ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በዚህም ሱባዔ ወንድ ልጅን ወለደችለት፥ ከሥራዬ ሁሉና ከኀዘኔ ሁሉ እግዚአብሔርም ከረገማት ምድር የሚያረጋጋኝ ነው ሲል ስሙን ኖኅ አለው። 2 በዐሥራ ዘጠነኛው ኢዮቤልዩ መጨረሻ በሰባተኛው ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት አዳም ሞተ። ልጆቹም ሁሉ በተፈጠረበት ምድር ቀበሩት። 3 እርሱም አስቀድሞ በምድር ተቀበረ፤ ከሺህ ዓመትም ሰባ ዓመትን አጐደለ። ይህችውም በሰማይ ምስክር እንደ አንዲት ቀን ነበረች። 4 “ከእርሱ በምትበሉበት ቀን ትሞታላችሁ” ተብሎአልና ስለዚህ ዕውቀትን የሚያሳውቅ ዕፅን ስለ በላ ተጻፈ፤ በእርስዋ ሞቶአልና ስለዚህ ነገር የአንዲቱን ቀን ዓመቶች አልጨረሰም። 5 በዚህ ኢዮቤልዩ መጨረሻ ከአንድ ዓመት በኋላ ቃየን ሞተ፤ ቤቱ በላዩ ተናደ፤ በቤቱም ውስጥ በድንጋዮች ሞተ። አቤልን በድንጋይ ገድሎታልና በእውነት ፍርድ በድንጋይ ሞተ። 6 ስለዚህ ሰው ባልንጀራውን በሚገድልበት መሣሪያ ይሞት ዘንድ እንዳቈሰለውም ያቈስሉት ዘንድ በሰማይ ጽላት ተጻፈ። 7 በሃያ አምስተኛው ኢዮቤልዩ ኖኅ ሚስት አገባ። ስምዋም አምዛራ ይባላል። ይህችውም የእኅቱ ልጅ የራዚኤል ልጅ ናት፤ ሚስትም ልትሆነው አገባት። በመጀመሪያም ዓመት በአምስተኛው ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ሴምን ወለደችለት። በአምስተኛውም ዓመት ካምን ወለደችለት። 8 በመጀመሪያው ዓመት በስድስተኛው ሱባዔ ያፌትን ወለደችለት። 9 የአዳም ልጆች በምድር ላይ ይበዙ ዘንድ በጀመሩ ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። የእግዚአብሔር መላእክትም በዚህ ኢዮቤልዩ በአንዲቱ ዓመት እነዚህን አዩአቸው። እነዚያ ላዩአቸው መልከ መልካሞች ነበሩና ከመረጡአቸው ሁሉ ሚስቶች ሊሆኑአቸው ወሰዱአቸው፤ ወንዶች ልጆችንም ወለዱላቸው፤ እነዚህም ረዓይት ናቸው። 10 ኀጢአትም በምድር ላይ በዛች፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳና እስከ አራዊት እስከ ወፎችም፥ በምድር ላይ እስከሚኖረውም ሁሉ ድረስ መንገዱን አጠፋ። ሁሉም መንገዳቸውንና ሥርዐታቸውን አጠፉ። እርስ በርሳቸውም ይበላሉ ጀመር። ኀጢአትም በምድር ላይ በዛች። የሰዎችም ሁሉ ዐሳብ፥ በዘመኑ ሁሉ እንዲህ ክፉ ሆነ። 11 እግዚአብሔርም ምድርን ተመለከታት፤ እነሆም፥ ጠፍታ ነበር፤ ሰውም ሁሉ ሥርዐቱን አጠፋ፥ ሁላቸውም በምድር ላይ ያለውን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት አከፉት፤ እርሱም ሰውንና በምድር ላይ የፈጠረውን የሥጋ ወገንን ሁሉ አጠፋዋለሁ አለ። 12 ኖኅ ብቻ በእግዚአብሔር ፊት ባለምዋልነትን አገኘ። ወደ ምድር በሰደዳቸው መላእክቱ ግን ተቈጣ፤ ከሥልጣናቸውም ለይቶ ፈጽሞ ያጠፋቸው ዘንድ አዘዘ። በምድር ጥልቅ ውስጥም አስረን እናግዛቸው ዘንድ አዘዘን። 13 እነርሱም እነሆ፥ በመካከላቸው ተግዘዋል፤ ብቻቸውንም ነበሩ። ከፊቱም በሰይፍ ያጠፋቸው ዘንድ፥ ከሰማይ በታችም ያርቃቸው ዘንድ በልጆቻቸው ላይ ቃል ወጣ። 14 “እነርሱ ሥጋውያን ናቸውና መንፈሴ በሰው ላይ ለዘለዓለም አያድርም። ዕድሜያቸውም መቶ ሃያ ዓመት ይሁን” አለ። 15 እያንዳንዳቸው ባልንጀሮቻቸውን ይገድሉ ዘንድ በመካከላቸው ሰይፍን ሰደደ። ሁሉም በሰይፍ እስኪጠፉ ድረስ አንዱ ሌላውን ይገድል ዘንድ ጀመሩ፤ ከምድርም ጠፉ፤ አባቶቻቸው ግን ይመለከቱ ነበር። 16 ከዚህ በኋላ መንገዳቸውን ባፋለሱ ሁሉ ላይ ፍርድ ሊሆን እስከ ታላቋ የፍርድ ቀን ድረስ በምድር ጥልቅ ውስጥ ተጋዙ። ሥራቸውም በእግዚአብሔር ፊት ነው፤ ከቦታቸውም ሁሉን አጠፋ፥ በኀጢአታቸውም ሁሉ ያልተፈረደበት ከእነርሱ አንድ ስንኳ አልቀረም። 17 በፍጥረታቸው ሁሉ እስከ ዘለዓለም ድረስ እንዳይበድሉ፥ ሁሉም በየወገኑ በዘመኑ ሁሉ የጽድቅ ሥራን እንዲሠራ ለፍጥረቱ ሁሉ አዲስና እውነተኛ ፍጥረትን ፈጠረላቸው። 18 የሁሉም ቅጣት ተዘጋጀ፥ በሰማይም ጽላት ያለ ዐመፃ ተጻፈ። ሁሉም ጸንተው ይኖሩባት ዘንድ ከተሠራችላቸው ሥርዐታቸው የወጡ ናቸው። 19 ጸንተው ባይኖሩባትም ለፍጥረቱ ሁሉ ለየወገኑም ሁሉ ፍርድ ተጻፈ። በሰማይና በምድር፥ በብርሃንና በጨለማ፥ በሲኦልና በጥልቅም፥ በጨለማም ምንም የለም። 20 ፍርዳቸውም ሁሉ ተዘጋጀ፥ የተቀረፀና የተጻፈም ነው። ስለዚህም ታላቁን እንደ ታላቅነቱ፥ ታናሹንም እንደ ታናሽነቱ እያንዳንዱን እንደ ኀጢአቱ ይፈርድበታል። 21 እርሱ ፊት አይቶ የሚያደላ አይደለም። ለእያንዳንዱም ፍርድ አደርጋለሁ ባለ ጊዜ እርሱ መማለጃን የሚቀበል አይደለም፤ እያንዳንዱም በምድር ያለ ሰው ያለውን ሁሉ ቢሰጥ ፊትን አይቶ አያደላም፤ የእውነት ዳኛ ነውና ከእርሱ መማለጃ አይቀበልም። 22 ይህ በእስራኤል ልጆች ላይ ተጽፎ ተሠራ። በእውነትም ወደ እርሱ ከተመለሱ በደላቸውን ሁሉ ይቅር ይላቸዋል። ኀጢአታቸውንም ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል። 23 ከኀጢአታቸውም ሁሉ የተመለሱ ሰዎች ሁሉ በየዓመቱ አንድ ጊዜ ይቅር ይባሉ ዘንድ ተጽፎ ተሠራ። ከጥፋት ውኃም አስቀድሞ ሥርዐታቸውንና ምክራችውን ባጠፉ ሰዎች ሁሉ ላይ ተጻፈ። 24 በእርሱ ምክንያት ከጥፋት ውኃ ስላዳናቸው ልጆቹ እርሱ ባለምዋልነትን አግኝቶአልና ከኖኅ ብቻ በቀር እነርሱ ባለምዋልነትን አላገኙም። ስለ እርሱም እንደ ታዘዘ በመንገዱ ሁሉ ልቡ እውነተኛ ናትና ከተሠራለት ሕግ ሁሉ አልወጣም። 25 እግዚአብሔርም፥ “በምድር ላይ ያለው ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳና አራዊት፥ እስከ አዕዋፍና በምድር ላይ እስከሚንቀሳቀሰው ድረስ ይጥፉ” አለ። 26 ከጥፋት ውኃም ያድነው ዘንድ ኖኅን ለእርሱ መርከብን እንዲሠራ አዘዘው። 27 ኖኅም ዓመታት በሚቈጠሩበት በሁለተኛው ኢዮቤልዩ በአምስተኛው ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት እንዳዘዘው ሁሉ መርከብን ሠራ። 28 በስድስተኛውም ዓመት በሁለተኛው ወር እስከ ዐሥራ ስድስተኛው ቀን ድረስ እርሱ ገባ። ያገባንለትም ሁሉ ወደ መርከብ ገባ። 29 እግዚአብሔርም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን ማታ መርከቡን በውጭ ዘጋው፤ እግዚአብሔርም ሰባቱን የሰማይ ሻሻቴና ሰፊ የሆነ የጥልቁን ምንጮች አፍ በሰባት ስቍረት ከፈተ። 30 ሻሻቴዎችም ከሰማይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ዝናብን ያወርዱ ዘንድ ጀመሩ። 31 የጥልቁም ምንጮች ዓለሙ ሁሉ ውኃን እስኪሞላ ድረስ ውኃዎችን ያወጡ ነበር፤ ውኃዎችም በምድር ላይ በዙ፤ ውኃውም በረጅሙ ተራራ ሁሉ ላይ ዐሥራ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ አለ። 32 ውኃዎችም ከፍ ከፍ አሉ። መርከቢቱም በምድር ላይ ከፍ ከፍ አለች። በውኃውም ላይ ትመላለስ ነበር፤ ውኃዎችም በምድር ላይ አምስት ወር ማለት መቶ አምሳ ቀን ቈዩ። መርከቢቱም ሄደች፥ ከአራራት ተራራዎችም በአንዱ ሉባር በሚባል ተራራ ራስ ላይ ዐረፈች። 33 በአራተኛውም ወር ሰፊ የሆነ የጥልቁ ምንጮች ተገቱ። የሰማዩም ሻሻቴ ተገታ። 34 በሰባተኛውም ወር መባቻ የምድሩ ጥልቅ አፍ ሁሉ ተከፈተ። ውኃዎችም ወደ ታችኛዪቱ ጥልቅ ይወርዱ ጀመር። |