ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በሁለተኛዉ ሱባዔ በስድስቱ ቀናት በእግዚአብሔር ቃል አራዊትን ሁሉ፥ እንስሳትን ሁሉ፥ አዕዋፍን ሁሉና በምድር የሚንቀሳቀሰውን ፍጥረት ሁሉ፥ በውኃውም ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ፍጥረት ሁሉ በየወገናቸውና በየመልካቸው ወደ አዳም አመጣን። 2 በመጀመሪያዪቱ ቀን አራዊትን፥ በሁለተኛዪቱ ቀን እንስሳትን፥ በሦስተኛዪቱ ቀን አዕዋፍን፥ በአራተኛዪቱ ቀን በምድር ላይ የሚንቀሳቀሰውን ሁሉ፥ በአምስተኛዪቱም ቀን በውኃ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ሁሉ። አዳምም ሁሉን በየስማቸው ጠራቸው፤ ስማቸውም አዳም እንደ ጠራቸው እንዲሁ ሆነ። 3 በእነዚህም በአምስቱ ቀኖች አዳም እነዚህን ሁሉ፥ በምድር ያለውንም ፍጥረት ሁሉ ሴትና ወንድ ሆነው ያይ ነበር። እርሱ ግን ብቻውን ነበረ። እንደ እርሱ ያለ ረዳትንም ለራሱ አላገኘም ነበር። 4 እግዚአብሔርም ለእኛ እንዲህ አለን፥ “አዳም ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ ነገር ግን እንደ እርሱ ያለ ረዳትን እንፍጠርለት።” አምላካችን እግዚአብሔርም በእርሱ ላይ እንቅልፍን አመጣበት፤ እርሱም ተኛ። 5 ከአጥንቶቹም መካከል አንድ አጥንት ወስዶ ሴትን ፈጠራት። ይህችም ጎን ከአጥንቶች መካከል የሴት መገኛ ናት፤ ስለ እርስዋም ፋንታ ሥጋን ሞላ። ሴትም አድርጎ ፈጠራት። አዳምንም ከእንቅልፉ አነቃው። 6 አዳምም በስድስተኛዪቱ ቀን ከእንቅልፉ ነቅቶ በተነሣ ጊዜ ወደ እርሱ አመጣት፥ ዐወቃትም። እርሱም፥ “ከእኔ ከባልዋ ተገኝታለችና ይህች አጥንት ከአጥንቴ፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋም ሚስት ትሁነኝ” አላት። ስለዚህ ባልና ሚስት አንድ አካል ይሆናሉ። 7 ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፥ አንድ አካልም ይሆናሉ። 8 በመጀመሪያዪቱ ሱባዔ አዳም ተፈጠረ፤ ሚስቱም የተገኘችበት ጎኑ ተፈጠረ፤ በሁለተኛዪቱም ሱባዔ እርስዋን አሳየው፤ ስለዚህም በሕርስ ጊዜ ለወንድ ልጅ አንድ ሱባዔ፥ ለሴት ልጅ ሁለት ሱባዔ የመጠበቅ ትእዛዝ ተሰጠ። 9 በተፈጠረባትም ምድር ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ያበጃትና ይጠብቃት ዘንድ ወደ ኤዶም ገነት አስገባነው። ሚስቱንም በሰማንያኛው ቀን አስገባናት። 10 ከዚህም በኋላ ወደ ኤዶም ገነት ገባች፤ ስለዚህ ለምትወልድ ሴት በጽላተ ሰማይ ሥርዐት ተጻፈ። ወንድ ልጅ ብትወልድ እንደ መጀመሪያው ሰባት ቀን በአራስነቷ ሰባት ቀን ትቈያለች፥ ሠላሳ ሦስት ቀንም በመንጻቷ ደም ትቈያለች። 11 የተቀደሰውን ሁሉ አትንካ፤ ለወንድ ልጅ የታዘዘውን ይህን ቀን እስክትፈጽም ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ አትግባ። ሴት ልጅ ብትወልድ እንደ መጀመሪያዎቹ ሁለት ሱባዔያት በአራስነቷ ሁለት ሱባዔያት ትቈያለች። ስድሳ ስድስት ቀንም በመንጻቷ ደም ትቈያለች። ሁሉም ሰማንያ ቀኖች ይሆናሉ። 12 እነዚህንም ሰማንያ ቀኖች ከፈጸመች በኋላ ገነት ከምድር ሁሉ የተቀደሰች ናትና፥ በውስጥዋም የበቀለው እንጨት ሁሉ የተቀደሰ ነውና ወደ ኤዶም ገነት አገባናት። 13 ስለዚህም ወንድ ልጅና ሴት ልጅ ለምትወልድ ሴት የእነዚህ ቀኖች ሥርዐት ተሠራ፤ ለወንድ ልጅና ለሴት ልጅ የታዘዙ እነዚህ ቀኖች እስኪፈጸሙ የተቀደሰውን ሁሉ አትንካ፤ ወደ መቅደስም ሁሉ አትግባ። እስራኤልም በዘመኑ ሁሉ ይጠብቁት ዘንድ የተጻፈው ሕግና ሥርዐት ይህ ነው። 14 በመጀመሪያው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያ ሱባዔ አዳምና ሚስቱ በኤዶም ገነት ሰባት ዓመት ሲሠሩና ሕጉን ሲጠብቁ ኖሩ። ሥራንም ሰጠነው፤ ለማገልገልም ተገልጦ የሚታየውን ሥራ ሁሉ እያስተማርነው ኖርን፤ እርሱም እየሠራ ኖረ። 15 እርሱ ግን ዕራቁቱን ነበረ፤ ዕራቁቱንም እንደ ሆነ አያውቅም ነበር፥ አያርፍምም ነበር። ተክልንም ከወፎችና ከአራዊት፥ ከእንስሳትም ይጠብቅ ነበር። 16 ፍሬውንም ለቅሞ ይበላ ነበር፥ የተረፈውንም ለእርሱና ለሚስቱ ያኖር ነበር፤ የሚጠብቀውንም ያኖር ነበር፤ ሰባቱን ዓመት ጠንቅቆ ቈጥሮ በዚያ የፈጸማቸው የሰባቱ ዓመት ፍጻሜ ባለቀ ጊዜ፥ 17 በሁለተኛው ወር በዐሥራ ሰባተኛው ቀን እባብ መጥቶ ወደ ሔዋን ቀረበ። እባቡም ሔዋንን፥ “በገነት ካሉ ዛፎች ፍሬ ሁሉ እግዚአብሔር፦ ከእርሱ አትብሉ ብሎ አዝዞአችኋልን?” አላት። 18 እርስዋም እንዲህ አለችው፥ “እግዚአብሔር፦ በገነት ካለ ዛፍ ፍሬ ሁሉ ብሉ፥ በገነት መካከል ካለ ዛፍ ፍሬ ግን አትብሉ፥ እንዳትሞቱም አትንኩ” አለን። 19 እባብም ሔዋንን፥ “ከእርሱ በምትበሉበት ቀን ዐይኖቻችሁ እንደሚበሩ፥ አማልክትም እንደምትሆኑ፥ ክፉውንና በጎውንም እንደምታውቁ እግዚአብሔር ያውቃልና ነው እንጂ ሞትን የምትሞቱ አይደለም” አላት። 20 ሔዋንም ዛፉ ያማረ እንደ ሆነ፥ ለማየትም ደስ የሚያሰኝ፥ ፍሬውም ለመብላት የሚያስጐመጅ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ ከእርሱ ወስዳ በላች። ኀፍረቷንም በቀደመው በበለሱ ቅጠል ሸፈነች። ለአዳምም ሰጠችውና በላ። ዐይኖቹም አዩ፤ ዕራቁቱንም እንደ ሆነ ባየ ጊዜ የበለስ ቅጠል ወስዶ ሰፋ፤ ግልድም አድርጎም ኀፍረቱን ሸፈነ። 21 እግዚአብሔርም እባቡን ረገመው፤ ለዘለዓለምም ፈረደበት። 22 ሔዋንንም የእባቡን ቃል ሰምታ በልታለችና ፈረደባት፤ “ኀዘንሽንና ጣርሽን ፈጽሜ አበዛዋለሁ፤ በኀዘን ልጆችን ውለጂ፥ መመለሻሽም ወደ ባልሽ ይሁን፤ እርሱም ይግዛሽ” አላት። 23 አዳምንም፥ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ከዚያ ዛፍ በልተሃልና በአንተ ምክንያት ምድር የተረገመች ትሁን፤ እሾህና አሜከላ ይብቀልብህ፤ አንተ ከምድር ተገኝተሃልና ወደ ምድርም ትመለሳለህና ከእርስዋ ወደ ተገኘህባት ወደ ምድር እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራህን ብላ” አለው። 24 የቍርበት ልብስንም አደረገላቸው፤ አለበሳቸውም ከኤዶም ገነትም አሰናበታቸው። |