ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከዚህም ሁሉ በኋላ ሰውን ፈጠረ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ በምድር ላይና በባሕር ውስጥ ባለውም ሁሉ ላይ አሠለጠነው። በሚበርሩ አዕዋፍ ላይና በአራዊት ላይ፥ በእንስሳት ላይና በምድር ላይ በሚንቀሳቀሰው ላይ፥ በምድርም ሁሉ ላይ፥ በዚህም ሁሉ ላይ አሠለጠነው፤ በስድስተኛዪቱ ቀን እነዚህን አራት ዓይነት ፍጥረታት ፈጠረ። 2 ሁሉም ሃያ ሁለት ዓይነት ፍጥረት ሆነ፤ በስድስተኛዪቱም ቀን በሰማይና በምድር፥ በባሕሩና በጥልቁ ውስጥ፥ በብርሃንና በጨለማ መካከል፥ በሁሉም ላይ ያለውን ፍጥረት ሁሉ ፈጥሮ ፈጸመ። 3 ስድስት ቀን ሥራ ሠርተን በሰባተኛዪቱ ቀን ከሥራ ሁሉ እናርፍ ዘንድ ታላቅ ምልክት ሰባተኛዪቱን ቀን ሰጠን። 4 መላእክተ ገጽ ሁሉና የምስጋና መላእክት ሁሉ እነዚህ ሁለቱ ታላላቅ ወገኖች ናቸው። ከእርሱም ጋር በሰማይና በምድር ይህን እናከብር ዘንድ አዘዘን። 5 እንዲህም አለን፥ “እነሆ፥ እኔ ከአሕዛብ መካከል ሕዝብን እለያለሁ፤ እነርሱም ሰንበትን ያከብራሉ። ለእኔም ሕዝብ አድርጌ እለያቸዋለሁ፤ የሰንበትንም ቀን እንደ ቀደስኋት እባርካቸዋለሁ። ለእኔም እለያቸዋለሁ። 6 እንዲህም እባርካቸዋለሁ። ሕዝቤም ይሆናሉ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ በሁሉም ካየሁት የያዕቆብን ዘር መረጥሁ፥ ለእኔም የበኵር ልጅ አድርጌ ጻፍሁት፤ ለዘለዓለምም ቀደስሁት። 7 “ከሥራ ሁሉ ያርፉባት ዘንድ የሰንበታትን ቀን አመለክታቸዋለሁ። እንደዚሁም በዓል ያከብሩባት ዘንድ ምልክት አደረግሁባት። 8 እነርሱም በሰባተኛዪቱ ቀን ለመብላትና ለመጠጣት፥ ሁሉን የፈጠረ እግዚአብሔርንም ለማመስገን ከእኛ ጋር ነበሩ። ከእኛ ጋርም በአንድነት ያርፉ ዘንድ ከአሕዛብ ሁሉ ተለይቶ የሚታይ ሕዝብን ባረከ፥ ቀደሰም። 9 በዘመኑ ሁሉ በፊቱ የሚቀበለው በጎ መዓዛ ያርግ ዘንድ በፊቱ መሥዋዕትን ሠዋ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ያዕቆብ ድረስ ያሉ አበው ሃያ ሁለት ናቸው። እስከ ሰባተኛዪቱም ቀን ድረስ ሃያ ሁለት ዓይነት ፍጥረት ተፈጠረ። ይህም የተባረከና የተቀደሰ ሰንበቱ ነው። እርሱም ቡሩክና ቅዱስ ነው። 10 ይህም ከዚህ ጋር ለምስጋናና ለበረከት ሆነ። ቀድሞ ሰባተኛው ቀን እንደ ተቀደሰና እንደ ተባረከ በዘመኑ ሁሉ ለምስክሩና ለሕጉ የተባረኩና የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ ይህ ለእርሱ ተሰጠው። 11 “በመጀመሪያዪቱ ሱባዔ ሰማይንና ምድርን፥ በስድስት ቀን የተፈጠረውንም ፍጥረት ሁሉ ፈጠረ። እግዚአብሔርም ለፍጥረቱ ሁሉ የተቀደሰች የበዓል ቀንን ሰጠ። ስለዚህም ሥራን ሁሉ የሚሠራባት ሁሉ ይሞት ዘንድ፥ የሚሽራትም ሞትን ይሞት ዘንድ አዘዘ። 12 አንተም የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፥ እነርሱም እንዲያከብሯት፥ ሥራንም ሁሉ እንዳይሠሩባት፥ እንዳይሽሩአትም፥ ያችን ዕለት ይጠብቁ፤ ከዕለታት ሁሉ እርስዋ የተቀደሰች ናትና። 13 የሚያረክሳትም ሁሉ ሞትን ይሙት፤ ሥራንም የሚሠራባት ሁሉ ለዘለዓለሙ ሞትን ይሙት። የእስራኤልም ልጆች ከምድር እንዳይጠፉ በትውልዳቸው ይህችን ቀን ይጠብቁ። የተባረከችና የተቀደሰች ናትና። 14 የሚጠብቃት ሰው ሁሉ፥ ከሥራውም ሁሉ የሚያርፍባት ሰው በዘመኑ ሁሉ እንደ እኛ የተቀደሰና የተባረከ ይሆናል። 15 “ለእስራኤል ልጆች፦ የዚህችን ቀን ፍርድ አስረድተህ ንገር፤ ያክብሯትም፤ የማይገባ ሥራን ለመሥራትም የተዘጋጁ እንዳይሆኑ በልቡናቸው ስሕተት አይተዉአት፤ የሚታየውን ፈቃዳቸውንም በእርስዋ ለማድረግ የሚበላውንና የሚጠጣውን ሁሉ ያዘጋጁባት ዘንድ፥ 16 ውኃንም ለመቅዳት፥ በአደባባያቸውም ሸክሙን ሁሉ ለማግባትና ለማውጣት፥ እነርሱ በስድስት ቀን በቤታቸው ያላዘጋጁትን ሥራ አይሥሩ። 17 በኢዮቤልዩ ከሚቈጠር ቀን ሁሉ ተለይታ የከበረች ናትና በዚህች ቀን ከቤት ወደ ቤት አያውጡባት፥ አያግቡባትም። በምድር ዕረፍት ያደርጉባት ዘንድ ለሥጋዊ ሁሉ ሳይታወቅ እኛ በሰማያት ዕረፍትን አደረግንባት።” 18 የሁሉ ፈጣሪም ባረካት፤ ከእስራኤልም ብቻ በቀር በእርስዋ ዕረፍት ለማድረግ አሕዛብን ሁሉ አልመረጠም፤ ነገር ግን በልቶና ጠጥቶ በምድር ዕረፍትን ሊያደርግባት ለእርሱ ብቻ ሰጠው። 19 ከቀኑ ሁሉ ተለይታ ለበረከትና ለቅድስና ለማመስገኛም ልትሆን ይህችን ቀን የፈጠረ የሁሉ ፈጣሪ ባረካት፤ ይህ ሕግ፥ ይህም ምስክር ለእስራኤል ልጆችና ለትውልዳቸውም ለዘለዓለም ሥርዐት ሆኖ ተሰጠ። |