ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በዚህ ኢዮቤልዩ በሰባተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት መርከቢቱ ባረፈችበት ስሙ ሉባር በሚባል ከአራራት ተራሮች በአንዱ ተራራ ላይ ኖኅ ወይንን ተከለ። 2 በአራተኛውም ዓመት አፈራ፤ ፍሬውንም ጠበቀ፤ በዚያውም ዓመት በሰባተኛው ወር ፍሬውን ለቀመ። ከእርሱም ጠጅ ጥሎ በዕቃ አኖረው፥ እስከ አምስተኛውም ዓመት እስከ መጀመሪያው ወር መጀመሪያዪቱ ቀን ድረስ ጠበቀው። 3 ይህችንም ቀን በደስታ በዓል አደረገ፥ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕትን ሠዋ። የራሱንም ኀጢአት ያስተሰርይበት ዘንድ ከላሞች አንድ ወይፈንን፥ አንድ የበግ አውራን፥ ዓመት የሆናቸው ሰባት በጎችን፥ አንዲት የፍየል ጠቦትንም ሠዋ። 4 ስለ ልጆቹም አስቀድሞ ጠቦትን ሠዋ፤ ከደሙም በሠራው መሠዊያ ላይ ባለው ሥጋ ላይ አኖረ። የሚቃጠል መሥዋዕትንም በሠዋበት መሠዊያ ላይ ስቡን ሁሉ አጤሰ። ላሙንና የበጉን አውራ፥ በጎቹንም ሠውቶ ሥጋቸውን ሁሉ በመሠዊያው ላይ አኖረ። በዘይት የተለወሰ መሥዋዕታቸውንም ሁሉ በላያቸው አኖረ። 5 ከዚህም በኋላ በመሠዊያው ላይ ባለው እሳት ላይ ወይኑን ረጨ። አስቀድሞ ዕጣኑን በመሠዊያው ላይ አኖረ፤ እግአብሔር የሚወደውንም በጎ መሥዋዕት ሠዋ። መሥዋዕቱም ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ዐረገ፤ ከዚህም ወይን ጠጥቶ ደስ አለው። ልጆቹንም ደስ አላቸው። 6 በመሸም ጊዜ ወደ ድንኳኑ ገብቶ ሰክሮ ተኛ፤ በድንኳኑም ተኝቶ ዕርቃኑን ጣለ። 7 ካምም አባቱ ኖኅን ዕራቁቱን እንደ ሆነ አየ፤ ወጥቶም በውጭ ለነበሩ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። 8 ሴምም ልብሱን ይዞ ተነሣ፤ እርሱና ያፌትም ልብሳቸውን ከጫንቃቸው አውርደው አለበሱት፥ ፊታቸውንም ወደ ኋላ መልሰው የአባታቸውን ኀፍረት ሸፈኑ። 9 ኖኅም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ ታናሹ ልጁ በእርሱ ላይ ያደረገበትን ሁሉ ዐወቀ፥ ልጁንም ረገመው፥ “የተረገመ ከነዓን ለወንድሞቹ ተገዥ ባሪያ ይሁን” አለ። 10 ሴምንም መረቀው፤ እንዲህም አለ፥ “የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ከነዓንም ባሪያው ይሁን፤ እግዚአብሔርም የያፌትን ሀገር ያስፋለት፥ እግዚአብሔርም በሴም ድንኳን ይደር፤ ከነዓንም ባሪያው ይሁን።” 11 ካምም አባቱ ታናሹን ልጁን እንደ ረገመው ዐወቀ። ልጁንም ረግሞታልና ለእርሱ ክፉ ነገር ሆነበት፤ እርሱም ከአባቱ ተለየ፤ ልጆቹም ከእርሱ ጋር ነበሩ። እነዚህም ኩሽና ሜስራይም፥ ፉጥና ከነዓን ናቸው። እርሱም ከተማን አቀና፤ የከተማዪቱንም ስም በሚስቱ ስም አኤልታማክ ብሎ ጠራት። 12 ያፌትም አይቶ በወንድሙ ቀና፤ እርሱም ከተማን አቀና፤ ስምዋንም በሚስቱ ስም አዶታኔስስ ብሎ ጠራት። 13 ሴም ግን ከአባቱ ከኖኅ ጋር ተቀመጠ፤ በአባቱም እጅ በተራራው ላይ ከተማን አቀና፤ እርሱም ስምዋን በሚስቱ በሴዴቄተልባብ ስም ጠራ። 14 እነዚህም ሦስቱ ከተሞች፥ እነሆ፥ በሉባር ተራራ አቅራቢያ ናቸው። ሴዴቄተልባብም በተራራው አንጻር በምሥራቅ ናት፥ አኤልታማክም በሰሜን አንጻር ናት፤ አዶታኒስስም በምዕራብ ናት። 15 የሴምም ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ኤላምና አሱር፥ አርፋክስድም ሉድና አራምም፥ እነዚህ የጥፋት ውኃ ከሆነበት ከአራተኛው ዓመት በኋላ የተወለዱ ናቸው። ያፌትም ጎሜርንና ማጎግን፥ ያዋንንና ቶቤልን፥ ሞሳክንና ቴራስን ወለደ። እነዚህ ሁሉ የኖኅ ልጆች ናቸው። 16 ኖኅም በሃያ ስምንተኛው ኢዮቤልዩ ለልጅ ልጆቹ ሥርዐትንና ትእዛዝን፥ የሚያውቀውንም ፍርድ ሁሉ ያዝዝ ጀመረ። እውነትንም ያደርጉ ዘንድ፥ የሰውነታቸውንም ኀፍረት ይሸፍኑ ዘንድ፥ የፈጠራቸው እግዚአብሔርንም ያመሰግኑ ዘንድ፥ አባትና እናታቸውንም ያከብሩ ዘንድ፥ እያንዳንዳቸውም ባልንጀራቸውን ይወድዱ ዘንድ፥ ሰውነታቸውንም ከዝሙትና ከርኵሰት፥ ከበደልም ይጠብቁ ዘንድ ያዝዛቸው ጀመር። 17 ትጉሃን ከታዘዘላቸው ሕግ ወጥተው ከሰው ልጆች ጋር ስላደረጉት ዝሙት በእነዚህ በሦስቱ ኀጢአቶች በምድር ላይ የጥፋት ውኃ ተደርጎአልና። 18 ከመረጡአቸው ሴቶችም ሁሉ ሚስቶችን አገቡ፥ አስቀድመውም ርኵሰትን ሠሩ። ኀይለኞች ልጆችንም ወለዱ፤ ሁሉም አይመሳሰሉም ነበሩ። 19 እያንዳንዱም ባልንጀራውን ይበላው ነበር። አርበኛውም ናፊልን ገደለው፤ ናፊልም ኢልዮንን ገደለው፥ ኢልዮንም የሰውን ልጅ ገደለው። ሰውም ባልንጀራውን ገደለው፤ ሁሉም ዐመፅን ያደርግ ዘንድ፥ ንጹሕ ደምንም ያፈስስ ዘንድ ተመለሰ። ምድርም ዐመፅን ተሞላች፥ ከእነዚህም ሁሉ በኋላ በአውሬዎችና በወፎች፥ በምድር ላይም በሚንቀሳቀሰውና በሚመላለሰው ሁሉ ላይ በደሉ። 20 በምድርም ላይ ብዙ ደም ፈሰሰ፤ የሰውም ልቡናውና ፈቃዱ በዘመኑ ሁሉ ከንቱና ክፉ ነገርን ያስቡ ጀመር። 21 እግዚአብሔርም ስለ ክፉ ሥራቸው በምድር ሁሉ ፊት ሁሉን አጠፋ። በምድርም ስላፈሰሱት ደም ሁሉን ደመሰሰ፤ “እኔና እናንተ ልጆች፥ ከእኛም ጋር ወደ መርከብ የገባው ሁሉ ቀረን። 22 በጥፋት ሥራ ጸንታችሁ ትኖሩ ዘንድ ጀምራችኋልና እናንተ በእውነት ሥራ ጸንታችሁ የምትኖሩ እንዳልሆናችሁ እነሆ፥ እኔ የቀደመ ሥራችሁን አየሁ። እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ትለያላችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ትቀናናላችሁ። 23 ልጆች፥ አንዱ ከአንዱ ጋር በአንድነት እንደማትኖሩ እኔ አያለሁ፤ አጋንንትም በእናንተና በልጆቻችሁ ላይ እነሆ፥ ማሳት ጀመሩ። 24 አሁንም እኔ ከሞትሁ በኋላ በምድር ላይ የሰውን ደም ታፈስሳላችሁ፤ እናንተም ከገጸ ምድር ትጠፋላችሁ ብዬ እኔ ስለ እናንተ እፈራለሁ። የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉና ብርንዶ የሚበላ ሁሉ፥ ሁሉም ከዚህ ዓለም ይጠፋሉና፤ ብርንዶንም የሚበላ ደምንም የሚያፈስስ ሁሉ በዚህ ዓለም አይቀርምና። 25 ወደ መቃብር ይሄዳሉና፥ ቍርጥ ፍርድ ወዳለበት ወደ ሲኦልም ይወርዳሉና፥ ሁሉም በክፉ ሞት ተይዘው ወደ ጨለማው ጥልቅ ይጣላሉና፥ ከሰማይ በታች ልጅ፥ የልጅ ልጅም በሕይወት አይቀርለትም። 26 “ማንኛውንም አውሬና እንስሳ፥ በምድር ላይ የሚበርረውንም ባረዳችሁ ጊዜ በዘመናችሁ ሁሉ ከማንኛውም ደም፦ ደም ሁሉ በእናንተ ላይ አይታይ። 27 በምድር ላይ የሚፈስሰውን ደም በመቅበር ስለ ሰውነታችሁ ምጽዋት መጽውቱ፤ ከደም ጋር የሚበላም አትሁኑ። ሌሎችም በፊታችሁ ደም እንዳይበሉ ተጠንቀቁ። እኔ እንደዚህ ታዝዣለሁና ደሙን ቅበሩ። 28 በእናንተና በልጆቻችሁ ከሰው ሁሉ ጋር እመሰክርባችኋለሁ። በምድር ላይ ደምን ከሚያፈስስ ሰው ሁሉ ጋር በሰውነታችሁ ደማችሁን የሚመረምሩአችሁ እንዳይሆኑ ነፍስን ከሥጋ ጋር አትብሉአት፤ ምድር በትውልዱ ሁሉ ደምን ባፈሰሰ ሰው ደም የምትነጻ ስለሆነ ምድር በላይዋ ከፈሰሰ ደም አትነጻምና። 29 “አሁንም ልጆች፥ ስሙኝ፥ በምድር ሁሉ በእውነት ፊት ጸንታችሁ ትኖሩ ዘንድ፥ ክብራችሁም ከጥፋት ውኃ ባዳነኝ በአምላኬ በእግዚአብሔር ፊት ይገለጥ ዘንድ ፍርድንና ጽድቅን ፍረዱ። 30 እነሆ፥ እናንተም ሄዳችሁ ከተሞችን ታቀናላችሁ፤ በውስጣቸውም በምድር ላይ ያለውን ተክል ሁሉ ትተክላላችሁ። ተክሉም ሁሉ በሦስተኛው ዓመት የሚያፈራውን ፍሬ ሁሉ ለመብላት የማይለቀም ይሆናል። 31 በአራተኛውም ዓመት ፍሬው ይቀደሳል፤ ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በልዑል እግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለውንም የፍሬውን መጀመሪያ ይሠዋሉ፥ የወይኑንና የዘይቱን መጀመሪያ፥ እንደ አዝመራው መጀመሪያ በሚቀበለው በእግዚአብሔር መሠዊያ በፈሳሽነት ያቀርባሉ፤ የቀረውንም የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች መሥዋዕቱን በሚቀበልበት በመሠዊያው ፊት ይብሉት። 32 እናንተ በእውነትና በሚገባ ትተዉት ዘንድ በአምስተኛው ዓመት ዕረፍትን አድርጉ፤ እናንተም ትከብራላችሁ፤ ተክላችሁም ሁሉ የበጀ ይሆናል። የአባታችሁ አባት ሄኖክ ልጁ ማቱሳላን እንዲሁ አዝዞታልና፤ ማቱሳላም ልጁ ላሜህን አዝዞታልና፤ ላሜህም አባቶቹ ያዘዙትን ሁሉ ለእኔ አዝዞኛልና። 33 እኔም፥ ልጆች ሆይ፥ ሄኖክ ልጁን እንዳዘዘው አዝዛችኋለሁ፤ በመጀመሪያው ኢዮቤልዩ በሕይወት ሳለ በሰባተኛው ትውልድ ማቱሳላ እስከሚሞትባት ቀን ድረስ ልጆቹንና የልጆቹን ልጆች አዝዞ አዳኘ።” 34 በሃያ ዘጠነኛው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት አርፋክስድ ሚስት አገባ፤ ስምዋም ራሱእያ ይባላል፤ ይህችውም የኤላም ልጅ የሱሳን ልጅ ናት። በሦስተኛው ዓመት በዚህ ሱባዔ ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ ስሙንም ቃይናም አለው፤ ልጁም አደገ፤ አባቱም መጽሐፍን አስተማረው። 35 ከተማንም የሚይዝበት ቦታን ይፈልግ ዘንድ ሄደ፤ የቀደሙ ሰዎችም በድንጋይ የቀረፁትን መጽሐፍ አገኘ። በእርስዋም ያለውን አንብቦ ተረጐመ። የፀሓይንና የጨረቃን፥ የከዋክብትንም ሰገል ከሰማይ ምልክቶች ጋር የሚመለከቱበት የትጉሃን ትምህርት ሁሉ በእርስዋ ስለ ነበር በእርስዋ በተጻፈው በደለ። 36 እርሱም ጻፋት፥ የእርስዋንም ነገር አልተናገረም። ስለ እርስዋ በእርሱ እንዳይቈጣ የእርስዋን ነገር ለመናገር ኖኅን ይፈራዋልና። 37 በሠላሳኛው ኢዮቤልዩ በሁለተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ሚስትን አገባ፤ ስምዋም ሜልካ ይባላል፤ ይህችውም የያፌት ልጅ የአበዳይ ልጅ ናት። 38 በአራተኛውም ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት፦ ስሙንም ሳላ አለው፤ መልእክትን ተልኬአለሁ ብሎአልና፤ ሳላም አደገ፤ በሠላሳ አንደኛውም ኢዮቤልዩ በአምስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ሚስትን አገባ ስምዋም ሙአክ ይባላል፤ ይህችውም የአባቱ ወንድም የኬሴድ ልጅ ናት። 39 በአምስተኛውም ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ ስሙንም ኤቦር አለው። እርሱም በሠላሳ ሁለተኛው ኢዮቤልዩ በሰባተኛው ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ሚስትን አገባ፤ ስምዋም አዙራድ ይባላል፥ ይህችውም የአብሮድ ልጅ ናት። 40 በስድስተኛውም ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ ስሙንም ፋሌክ አለው፤ በተወለደበት ዘመን የኖኅ ልጆች ምድርን ሊካፈሉ ጀምረዋልና፤ ስለዚህም ስሙን ፋሌክ ብሎ ጠራው፤ እርስ በርሳቸውም አስተካክለው ተካፈሉ፥ ለኖኅም ነገሩት። |