በዕጣው ያልወጣለትን ክፍል ይይዝ ዘንድ የሚፈልገውን እያንዳንዱን አምሎ ረገመ። 27 ሁሉም ይሁን አሉ። ስለሚያጸይፍ ክፉ ኀጢአታቸው ሁሉ፥ ምድርንም በበደልና በርኵሰት፥ በዝሙትና በኀጢአትም ስለ ሞሉአት እግዚአብሔር አምላክ በሰይፍና በእሳት ይፈርድባቸው ዘንድ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ በራሳቸውና በልጆቻቸው፥ በዘራቸውም እስከ ዘለዓለም ይሁን አሉ። |