ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በዚያችም ቀን አዳም ከኤዶም ገነት ሲወጣ ለበጎ መዓዛ ነጭ ዕጣን፥ ቀንዓትና ልባንጃ፥ ስንቡልም ኀፍረቱን በሸፈነበት ቀን በጥዋት ፀሓይ ሲወጣ ዐጠነ። 2 በዚያችም ቀን የአራዊትና የእንስሳት ሁሉ፥ የሚመላለሰውና የሚንቀሳቀሰው፥ የወፎችም ሁሉ አፍ ከመናገር ተከለከለ። ከዚያ አስቀድሞ አንዱ ከአንዱ ጋር በአንድ አነጋገርና በአንድ ቋንቋ ይናገሩ ነበርና። 3 በኤዶም ገነት የነበረውንም ሥጋዊ ሁሉ ከኤዶም ገነት አሰናበተ። 4 ሥጋ ለባሹ ሁሉም በየወገናቸውና በየተፈጥሮአቸው ወደ ተፈጠረላቸው ቦታ ተበተኑ። 5 ለአዳም ብቻ ከአራዊትና ከእንስሳት ሁሉ ተለይቶ፥ ኀፍረቱን ይሸፍን ዘንድ ልብስን ሰጠው። ስለዚህ የሕግን ፍርድ በሚያውቁ ሰዎች ሁሉ ላይ ኀፍረታቸውን እንዲሰውሩ እንጂ፥ አሕዛብም እንደሚገለጡ እንዳይገለጡ በሰማይ ጽላት ታዘዘ። 6 በአራተኛው ወር መባቻ አዳምና ሚስቱ ከኤዶም ገነት ወጥተው በተፈጠሩባት ምድር በኤልዳ ምድር ኖሩ። አዳምም የሚስቱን ስም ሔዋን አላት፤ እስከ መጀመሪያው ኢዮቤልዩም ድረስ ልጅ አልነበራቸውም። 7 ከዚህም በኋላ በግብር ዐወቃት፤ እርሱ ግን በኤዶም ገነት እንደ ተማረ ምድርን ያርሳት ነበር። 8 በሦስተኛው ሱባዔ በሁለተኛው ኢዮቤልዩ ቃየንን ወለደች፤ በአራተኛውም ሱባዔ አቤልን ወለደችው፤ በአምስተኛውም ሱባዔ ልጅዋን አዋንን ወለደቻት። 9 እግዚአብሔር ከአቤል እጅ መሥዋዕትን ተቀብሎአልና፥ ከቃየን እጅ ግን መሥዋትን አልተቀበለምና በሦስተኛው ኢዮቤልዩ መጀመሪያ ቃየን አቤልን ገደለው፤ በምድረ በዳም ገደለው፤ ስለ ተገደለም እየተካሰሰ ደሙ ከምድር እስከ ሰማይ ጮኸ። 10 እግዚአብሔርም ስለ ገደለው ስለ አቤል ቃየንን ዘለፈው፤ ስለ ወንድሙ ስለ አቤል ደም በምድር ላይ ተቅበዝባዥ አደረገው፥ በምድርም ረገመው። 11 ስለዚህ ወንድሙን በተንኰል የሚገድል ሰው የተረገመ እንደ ሆነ በሰማይ ጽላት ተጻፈ። ያዩም ሁሉ ይሁን አሉ። አይቶም ያልተናገረ ሰው እንደ እርሱ የተረገመ ይሁን። 12 ስለዚህም እኛ በሰማይና በምድር፥ በብርሃንና በጨለማ በሁሉም የሚደረገውን ኀጢአት ሁሉ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እንናገር ዘንድ መጣን አሉ፤ አዳምና ሚስቱም ስለ አቤል አራት የዘመን ሱባዔ እያለቀሱ ኖሩ። 13 አዳምም በአምስተኛው ሱባዔ በአራተኛው ዓመት ደስ አለው። ዳግመኛ ሚስቱን በግብር ዐወቃት፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት። “ቃየን ስለ ገደለው ስለ አቤልም እግዚአብሔር በምድር ሌላ ዘር አስነሥቶልናል” ብሎአልና ስሙን ሴት አለው። 14 በስድስተኛው ሱባዔ ልጁን አዙራን ወለዳት፥ ቃየንም እኅቱ አዋንን ሚስት ትሆነው ዘንድ አገባት፤ በአራተኛውም ኢዮቤልዩ መጨረሻ ኤኖሕን ወለደችለት። 15 በአምስተኛው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያው ሱባዔ በአንደኛው ዓመት በምድር ቤቶች ተሠሩ። ቃየንም ከተማ ሠራ፤ ስምዋንም በልጁ በኤኖሕ ስም ጠራት። 16 አዳምም ሚስቱ ሔዋንን በግብር ዐወቃት። ዳግመኛም ዘጠኝ ልጆችን ወለደችለት። 17 ሴትም በአምስተኛው ኢዮቤልዩ በአምስተኛው ሱባዔ እኅቱን አዙራን ሚስት አድርጎ አገባት። 18 በአራተኛውም ዓመት ሄኖስን ወለደችለት። እርሱም በምድር ላይ የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የጀመረ ነው። 19 በሰባተኛው ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ ሄኖስ ሚስት ትሆነው ዘንድ እኅቱ ኖአምን አገባ፤ በአምስተኛውም ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም ቃይናን አለው። 20 በስምንተኛው ኢዮቤልዩ መጨረሻ ቃይናን እኅቱን ሙአሊሊትን ሚስት አድርጎ አገባት፤ በዘጠነኛው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያው ሱባዔ በዚህም ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ ስሙንም መላልኤል አለው። 21 በዐሥረኛው ኢዮቤልዩ በሁለተኛው ሱባዔ መላልኤል ሚስት ትሆነው ዘንድ የአባቱን ወንድም የበራኪሄልን ልጅ ዲናን አገባ። በሦስተኛውም ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት፥ ስሙንም ያሮድ አለው። በዘመኑ ትጉሃን የተባሉ የእግዚአብሔር መላእክት በምድር የሰው ልጆችን ያስተምሩ ዘንድ፥ በምድርም ፍርድንና ቅንነትን ያደርጉ ዘንድ ወደ ምድር ወርደዋልና። 22 ያሮድም በዐሥራ አንደኛው ኢዮቤልዩ ሚስት አገባ፤ ስምዋም ባረካ ይባላል፤ ይህችውም የአባቱ እኅት የራሱየል ልጅ ናት፤ በዚህም ኢዮቤልዩ በአራተኛው ሱባዔ ሚስት አገባ፥ በዚህ ኢዮቤልዩ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ሱባዔ ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ ስሙንም ሄኖክ አለው፤ እርሱም አስቀድሞ በምድር ላይ ከተወለዱ ሰዎች ይልቅ መጽሐፍንና ትምህርትን ጥበብንም ተማረ። 23 ሰዎች በየወራቸው እንደ ሥርዐታቸው የዘመናትን ጊዜ ያውቁ ዘንድ እንደ ወራቸው ሥርዐት የሰማይን ምልክት በመጽሐፍ ጻፈ። 24 እርሱም አስቀድሞ ምስክርን ጻፈ። ለሰው ልጆችም በየወገናቸው አሰማባቸው፤ እርሱም በሱባዔ የሚቈጠሩ ቍጥሮችን ተናገረ፤ የዘመኖችንም ቀኖች እርሱ ተናገረ፤ ወሮችንም ሠራ፤ እኛም እንደ ነገርነው ዘመኖችን የሚቈጥሩባቸው ሱባዔዎችን ተናገረ። የተደረገውንና ገና የሚደረገውንም ቍርጥ ፍርድ እስከሚደረግበት ቀን ድረስ በዘመናቸው በሰው ልጆች ላይ የሆነውንና የሚሆነውን ሌሊት በራእይ አየ፤ ዐወቀም። 25 ለምስክርነትም ጻፈው። በሰው ልጆችም ሁሉ ላይ በየትውልዳቸው በምድር ምስክር ሊሆን አኖረው። 26 በዐሥራ ሁለተኛውም ኢዮቤልዩ በሰባተኛው ሱባዔ ሚስት አገባ። ስምዋም አድኒ ይባላል፥ ይህችውም የዳንኤል ልጅ የአባቱ እኅት ልጅ ናት፤ ለእርሱም ሚስት ልትሆነው አገባት። 27 በዚህም ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት። ስሙንም ማቱሳላ ብሎ ጠራው። 28 ከዚህም በኋላ ከአምላክ መላእክት ጋር ስድስት የኢዮቤላት ዘመኖችን ኖረ። በምድርም ያለውን ሁሉ፥ በሰማይም ያለውን የፀሓይን ሥልጣን አሳዩት። 29 ሁሉንም ጻፈ። ከሰው ልጆች ጋር በኀጢአት አንድ ሆነው በደል በሠሩት በትጉሃንም አዳኘባቸው። እነዚህ ከሰው ልጆች ጋር ይረክሱ ዘንድ፥ በግብርም አንድ ይሆኑ ዘንድ ጀምረዋልና፤ ሄኖክም በሁሉ ላይ አዳኘባቸው። 30 ከሰው ልጆችም መካከል ተወሰደ። ለጌትነትና ለክብርም ወደ ኤዶም ገነት ወሰድነው፤ እነሆ፥ እርሱ በዚያ የዘለዓለም ቅጣትንና ቍርጥ ፍርድን፥ የአዳምንም ልጆች ኀጢአት ሁሉ ይጽፋል። 31 ለሰው ሁሉ ልጅ ያሰማ ዘንድ፥ ቍርጥ ፍርድም እስከሚደረግባት ቀን ድረስ የሰውን ሁሉ ሥራ ይናገር ዘንድ እርሱ ለምልክት ተሰጥቶአልና ስለ እርሱ በኤዶም ምድር ላይ ሁሉ የጥፋት ውኃን አመጣ። 32 እርሱም እግዚአብሔር የሚቀበለውን ዕጣን በሠርክ አስቀድሞ ዕጣን በሚቃጠልበት በተቀደሰው ተራራ ላይ ዐጠነ፤ ለእግዚአብሔር በምድር አራት ቦታዎች አሉትና፥ እነዚህም የኤዶም ገነትና ደብረ ዘይት፥ ይህም ዛሬ አንተ በውስጡ ያለህበት ደብረ ሲናና ምድርን ለማንጻት በሚደረግ በአዲስ ፍጥረት የሚነጻ ደብረጽዮን ናቸው። 33 ስለዚህም ምድር ከበደልና ከርኵሰት ሁሉ ለልጅ ልጅ ዘመን ትነጻለች። 34 በዐሥራ አራተኛው ኢዮቤልዩ ማቱሳላ ሚስቱን አድናን አገባ፤ ይህችውም የአባቱ እኅት ልጅ የአዝራኤል ልጅ ናት። 35 በስድስተኛው ሱባዔ በአንደኛው ዘመን ልጅን ወለደ። ስሙንም ላሜህ አለው። 36 በዐሥራ አምስተኛው ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ ላሜህ ሚስት አገባ፤ ስምዋም ቤቴናስ ይባላል፥ ይህችውም የአባቱ የእኅት ልጅ የበራኪኤም ልጅ ናት፤ ሚስት ትሆነው ዘንድም አገባት። |