ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በእስራኤል ሠራዊት ፊት የሚሄድ መልአከ ገጹም የዘመኖች አከፋፈል የተጻፈበትን ጽላት ያዘ። 2 ይኸውም ለሕግና ለምስክርነት በሱባዔ የሚቈጠረው የዘመኑ አከፋፈል ከዓለም ፍጥረትና አዲስ ፍጥረት ከተፈጠረበት ቀን ጀምሮ፥ ሰማያትና ምድር፥ ፍጥረታቸውም ሁሉ የሰማይ ሠራዊት እንደ መሆናቸው እስኪታደሱ ድረስ ያለው የተጻፈበት ነው። 3 የምድር ፍጥረት ሁሉ እንደ መሆናቸውም የእግዚአብሔር መቅደስ በኢየሩሳሌምና በደብረ ጽዮን እስኪሠራ ድረስ፥ ብርሃናትም ሁሉ ከእስራኤል ለተመረጡ ሰዎች ሁሉ ለደኅንነት፥ ለሰላምና ለበረከት ሊሆኑ እስኪታደሱ ድረስ፥ ከዚህች ቀን ጀምሮ እስከ ምድር ዘመን ሁሉ እንደዚሁ ይሆን ዘንድ የሚደረገው ሁሉ የተጻፈበት ነው። 4 መልአከ ገጹም በእግዚአብሔር ቃል ሙሴን እንዲህ አለው፥ “እግዚአብሔር አምላክ በስድስተኛው ቀን ፍጥረቱን ሁሉ ፈጥሮ እንደ ጨረሰ፥ የፍጥረትን ነገር ሁሉ ጻፍ፤ 5 በሰባተኛዪቱም ቀን እንዳረፈ፥ ከዕለታቱም ሁሉ እንደ ለያት፥ ለሥራውም ሁሉ ምልክት አድርጎ እንዳኖራት ጻፍ። በመጀመሪያዪቱ ቀን በላይ ያሉ ሰማዮችን ፈጥሮአልና፤ ምድርንና ውኃዎችንም፥ በፊቱ የሚያገለግል ፍጥረትንም ሁሉ ፈጥሮአልና። 6 መላእክተ ገጽንም፥ የሚያመሰግኑ መላእክትንም፥ በእሳት አካል ላይ የተሾሙ መላእክትንም፥ በነፋስ አካል ላይ የተሾሙ መላእክትን፥ በብርሃንና በጨለማ አካል ላይ የተሾሙ መላእክትንም፥ በበረድና በውርጭ አካል ላይ የተሾሙ መላእክትንም፥ 7 በውኃ ላይ የተሾሙ መላእክትን፥ በነጐድጓድና በመብረቅ ላይ የተሾሙ መላእክትን፥ በቍርና በውርጭ፥ በክረምትና በመጸው፥ በጸደይና በበጋ፥ በሰማይና በምድር ባሉ ነፋሳት ሁሉ የተሾሙ መላእክትን፥ በወንዙ ሁሉ፥ በጨለማና በብርሃን፥ በንጋትና በምሽት በባሕርይ ዕውቀቱ ባዘጋጃቸው ላይ የተሾሙ መለእክትን ፈጥሮአልና።” 8 ያንጊዜም ሥራውን አይተን ስለ ሠራው ሥራ ሁሉ በፊቱ ፈጽመን አመሰገንነው፤ በመጀመሪያዪቱ ቀን ሰባት ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶአልና። 9 በሁለተኛዪቱም ቀን በሐኖስና በውቅያኖስ መካከል ጠፈርን አድርጎአልና፤ በዚያችም ቀን ውኃዎች ተከፍለው እኩሌቶቹ ወደ ላይ ወጥተዋልና፤ እኵሌቶቹ ከጠፈር በታች ወዳለው ወደ ምድር መካከል ወርደዋልና፤ በሁለተኛው ቀን ይህን ሥራ ብቻ ሠራ። 10 በሦስተኛዪቱም ቀን፥ “ውኃዎች ከምድር ላይ ወደ አንዱ ቦታ ሄደው ይወሰኑ፥ ምድርም ትገለጥ” ብሎ እንደ ተናገረው አድርጎአልና። 11 ውኃዎችም እንዳዘዛቸው እንደዚሁ ተዘጋጁ። ከምድር ፊት ወደ አንድ ቦታ ሄደው ከዚህ ከጠፈር በታች በውቅያኖስ ተወሰኑ፤ ምድርም ተገለጠች። 12 በዚያችም ቀን በየመወሰኛቸው የባሕር ጥልቆችን ፈጠረላት፤ ፈሳሾችንም ሁሉ፥ የውኃዎችንም መወሰኛዎች፥ በተራራዎች ሥር በምድር ውስጥ ምንጮች ሁሉና በተራራዎች ሥር ያሉ የውኃዎችን መወሰኛዎች ሁሉ፥ በምድር ያሉ የውኃዎችንም ጕድጓድ ሁሉ ፈጠረላት። በየዘሩም የሚዘራውን ዘር፥ የሚበላውንም ዘር ሁሉ፥ የሚያፈሩ እንጨቶችንና ዛፎችንም፥ በገነትም ለተድላ የተፈጠሩ ተክሎችን፥ በሦስተኛዪቱ ቀን እነዚህን አራቱን ታላላቆች ፍጥረቶች ፈጠረ። 13 በአራተኛዪቱም ቀን ጨረቃንና ፀሓይን፥ ከዋክብትንም ፈጥሮ በዓለሙ ሁሉ ያበሩ ዘንድ በጠፈር አኖራቸው። ሌሊትንና ቀንንም አስገዛቸው፤ በብርሃንና በጨለማ መካከልም ለመለየት ድንበር አደረጋቸው። 14 እግዚአብሔርም በምድር ላይ ለቀኖችና ለሱባዔዎች፥ ለወሮችና ለበዓሎች፥ ለዓመታትና ለኢዮቤላት፥ በዓመት ለሚመላለሱ ሰዓቶችም ሁሉ ታላቅ ምልክት እንዲሆን፥ በብርሃንና በጨለማ መካከልም ድንበርን እንዲለይ፥ በምድርም ላይ የሚበቅለውና የሚያድገው ሁሉ ይድን ዘንድ፥ ለማዳን ፀሐይን ፈጠረ፤ በአራተኛዪቱ ቀን እነዚህን ሦስቱን ፍጥረቶች ፈጥረ። 15 በአምስተኛዪቱም ቀን በጥልቅ ውኃዎች መካከል ያሉትን ታላላቅ ዓሣ አንበሪዎች ፈጠረ። ይህ ሁሉ መጀመሪያ በእጁ ተፈጥሮአልና፤ ሥጋዊ ደማዊ ሁሉ፥ በውኃዎችም ውስጥ የሚመላለስ ፍጥረት ሁሉ፥ ዓሣዎችና የሚበሩ ወፎች ሁሉ፥ ወገኖቻቸውም ሁሉ ተፈጥረዋልና፤ 16 ፀሓይም ሕይወት ሊሆናቸው በእነርሱ ላይ ወጥቶአልና፥ በዚህ ዓለም በሚኖር ፍጥረትና በምድር በሚበቅለው ሁሉ ላይ፥ በሚያፈራውም እንጨት ሁሉ ላይ፥ በሥጋዊ ደማዊ ሁሉ ላይ ወጥቶአልና፤ በአምስተኛዪቱ ቀን እነዚህን ሦስቱን ፍጥረታት ሁሉ ፈጠረ። 17 በስድስተኛዪቱም ቀን እንስሳትንና አራዊትን ሁሉ በምድር ላይ የሚመላለሰውንም ፍጥረት ሁሉ ፈጠረ። |