ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በዐሥረኛው ወር መባቻም የተራሮች ራሶች ታዩ፤ በመጀመሪያው ወር መባቻም ምድር ታየች፤ ውኃዎችም በአምስተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት ከምድር ላይ ደረቁ። በዐሥራ ሰባተኛውም ቀን በሁለተኛው ወር ምድር ደረቀች። 2 በሃያ ሰባተኛውም ቀን መርከቢቱን ከፈታት፤ ከውስጥዋም አራዊትንና ወፎችን፥ የሚንቀሳቀሰውንም ሁሉ ሰደደ። በሦስተኛውም ወር መባቻ ኖኅ ከመርከብ ወጣ። በዚህም ተራራ ላይ መሠዊያን ሠራ፤ ለምድርም አስተሰረየ። ከኖኅ ጋር በመርከብ ካሉት በቀር በእርስዋ ያለው ሁሉ ጠፍቶአልና የፍየል ጠቦት ሠውቶ በደሙ የምድርን ኀጢአት ሁሉ አስተሰረየ። 3 ስቡንም በመሠዊያው ላይ አጤሰ። ላምን ፍየልንና የበግ አውራን፥ ጨውን፥ ርግብንና ዋኖስንም ሠውቶ በመሠዊያው ላይ ስቡን አሻተተ። በዘይት የታሸ መሥዋዕትንም በእነርሱ ላይ ጨመረ። 4 ደሙንና ወይኑንም አምጥቶ በሁሉ ላይ ዕጣን ጨመረበት። እግዚአብሔርም የሚወደውን በጎ መዓዛ አድርጎ አቀረበ። 5 እግዚአብሔርም በጎ መዓዛውን ተቀበለው፤ የጥፋትም ውኃ ምድርን እንዳያጠፋ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። እንዲህም አለ፥ “በምድርም ዘመን ሁሉ ዘርና አዝመራ አይቋረጥም፤ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት ሥርዐታቸውን አይለውጡም። ለዘለዓለሙም አይቋረጡም። 6 “እናንተም ብዙ፥ በምድርም የብዙ ብዙ ሁኑ፥ በላይዋም ብዙ፥ ለበረከትም ሁኑ፤ ከእናንተም የተነሣ መፍራትንና መንቀጥቀጥን በምድርና በባሕር ውስጥ ባሉ ሁሉ ላይ አመጣለሁ። 7 እነሆ፥ አውሬዎችንና ከብቶችን ሁሉ፥ በክንፍ የሚበሩትንና በምድርና በባሕር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ዓሣዎችን ሰጠኋችሁ፥ ሁሉንም ትበሉ ዘንድ ልምላሜውን ለምግብነት ሰጠኋችሁ። 8 ነገር ግን ደም የነፍስ ማደሪያ ነውና ከሰውነታችሁ መካከል ደማችሁን እንዳልፈልግ ደመ ነፍስ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ። ከሰውም ሁሉ እጅ፥ ከአራዊትም ሁሉ እጅ የሰውን ደም እመራመራለሁ፤ የሰውንም ደም ያፈሰሰ ደሙ ይፈስሳል፥ እግዚአብሔርም አዳምና ሔዋንን በእርሱ መልክ ፈጥሮአቸዋልና እናንተ ብዙ፤ በምድርም ላይ የብዙ ብዙ ሁኑ” አላቸው። 9 ኖኅና ልጆቹም በሥጋው ሁሉ ያለ ብርንዶውን ሁሉ እንዳይበሉ ማሉ። በምድር ዘመን ሁሉ በዚህ ወራት በዘለዓለማዊ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ገባ። 10 ስለዚህም፥ “አንተ ከእስራኤል ልጆች ጋር በዚህ ወራት በተራራው ላይ በመሐላ ቃል ኪዳን ታደርግ ዘንድ ተናገረህ፤ እግዚአብሔርም በዘመኑ ሁሉ ከእነርሱ ጋር ስለ አደረገው ቃል ኪዳን በላያቸው ደምን ትረጫለህ። 11 በምድርም ዘመን ሁሉ የወፎችንና የአውሬዎችን ሥጋ ሁሉ እንዳትበሉ በዘመኑ ሁሉ ትጠብቁአት ዘንድ ይህች ምስክር በእናንተ ላይ የተጻፈች ናት። 12 በምድርም ዘመን ሁሉ የአውሬውን፥ የከብቶችንና የወፎችን ሥጋ ብርንዶውን የበላ ሰው እርሱና ዘሩ ከምድር ይጠፋሉ። 13 አንተም በዘመኑ ሁሉ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ስማቸውና ዘራቸው ጸንቶ ይኖር ዘንድ ብርንዶውን ሁሉ እንዳይበሉ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 14 በቀኑ ሁሉ በመሠዊያው አንጻር በደም ስለ እናንተ እየለመኑ እንዲኖሩ ለልጅ ልጅ ይጠብቁት ዘንድ የዘለዓለም ሕግ ነውና ለዚህ ሕግ የዘመን ፍጻሜ የለውም። ይጠብቁትም ዘንድ እንዳይጠፉ ማታና ጥዋት ስለ እነርሱ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአታቸውን ያስተሰርያሉ። 15 “ዳግመኛም በምድር ላይ ጥፋት እንዳይሆን ለኖኅና ለልጆቹ የቃል ኪዳኑን ምልክት ሰጣቸው፤ እርስዋንም ዳግመኛ ለማጥፋት በዘመኑ ሁሉ በምድር ላይ የጥፋት ውኃ እንዳይሆን ለዘለዓለም ለቃል ኪዳኑ ምልክት ቀስቱን በደመና ውስጥ ሰጠ። 16 “ስለዚህም በዘመኑ ሁሉ ለአዲስ ኪዳን በየዓመቱ አንድ ጊዜ በዚህ ወር የሱባዔያትን በዓል የሚያደርጉ ይሆኑ ዘንድ ተሠራ፤ በሰማይ ጽላትም ተጻፈ። 17 ይህችም በዓል ከፍጥረት ቀን ጀምሮ እስከ ኖኅ ዘመን ድረስ በሰማይ ስትሠራ ኖረች፤ ይኸውም ሃያ ሰባት ኢዮቤልዩና አምስት የዓመት ሱባዔ ነው። ኖኅና ልጆቹም፥ ኖኅ እስከሚሞትባት ቀን ድረስ ሰባት ኢዮቤልዩና አንድ የዓመት ሱባዔ ጠበቁት። 18 ኖኅ ከሞተ በኋላም እስከ አብርሃም ዘመን ድረስ ልጆቹ ሕግን አፈረሱ፤ ብርንዶውንም በሉ። ነገር ግን አብርሃም ብቻ ሕግን ጠበቀ፤ ይስሐቅና ያዕቆብም እስከ አንተ ዘመን ድረስ ጠበቁት። በዘመንህም በዚህ ተራራ እስካድሳቸው ድረስ የእስራኤል ልጆች ሕግን ዘነጉ። 19 አንተም የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ ይህችንም በዓል በትውልዳቸው ሁሉ ለእነርሱ እንደ ታዘዘ ይጠብቁአት። በሱባዔ የምትደረግ በዓል ናትና በዓመት አንድ ቀን በዚህ ወር ይህችን በዓል ያድርጉ። 20 የመጀመሪያውም አዝመራ የሚሰበሰብባት በዓል ናትና። ይህችውም ሁለት ቀን በዓል የሚያደርጉባት ሁለት አይነት በዓል ናት። በየጊዜዋም ታደርጋት ዘንድ በጻፍሁልህ በዚህ በመጀመሪያው የሕግ መጽሐፍ ጽፌልሃለሁና ስለ እርስዋ ሥራዋ እንደ ተጻፈና እንደ ተቀረፀ ከዓመት አንድ ቀን ጠብቃት። 21 የታሰቡም ይሆኑ ዘንድ፥ የእስራኤልም ልጆች በየወገናቸው ለእያንዳንዱ ዓመት በዚህ ወር አንድ ቀን ያደርጉአት ዘንድ ቍርባኑን ነገርሁህ። 22 “በመጀመሪያው ወር መባቻ፥ በአራተኛውም ወር መባቻ፥ በሰባተኛውም ወር መባቻ፥ በዐሥረኛውም ወር መባቻ እነዚህ የመታሰቢያ ቀኖች ናቸው። በአራቱም ክፍለ ዓመት፥ ጊዜ ያላቸው ቀኖች ናቸው፤ እነዚህም ለስምንተኛው ዓመት የተጻፉና የተዘጋጁ ናቸው። 23 ኖኅም እነርሱ ለእርሱ መታሰቢያ እስኪሆኑለት ድረስ በዓላትን ለልጅ ልጅ ለዘለዓለም ሠራቸው። 24 በመጀመሪያው ወር መባቻ ለራሱ መርከብን ይሠራ ዘንድ ተነገረው፤ በእርስዋም ምድር ደረቀች፤ መስኮቱንም ከፍቶ ምድርን አየ። 25 በአራተኛው ወር መባቻ የታችኛው የጥልቁ ምንጭ አፍ ተዘጋ። የሰማዩም ሻሻቴ ተገታ። 26 በሰባተኛው ወር መባቻ በምድር ያለ የምንጭ ውኃ ጕድጓድ ሁሉ ተከፈተ፤ ውኃዎችም ወደ ታችኛው ጥልቅ ይወርዱ ጀመር። 27 በዐሥረኛውም ወር መባቻ የተራሮች ራሶች ታዩ፥ ኖኅም ደስ አለው፤ ስለዚህም እነርሱን እስከ ዘለዓለም ድረስ ለመታሰቢያ በዓላት አደረጋቸው። እነዚህ እንዲህ የተሠሩ ናቸው፤ ወደ ሰማይ ጽላትም ያወጡአቸዋል። 28 ከእነርሱም እያንዳንድዋ ከዚችኛዪቱ እስከዚያችኛዪቱ መታሰቢያ፥ ከመጀመሪያዪቱ እስከ ሁለተኛዪቱ፥ ከሁለተኛዪቱ እስከ ሦስተኛዪቱ፥ ከሦስተኛዪቱ እስከ አራተኛዪቱ ድረስ ዐሥራ ሦስት ሱባዔ ናቸው። 29 የትእዛዛት ቀኖች ሁሉ ቀን የሚቈጠርባቸው አምሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናሉ። ፍጹም የሆነ ዓመቱ ሁሉ እንዲህ ተቀርፆና ተቈጥሮ በሰማይ ጽላት ተጻፈ። አንድ ዓመትና ሁለት ዓመት፥ ሦስት ዓመትም መተላለፍ የለውም። 30 አንተም የእስራኤልን ልጆች በዓመቱ በዚህ ቍጥር ሦስት መቶ ስድሳ አራት ቀንን ይጠብቁ ዘንድ እዘዛቸው፤ ፍጹም ዓመትም ይሆናል። ጊዜውንም ከቀኑና ከበዓሉ አሳልፈው አያጥፉ። ሁሉ እንደ ምስክርነታቸው ይደርስባቸዋልና ቀኑን አያስቀሩ፤ በዓሉንም አያጥፉ። 31 ቢተላለፉአቸውም፥ እንደ እርሱ ትእዛዝም ባያደርጉአቸው ያን ጊዜ ሁሉም ጊዜዎቻቸውን ያጠፋሉ። 32 ዓመታትም ከዚህ ወደዚያ ይለዋወጣሉ፤ ጊዜያትም ይጠፋሉ፤ ዓመታቱም ይለዋወጣሉ፤ ሥርዐታቸውንም ያፈርሳሉ፤ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ይዘነጋሉ። የዓመታትንም መንገድ አያገኙም፤ መባቻውን ይረሳሉ፤ ጊዜውንና ሱባዔውን፥ የዘመኑንም ሥርዐት ሁሉ ያፈርሳሉ። 33 እኔ አውቃለሁና፥ እንግዲህ ወዲህ እኔ እነግርሃለሁ፤ እንዲህ ያለ መጽሐፍ በፊቴ ተጽፎአልና፥ የምነግርህ ከልቤ አይደለም፤ ከሳቱ በኋላ አእምሮአቸውንም ካጡ በኋላ የቃል ኪዳኑን በዓል እንዳይረሱ፥ በአሕዛብ በዓላትም እንዳይሄዱ የዘመኑ አከፋፈል በሰማይ ጽላት ተጻፈ። 34 “እርስዋ ጊዜያትን ትለውጣለችና፥ ከዓመታትም ለዓመት ዐሥር ቀን ትቀድማለችና፥ በጨረቃ አጐዳደል ጨረቃን የሚመለከቱ ይሆናሉ። 35 ስለዚህ ሥርዐትን ከለወጡ በኋላ ዓመታት ይመጡላቸዋል፤ ምስክር የምትሆን ቀንንም የተናቀች ያደርጋሉ። የረከሰችውምን ቀን በዓል ያደርጋሉ፤ ሁሉንም ይቀላቅላሉ፤ የተቀደሱትን ቀናት የረከሱ፥ የረከሱትንም ቀናት ለቅድስና ያደርጋሉ፤ ወራቶችንና ሱባዔዎችን፥ በዓላቱንና ኢዮቤላቱን ይስታሉና። 36 ስለዚህም እኔ አዝዝሃለሁ፤ ልጆችህ አንተ ከሞትህ በኋላ ሦስት መቶ ስድሳ አራቱን ቀን ብቻ ዓመትን እንዳያደርጉ ሥርዐትን ይለውጣሉና ታዳኝባቸው ዘንድ አዳኝብሃለሁ። 37 ስለዚህም የወሩን መባቻና ሱባዔውን፥ ጊዜውንና በዓላቱን ይስታሉ፤ ከሰው ሁሉ ጋር ብርንዶውን ሁሉ ይበላሉ።” |