ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከዚህ ነገር በኋላ በዚህ ሱባዔ በአራተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር መባቻ፥ “አብራም፥ አትፍራ፤ ጠበቃህ እኔ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ይበዛል፥” ሲል የእግዚአብሔር ቃል በሕልም ወደ አብራም መጣ። 2 እርሱም እንዲህ አለ፥ “አቤቱ፥ ምን ትሰጠኛለህ? እኔ ልጅ ሳልወልድ እሄዳለሁ፤ የደማስቆ ሰው የሚሆን የአማቲየል ልጅ የማሴቅ ልጅ ኤልኤዘር እርሱ ይወርሰኛል፤ ለእኔ ግን ልጅ አልሰጠኸኝም፤ ልጅ ስጠኝ።” 3 እርሱም፥ “ከአብራክህ የሚወለድ ልጅ እርሱ ይወርስሃል እንጂ ይህ አይወርስህም” አለው። 4 ወደ ውጭም አውጥቶ፥ “ወደ ሰማይ ተመልከት፤ መቍጠር ይቻልህ እንደ ሆነ ከዋክብትን ቍጠር” አለው። ሰማይን አየ፤ ከዋክብትንም ተመለከተ፤ እርሱም፥ “ዘርህ እንደዚህ ይሆናል” አለው። እግዚአብሔርንም አመነው፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት። 5 “ለዘለዓለም ይዘሃት ልትኖር ለአንተም ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ልትሆን የከነዓናውያንን ሀገር እሰጥህ ዘንድ የከላውዴዎን ዕጣ ከምትሆን ከዑር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” አለው። 6 እርሱም፥ “አቤቱ አቤቱ፥ እንደምወርሳት በምን አውቃለሁ?” አለ። 7 እርሱም፥ “የሦስት ዓመት ወይፈን፥ የሦስት ዓመት ፍየል፥ የሦስት ዓመት በግ፥ ዋኖስና ርግብንም አምጣልኝ” አለው። 8 ይህንም ሁሉ በወር እኩሌታ አመጣ። እርሱ ግን የኬብሮን አቅራቢያ በምትሆን በመምሬ ባለ ግራር ሥር ተቀምጦ ነበር። 9 በዚያም መሠዊያን ሠራ፥ ይህንም ሁሉ ሠዋ፤ በመሠዊያውም ላይ ደማቸውን አፈሰሰ፤ ከሁለት ከሁለትም አደረጋቸው፤ በየመልካቸውም በአንጻራቸው አኖራቸው፤ አዕዋፍን ግን ጨርሶ አልቈረጣቸውም። ወፎችም ወደ መሥዋዕቱ ይወርዱ ነበር። 10 አብራም ግን ይከለክላቸው ነበር፤ ወፎችም ይበሉአቸው ዘንድ አልተወም ነበር። 11 ፀሐይም በገባ ጊዜ እንዲህ ሆነ፥ በአብራም እንቅልፍ መጣበት ፤ እነሆም፥ የሚያስፈራ ጽኑ ጨለማ በላዩ ወደቀበት። 12 ለአብራምም እንዲህ ተብሎ ተነገረ፥ “ዘርህ በአሕዛብ ሀገር ስደተኞች እንደሚሆኑ፥ አራት መቶ ዓመትም እንደሚገዙአቸውና መከራ እንደሚያጸኑባቸው ፈጽመህ ዕወቅ፤ የሚገዙአቸውንም ወገኖች እኔ እፈርድባቸዋለሁ። 13 ከዚህ በኋላ ከብዙ ገንዘብ ጋር ከዚያ ይወጣሉ። አንተም ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ በበጎ እርግናም ትቀበራለህ። 14 በአራተኛው ትውልድ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ እስከ ዛሬ ድረስ የአሞራውያን ኀጢአት አልተፈጸመምና።” 15 ከእንቅልፉም ነቅቶ ተነሣ፤ ፀሐይም ገባ፤ እሳትም ይነድ ጀመር፤ እነሆ፥ ምድጃው እየጤሰ የእሳቱ ነበልባል በመሠዊያው መካከል አለፈ። 16 በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ከአብራም ጋር እንዲህ ሲል ቃል ኪዳን አደረገ፥ “ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ፤ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ፥ ይህችን ሀገር ለልጆችህ እሰጣለሁ፤ የቄኔዎስንና የቄኔዜዎስን፥ የቀድሞኔዎስን፥ የፌርዜዎስንና የራፋይምን፥ የፌኮሬዎስን፥ የኤዌዎስንና የአሞሬዎስን፥ የከናኔዎስንና የጌርጌሴዎስን፥ የኢያቡሴዎስንም ሀገር እሰጥሀለሁ።” 17 አብራምም ሄዶ መሠዊያውን አዘጋጀ፤ አዕዋፍንና መሥዋዕታቸውን፥ ወይናቸውንም አቀረበ፤ እሳትም በላው። 18 በዚያችም ወር ከኖኅ ጋር ቃል ኪዳን እንደ አደረግን በዚችም ዕለት ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን አደረግን። 19 አብራምም ይህችን በዓልና ሥርዐቷንም እስከ ዘለዓለም ድረስ ለራሱ አጸናት፤ አብራምም ደስ አለው፤ ይህንም ነገር ሁሉ ለሚስቱ ለሶራ ነገራት፤ ልጅ እንደሚወለድለትም አመነ። እርስዋ ግን ልጅ አትወልድም ነበር፤ ሶራም ባልዋን አብራምን መከረችው፦ “ከእርስዋ የሚወለደውን ልጅ አሳድግልሃለሁና ወደ ግብፃዊቱ አገልጋዬ ወደ አጋር ግባ” አለችው። 20 አብራምም የሚስቱ የሶራን ቃል ሰማ፥ “እንዳልሽ አድርጊ” አላት። ሶራም ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን አምጥታ ሚስት ትሆነው ዘንድ ለባልዋ ለአብርሃም ሰጠቻት። 21 ወደ እርስዋም ገባ፥ ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች። በዚህ ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት ስሙን ይስማኤል ብሎ ጠራው። በዚያም ዓመት የአብራም ዕድሜ ሰማንያ ስድስት ዓመት ነበር። 22 በዚህ ኢዮቤልዩ በአራተኛው ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በወሩ እኩሌታ መጀመሪያ ስለ ደረሰው የስንዴ አዝመራ አብራም በዓልን አደረገ። 23 በመሠዊያውም ላይ የእህሉን መጀመሪያ አዲስ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ወይፈኑንና የበጉን ሙክት፥ በጉንም በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር አቀረበ። መሥዋዕታቸውንና ወይናቸውንም ከነጭ ዕጣን ጋር አቀረበ። 24 እግዚአብሔርም ለአብራም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥ “ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ። በፊቴ የምትወደድ ሁን፤ ፍጹምም ሁን፤ በእኔና በአንተ መካከልም ቃል ኪዳን እሰጣለሁ፤ እጅግም አከብርሃለሁ።” 25 አብራምም በግንባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “እነሆ፥ ሥርዐቴ ከአንተ ጋር ነው፤ ለብዙ አሕዛብም አባት አደርግሃለሁ። 26 እንግዲህ ወዲህ ስምህ አብራም አይባል፤ የብዙ ሕዝብ አባት አድርጌሃለሁና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ስምህ አብርሃም ይባል። አንተንም በአሕዛብ መካከል ፈጽሜ አከብርሃለሁ፤ ነገሥታቱም ከአንተ ይወለዳሉ። 27 በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በልጆችህ መካከል በወገናቸው የዘለዓለም ሥርዐት ልትሆን፥ ቃል ኪዳኔን አጸናለሁ፤ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ ለዘለዓለም በምትገዛት፥ ተሰደህ በሄድህባት በከነዓን ቃል ኪዳኔን አጸናለሁ፤ አምላካቸውም እሆናቸዋለሁ።” 28 እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፥ “አንተ ቃል ኪዳኔን ጠብቅ፤ ከአንተም በኋላ ልጆችህ ይጠብቁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ሁሉ ትገዝራላችሁ፤ የሰውነታችሁንም ሸንኮፍ ሁሉ ትገዝራላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከልም ለልጅ ልጅ ለዘለዓለም የኪዳኔ ምልክት ይሆናል። 29 በስምንተኛውም ቀን ወንድ ልጅን ሁሉ በየወገናችሁ ትገዝራላችሁ። በቤት የተወለደው፥ ከአሕዛብም ልጆች ሁሉ በወርቅ የገዛችሁት፥ ከዘርህም ያይደለ ቢሆን ይገዘሩ፤ በቤትህ የተወለደም፥ በወርቅህም የገዛኸው ቢሆን ይገዘሩ። 30 ለዘለዓለም ሥርዐቴ ሊሆን ቃል ኪዳኔ በሰውነታችሁ ጸንቶ ይኖራል። ግዙር ያልሆነ ወንድ ልጃችሁ ሁሉ፥ በስምንተኛዪቱም ቀን የሰውነቱን ሰንኮፍ ያልተገዘረ ሁሉ ቃል ኪዳኔን አፍርሶአልና ያ ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ።” 31 እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፥ “ሚስትህ ሶራ ስምዋ ሳራ ነውና ከእንግዲህ ወዲያ ስምዋ ሶራ ተብሎ አይጠራ፤ እባርካታለሁ፤ ከእርስዋም ልጅ እሰጥሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ታላቅ ወገንም ይሆናል፤ የአሕዛብ ነገሥታትም ከእርሱ ይወለዳሉ።” 32 አብርሃምም በግንባሩ ወደቀ። ደስ ብሎትም በልቡ እንዲህ አለ፥ “በመቶ ዘመኔ ልጅ እወልዳለሁን? ዘጠና ዓመት የሆናት ሳራስ ልጅ ትወልዳለችን?” 33 አብርሃምም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፥ “ይስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር።” 34 እግዚአብሔርም አለው፥ “ይሁን፥ ሳራም ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ቃል ኪዳኔንም የዘለዓለም ቃል ኪዳን ሊሆን ከእርሱ ጋር አጸናለሁ፤ ከእርሱም በኋላ ለልጆቹ አጸናለሁ። 35 ስለ ይስማኤልም ሰማሁህ፤ እነሆ፥ እባርከዋለሁ፥ አገነዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ ዐሥራ ሁለት መሳፍንትንም ይወልዳል፤ በታላቅም ሕዝብ ላይ እሾመዋለሁ። 36 ቃል ኪዳኔን ግን በዚህ ወራት በሁለተኛው ዓመት ሳራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አጸናለሁ።” ከእርሱም ጋር ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃም ካለበት ወጣ። 37 አብርሃምም እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ ልጁ ይስማኤልንና በቤት የተወለደውን ሁሉ፥ በወርቁ የገዛውንም፥ በቤቱም ያለ ወንድ ልጅን ሁሉ ወስዶ የሰውነታቸውን ሰንኮፍ ገረዘ። 38 በዚህችም ቀን አብርሃም ተገረዘ፤ ቤተ ሰቦቹም፥ በወርቅ የገዛቸውም ሁሉ፥ ከአሕዛብም የተወለዱ ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ። ይህም ሕግ ለልጅ ልጅ ሁሉ የዘለዓለም ነው። 39 ይህ የዘለዓለም ሥርዐት ነውና፥ በሰማይ ጽላትም ተጽፎአልና ቀን ማሳጠር የለም፤ ከስምንቱ ቀንም አንዲት ቀን መተላለፍ የለም። 40 እስከ ስምንት ቀንም ድረስ የሰውነቱን ሰንኮፍ ያልተገረዘ ሰው ሁሉ ከጥፋት ልጆች ወገን ነውና እግዚአብሔር ለአብርሃም ከገባው ቃል ኪዳን ልጆች ወገን አይደለም። 41 ለእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ ምልክት የለውም፤ የአምላካችን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ስላፈረሰ ከምድር ለመጥፋትና ለመደምሰስ፥ ከምድርም ለመነቀል የተገባ ነውና። መላእክተ ገጽ ሁሉና የምስጋና መላእክት ሁሉ ከተፈጠሩበት ቀን ጀምሮ ተፈጥሮአቸው እንዲህ ነውና። 42 በመላእክተ ገጽና በምስጋና መላእክት አንጻር ከእርሱ ጋርና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ይሆኑ ዘንድ እስራኤልን ቀደሰው። 43 አንተም የእስራኤልን ልጆች እዘዝ፤ የዚህን ቃል ኪዳኔንም ምልክት ይጠብቁ፤ ለልጆቻቸውም የዘለዓለም ሥርዐት ይሁን፤ ለዘለዓለም በእስራኤል ልጆች ሁሉ ላይ ይጠብቁት ዘንድ ለቃል ኪዳን ሥርዐት ሠርቶአልና ከምድር እንዳይጠፉ ይሁኑ። ይስማኤልንና ልጆቹን፥ ወንድሞቹንና ዔሳውንም እግዚአብሔር ወደ እርሱ አላቀረባቸውም፤ ምንም የአብርሃም ልጆች ቢሆኑና ቢወድዳቸውም እነርሱን አልመረጠም። 44 ሕዝብ ይሆኑት ዘንድ እስራኤልን ለይቶ መረጠ። ብዙ አሕዛብና፥ ብዙ ሕዝብ ሁሉ የእርሱ ናቸውና፥ ሁሉም ለእርሱ ይገባልና ከሰው ልጆች ሁሉ ለይቶ ሰበሰበው። ነገር ግን ከእርሱ በኋላ ያስቱአቸው ዘንድ መናፍስትን በሁሉ ላይ አሠለጠነ። 45 በእስራኤል ላይ ግን ገዢአቸው እርሱ ብቻ ነውና፥ መልአክም ቢሆን መንፈስም ቢሆን ማንንም አላሠለጠነም። እርሱም ይጠብቃቸዋል። ከመላእክትና ከመናፍስት እጅ፥ ከሥልጣናትም ሁሉ እጅ ይጠብቃቸው ዘንድ ይመራመራቸዋል። እነርሱ ልጆቹ ይሆኑት ዘንድ እርሱም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ አምላክ ይሆናቸው ዘንድ ይባርካቸዋል። 46 አሁንም የእስራኤል ልጆች ይህችን ሥርዐት ሐሰት እንደሚያደርጉ እኔ እነግርሃለሁ። በሰውነታቸው ከመገረዛቸው የተነሣ ልጆቻቸውን ሳይገርዙ ይቀራሉና፤ የቤልሆርም ልጆች ሁሉ ልጆቻቸውን እንደ ተወለዱ ሳይገርዙ ይተዋሉ። 47 ቃል ኪዳኑን አፍርሰዋልና፥ ከቃሉም ወጥተዋልና ያች ጽኑ መዓት ከእግዚአብሔር ታዝዛ በእስራኤል ልጆች ትደረጋለች። የዚህንም ምልክት ሥርዐቱን እንዳልፈጸሙ ከምድር ፈጽሞ ለመጥፋት ሰውነታቸውን እንደ አሕዛብ አድርገዋልና ተበሳጭተው ተሳደቡ። 48 በዚችም ምድር ለሚሠራው ስሕተት፥ ኀጢአትም ሁሉ ፈጽሞ ይሰረይ ዘንድ እንግዲህ ወዲህ የኀጢአት ስርየትና ይቅርታ የላቸውም። 49 በአራተኛው ወር መባቻ በመምሬ ባለው በግራሩ ሥር ለአብርሃም ተገለጥንለት፤ ከእርሱም ጋር ተነጋገርን። ከሚስቱ ከሳራም ልጅ እንደሚሰጠው ነገርነው፤ ሳራም ይህን ነገር ከአብርሃም ጋር እንደ ተነጋገርን ሰምታለችና ሳቀች። እኛም ዘለፍናት፤ እርስዋም ፈርታ ስለ ተነገረው ነገር እንደ ሳቀች አስተባበለች። 50 የልጅዋንም ስም ስሙ ይስሐቅ ተብሎ በሰማይ ጽላት እንደ ተሠራና እንደ ተጻፈ ነገርናት። ያንጊዜም ወደ እርስዋ በተመለስን ጊዜ እርስዋ ወንድ ልጅን ፀነሰች። 51 በዚያም ወር እግዚአብሔር በገሞራና በሰዶም፥ በሰቡኢምና በዮርዳኖስ አውራጃ ሁሉ ፍርዱን አደረገ። በእሳትና በድኝ አቃጠላቸው፤ እጅግ ክፉዎችና ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ በሰውነታቸውም እየሴሰኑ እንደሚረክሱ፥ በምድር ላይም ርኵሰትን እንደሚሠሩ፥ እነሆ፥ ሥራቸውን ሁሉ እንደ ነገርሁህ እስከዚህች ቀን ድረስ አጠፋቸው። 52 እንደዚሁም እግዚአብሔር እንደ ሰዶም ርኵሰት በሠሩባቸው ቦታዎች ሁሉ እንደ ሰዶም ፍርድ ያደርጋል። 53 እግዚአብሔርም አብርሃምን አስቦታልና ሎጥን አዳነው፤ ከጥፋትም መካከል አወጣው። ከአዳም ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ በምድር ላይ ያልተደረገ ኀጢአትን እርሱ ከልጆቹ ጋር በምድር አደረገ፤ አባት ከልጁ ጋር ተኝቶአልና። 54 ያጠፋቸውና ይነቅላቸው፥ ቅጣታቸውንም እንደ ሰዶም ቅጣት ያደርግ ዘንድ፥ በፍርድ ቀንም በምድር የሰውን ዘር ሁሉ እንዳያስቀርለት፥ እነሆ፥ ታዘዘ። በልጆቹም ሁሉ ላይ በሰማይ ጽላት ተቀረፀ። 55 በዚህም ወር አብርሃም ከኬብሮን ተጕዞ ሄዶ በጌራሮን ተራሮች ባሉ በቃዴስና በሱር መካከል ተቀመጠ። 56 በአምስተኛው ወር እኩሌታም ከዚያ ተጕዞ በመሐላ ጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። |