ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 አብራም በሕይወት በኖረበት በስድሳኛው ዓመት፥ ይኸውም በአራተኛው ሱባኤ በአራተኛው ዓመት፥ አብራም ሌሊት ተነሥቶ የጣዖታቱን ቤት አቃጠለ። በቤት ያለውንም ዕቃ ሁሉ አቃጠለ። ያወቀ ሰው ግን አልነበረም። 2 በሌሊትም ተነሥተው ጣዖቶቻቸውን ከእሳት ውስጥ ያወጡ ዘንድ ወደዱ። 3 አራንም ያድናቸው ዘንድ ተወረወረ፤ በላዩም እሳት ነደደበት፤ በእሳትም ተቃጥሎ የከላውዴዎን ዕጣ በምትሆን በዑር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ። የከላውዴዎን ዕጣ በምትሆን በዑርም ቀበሩት። 4 ታራም የከላውዴዎን ዕጣ ከምትሆን ከዑር ወጣ። እርሱና ልጆቹ ወደ ሊባኖስ ምድርና ወደ ከነዓን ምድር፥ ወደ ካራንም ምድር ይመጡ ዘንድ ወጣ። 5 አብራምም ከአባቱ ጋር በካራን ሁለት የዓመቶች ሱባዔ ተቀመጠ። 6 በስድስተኛው ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት አብራም ተነሣ፤ በሰባተኛው ወር መባቻ ከማታ እስከ ጥዋት ድረስ ከዋክብትን ይቈጥር ዘንድና ስለ ዝናም የዓመቱ ጠባይ ምን እንደሚሆን ያይ ዘንድ በሌሊት ወጥቶ ተቀመጠ። 7 ብቻውንም ተቀምጦ ይቈጥር ነበር፥ ቃልም ወደ ልቡ መጣ፤ “የከዋክብት ምልክት ሁሉ፥ የፀሐይና የጨረቃም ምልክት ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ ነው። ጥዋትም ማታም ያዘንብ ዘንድ ቢወድ፥ እንዳያዘንብም ቢወድ እኔ ለምን እመራመራለሁ? ሁሉም በእጁ ነው” አለ። 8 በዚህችም ሌሊት ጸለየ፥ እንዲህም አለ፥ “አምላኬ አምላኬ ሆይ፥ ልዑል አምላክ፥ አንተ ብቻ ለእኔ አምላክ ነህ፤ አንተ ሁሉን ፈጠርህ፤ የእጅህ ፍጥረት ሁሉ ጸንቶ ይኖራል፤ እኔ አንተንና መንግሥትህን ወደድሁ፤ ከክፉዎች በሰው ልቡና ከሚሠለጥኑ ከመናፍስት እጅ አድነኝ፤ አምላኬ ሆይ፥ አንተን ከመከተል አያስቱኝ፤ እኔንም ዘሬንም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ለዘለዓለም እንዳንስት አድርገን። 9 ወደ እነርሱም እመለስ ዘንድ ፊቴን ወደሚሹ ወደ ከላውዴዎን ዑር ልመለስን? ወይስ በዚህ ቦታ ልቀመጥ? ያገለግል ዘንድ በባሪያህ እጅ የቀናውን መንገድ በፊትህ አቅና። አምላኬ ሆይ፥ በልቡናዬ ስሕተት አልሂድ።” 10 እርሱም ይህን ተናግሮና ጸልዮ በጨረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል በእኔ እጅ እንዲህ ሲል ወደ እርሱ ተላከ፥ “አንተ ከሀገርህ፥ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤት ወጥተህ እኔ ወደማሳይህ ሀገር ሂድ፤ እጅግም ብዙ ወገን አደርግሃለሁ፤ እባርክህማለሁ፤ ስምህንም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤ በምድሩም ሁሉ የተባረክህ ትሆናለህ። 11 የምድር አሕዛብም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤ የሚመርቁህን እመርቃቸዋለሁ፤ የሚረግሙህንም እረግማቸዋለሁ። ለአንተና ለልጆችህ፥ ለልጅ ልጆችህም፥ ለዘርህም ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ ከአንተም በኋላ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ልጅ ልጅ ዘመን ድረስ አምላክህ እኔ ነኝና አትፍራ።” 12 እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ አለኝ፥ “ከውድቀት ቀን ጀምሮ ከሰው ልጅ ሁሉ ቋንቋ ተለይቶአልና የተገለጠች ቋንቋን ይሰማና ይናገር ዘንድ አፉንና ጆሮውን ክፈት።” 13 እኔም አፉንና ጆሮውን፥ ከንፈሩንም ከፈትሁ፤ በትውልድ ቋንቋው በዕብራይስጥ ቋንቋም ከእርሱ ጋር እናገር ጀመርሁ፤ የአባቶቹንም መጽሐፍ ወሰደ፤ እነዚያም በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፉ ነበሩ። ደግሞም ጻፋቸው፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ ይማራቸው ጀመር። የጸነነውንም ሁሉ እኔ እነግረው ነበር፤ ዝናብም በሚዘንብባቸው በስድስቱ ወሮች ተማራቸው። 14 በስድስተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት እንዲህ ሆነ፤ ከአባቱ ጋር ተነጋገረ፤ ከካራን ወደ ከነዓን ሄዶ አይቶአት ወደ እርሱ ይመለስ ዘንድ እንደሚሄድ ነገረው። 15 አባቱ ታራም እንዲህ አለው፥ “በሰላም ሂድ፤ የሰላም አምላክም ጎዳናህን ያቅናልህ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን፤ ከክፉ ሁሉ ይጠብቅህ፤ በሚያዩህ ሰዎች ፊት ቸርነትንና ይቅርታን፥ መወደድንም ይስጥህ፤ በአንተም ላይ ክፉ ነገርን ለማድረግ የሰው ልጆች ሁሉ አይሠልጥኑብህ፤ በሰላም ሂድ። 16 በእርስዋም ለመኖር ለዐይኖችህ ያማረች ምድርን ብታይ፥ መጥተህ ወደ አንተ ውሰደኝ፤ ለአንተ ልጅ ይሆንህ ዘንድ የወንድምህን የአራን ልጅ ሎጥንም ከአንተ ጋር ውሰደው፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን፤ በሰላም እስክትመለስም ድረስ ወንድምህ ናኮርን በእኔ ዘንድ ተወው፤ ሁላችንም በአንድነት ከአንተ ጋር እንሄዳለን።” 17 አብራምም ሚስቱን ሶራንና የወንድሙን የአራን ልጅ ሎጥን ይዞ ከካራን ወደ ከነዓን ሄደ። ወደ ሱርም መጣ፤ እስከ ሰቂሞንም ድረስ ተመላለሰ፤ በረጅም ግራር ሥር አደረ፤ ከኢማት መግቢያ ጀምሮ ረጅም ግራር እስካለበት ድረስ ሀገሪቱ እጅግ ያማረች እንደ ሆነች እነሆ፥ አየ። 18 እግዚአብሔርም፥ “ለአንተና ለልጆችህ ይህችን ሀገር እሰጣችኋለሁ” አለው። በዚያም መሠዊያን ሠራ፤ ለተገለጠለት ለእግዚአብሔርም በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መሥዋዕትን አቀረበ። 19 ከዚያም ተነሥቶ በምዕራብ አንጻር ወዳለች ወደ ቤቴል ተራራና በምሥራቅ አንጻር ወዳለች ወደ ጋይ ሄደ፤ በዚያም ድንኳኑን ተከለ፤ ባያትም ጊዜ፥ እነሆ፥ ሀገሪቱ ሰፊ ነበረች፤ እጅግም ያማረች ነበረች፤ ሁሉም በእርስዋ ላይ ይበቅላል፤ ወይን፥ በለስ፥ ሮማን፥ ወይራ፥ ግራር፥ ቡጥን፥ ዘይት፥ ዋንዛ፥ ሰኖባር፥ የሊባኖስም ዛፍ፥ የዱርም ዛፍ ሁሉ የሚበቅልባት ናት፤ ውኃውም በተራራው ላይ ነበር። 20 የከላውዴዎናውያን ዕጣ ከምትሆን ከዑር አውጥቶ ወደዚህ ተራራ ያመጣውን እግዚአብሔርንም አመሰገነው። 21 በሰባተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያው ወር መባቻ እንዲህ ሆነ። በዚያ ተራራ መሠዊያን ሠራ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ፥ “አንተ አምላኬ ሆይ፥ የዘለዓለም አምላክ አንተ ነህ” አለ። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ በሕይወቱም ዘመን ሁሉ እንዳይለየው በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትን አቀረበ። 22 ከዚያም ተነሥቶ ወደ ደቡብ ሄደ፤ እስከ ኬብሮንም ደረሰ። ኬብሮንም ያንጊዜ ተሠርታ ነበር። በዚያም ሁለት ዓመት ተቀመጠ። ሎጥም እስኪገባ ድረስ ወደ ደቡብ ሀገር ሄደ። 23 በምድርም ድርቅ ሆነ፤ አብራምም በዚህ ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ወደ ግብፅ ሄደ፤ ሚስቱ ከእርሱ ሳትወሰድ በግብፅ አምስት ዓመት ኖረ። የግብፅ ክፍል የምትሆን ጠናይስም ያንጊዜ ከኬብሮን በኋላ በሰባት ዓመት ተሠርታ ነበር። 24 ፈርዖንም የአብራምን ሚስት ሶራን በወሰዳት ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ ስለ አብራም ሚስት ስለ ሶራ እግዚአብሔር ፈርዖንን በደዌ ገረፈ፤ ቤተ ሰቡንም ሁሉ በጽኑ መቅሠፍት ገረፈ። 25 አብራምም በገንዘብ፥ በበጎችና በላሞች፥ በአህዮችና በፈረሶች፥ በግመሎችም፥ በወንዶች ባሪያዎችና በሴቶች ባሪያዎች፥ በብርና በወርቅ እጅግ የከበረ ነበረ። የወንድሙ ልጅ ሎጥም በገንዘብ እንደ እርሱ የከበረ ነበረ። 26 ፈርዖንም የአብራምን ሚስት ሶራን መለሰ። ከግብፅም ተነሥቶ በቤቴል ምሥራቅና በምዕራብ መካከል ወደ አለው ቀድሞ ድንኳኑን ተክሎበት ወደ ነበረው ወደ ጋይ የመሠዊያ ቦታ ሄደ። 27 በሰላም የመለሰው አምላኩ እግዚአብሔርንም አመሰገነው። 28 በአርባ አንድ ኢዮቤልዩ፥ በመጀመሪያው ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት እንዲህ ሆነ፤ ወደዚህ ቦታ ተመለሰ፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠል መሥዋዕትን አቀረበ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ፥ “ልዑል አምላክ የምትሆን አንተ እግዚአብሔር ሆይ፥ ለዘለዓለም አምላኬ ነህ” አለ። 29 በዚህ ሱባዔ በአራተኛው ዓመት ሎጥ ከእርሱ ተለየ፤ በሰዶምም ኖረ። የሰዶም ሰዎች ግን እጅግ ኀጢአተኞች ነበሩ። የወንድሙም ልጅ ከእርሱ ስለ ተለየ በልቡ አዘነ። ሎጥ በተማረከበት በዚያ ዓመት ልጅ አልነበረውምና። 30 ሎጥም ከእርሱ ከተለየ በኋላ በዚህ ሱባዔ በአራተኛው ዓመት እግዚአብሔር አብራምን አለው፥ “በዚያ ትኖር ዘንድ ካለህበት ከዚያ ቦታ ሁነህ ዐይኖችህን ወደ ሰሜንና ሊባ፥ ወደ ባሕርና ምሥራቅ አቅና፤ ይህችን የምታያትን ሀገር ሁሉ ለአንተና ለልጆችህ እስከ ዘለዓለም ድረስ እሰጣችኋለሁና። 31 ልጆችህንም እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ፤ ሰው የባሕር አሸዋን መቍጠር ይችል እንደ ሆነ ልጆችህም ይቈጠራሉ፤ ተነሥተህ ቁመቷንና ወርድዋን ዙራት፤ ሁሉንም ተመልከት፤ ለልጆችህ እሰጣታለሁና።” 32 አብራምም ወደ ኬብሮን ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ። 33 በዚያም ዓመት የኤላም ንጉሥ ኮሎዶጎሞር መጣ፤ የሰናዖርም ንጉሥ አምራፌል፥ የሲላሳር ንጉሥ አሪኦክ፥ የአሕዛብ ንጉሥም ቲርጋል መጡ፤ የገሞራንም ንጉሥ ወጉት። 34 የሰዶም ንጉሥ ግን ሸሸ፤ በጨው ባሕር በኩል በሲዲም ሸለቆ ብዙ ሰዎች በጦር ቈስለው ወደቁ፤ ሰዶምንና አዳማን ሴቦኢምንም ማረኩ፤ የአብራምን የወንድሙን ልጅ ሎጥንም ማረኩ፤ ገንዘቡንም ሁሉ ዘረፉ፤ እስከ ዳንም ድረስ ሄደ። ከጦር ያመለጠ አንድ ሰውም መጥቶ የወንድሙ ልጅ ሎጥ እንደ ተማረከ ለአብራም ነገረው። አሽከሮቹንም አስታጠቀ። 35 ከቀዳምያት ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐሥራትን እንዲሰጡ በአብርሃምና በልጆቹ ሥርዐት ተሠራ። እግዚአብሔርም ለዘለዓለም ይይዙት ዘንድ በፊቱ ለሚያገለግሉ ለካህናቱ እንዲሰጡአቸው የዘለዓለም ሥርዐትን ሠራ። 36 ከሁሉም ከእህሉም፥ ከወይኑም፥ ከዘይቱም፥ ከላሞችም፥ ከበጎችም፥ ከፍየሎችም ለእግዚአብሔር ዐሥራት ይሰጡ ዘንድ ለልጅ ልጅ ለዘለዓለም ሠርቶታልና ለዚህ ሕግ የተወሰነ ዘመን የለውም። 37 እርሱም በፊት ደስ ብሎአቸው ሊበሉትና ሊጠጡት ለካህናት ሰጠ። 38 የሰዶምም ንጉሥ ወደ እርሱ ደረሰ፤ በፊቱም ሰገደ፥ “ጌታችን አብራም ሆይ ፥ ያዳንኸውን ሰው ስጠን፤ ምርኮው ግን ለአንተ ይሁንልህ” አለው። 39 አብራምም፥ “እኔ አብራምን አበለጸግሁት የምትል እንዳትሆን፥ ጐልማሶች ከበሉት በቀር ከአንተ ገንዘብ ሁሉ የክር ፈትልና የጫማ ጠፍር እንዳልወስድ ገናና ወደ ሆነ አምላኬ እኔ እጆችን አነሣለሁ፤ ነገር ግን ከእኔ ጋር የሄዱ ሰዎች አውናንና ኤሴኬል፥ መምሬም እነርሱ ፈንታቸውን ይውሰዱ” አለው። |