ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በዚህ ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ ርኩሳን አጋንንት የኖኅን የልጅ ልጆች ያስቱአቸውና አእምሮአቸውን እያሳጡ ያጠፉአቸው ጀመሩ። 2 የኖኅም ልጆች ወደ አባታቸው ወደ ኖኅ መጡ። የልጅ ልጆቹንም የሚያስቱና የሚያደነቁሩ፥ የሚገድሉም የአጋንንትን ነገር ነገሩት። 3 ኖኅም ወደ ፈጣሪው ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፥ “ምሕረትህን አድርገህ ያዳንኸኝ፥ ልጆችንም ከጥፋት ውኃ ያዳንኻቸው፥ የጥፋትን ልጅ እንዳጠፋኸው እንድጠፋ ያላደረግኸኝ፥ በእኔ ላይ ያለ ይቅርታህ ብዙ ነውና፥ ቸርነትህም በሰውነቴ በዝታለችና፥ በሥጋ ውስጥ ሁሉ ያሉ የነፍሳት ፈጣሪ ሆይ፥ ይቅርታህ በልጆች ላይ ከፍ ከፍ ይበል፤ ክፉዎች አጋንንትም ከዚህ ዓለም እንዳያጠፉአቸው በላያቸው አይሠልጥኑ። 4 አንተም እኔን ባርከኝ። የብዙ ብዙ እንሆን ዘንድ፥ ምድርንም እንሞላት ዘንድ፥ ልጆችን ባርካቸው። አንተም በሕይወት ያሉ የእነዚህ ረቂቃን አጋንንት አባቶቻቸው ትጉሃን ያደረጉትን ታውቃለህ። ይዘህ በፍርድ ቦታ አግዛቸው፤ እነርሱ ክፉዎች ናቸውና፥ ለማጥፋትም ተፈጥረዋልና አምላኬ ሆይ፥ የእኔን የባሪያህን ልጆች አያጥፉ፤ በሕይወት በሚኖሩ ሰዎች ነፍስም አይሠልጥኑ፥ አንተ ብቻ ፍርዳቸውን ታውቃለህና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በጻድቃን ልጆች ላይ አይሠልጥኑ።” 5 አምላካችንም ሁሉን አስረን እናግዝ ዘንድ አዘዘን። የአጋንንትም አለቃ መስቴማ መጥቶ፥ “አቤቱ ፈጣሪዬ፥ ከእነርሱ በፊቴ ጥቂት አስቀርልኝ፤ ቃሌንም ይስሙ፤ እኔ የማዝዛቸውንም ሁሉ ያድርጉ፤ ከእነርሱ ካልቀሩልኝ በሰው ልጆች ላይ የፈቃዴን ሥልጣን ማድረግ አልችልምና። የሰው ልጆች ክፋታቸው ብዙ ስለ ሆነ ከፍርዴ አስቀድሞ እነርሱ ለማጥፋትና ለማሳት ናቸውና።” 6 “በፊቱ ዐሥረኛው ነገድ ይቅሩ፤ ዘጠኙን ነገድ ግን ወደ ፍርድ ቦታ ያውርዱአቸው” አለ። እርሱም በቀና ሥራ ጸንተው የሚኖሩ እንዳይደሉ፥ በእውነትም የሚጣሉ እንዳይደሉ ያውቃልና የሚድኑበትን ሁሉ ለኖኅ እናስተምረው ዘንድ ከእኛ አንዱን አዘዘው። 7 እኛም እንደ ቃሉ አደረግን፤ ፈጽመው የከፉ አጋንንትን በፍርድ ቦታ አስረን አጋዝን። ዐሥረኛውን ነገድ ግን በሰይጣን ፊት በምድር ይገዙ ዘንድ አስቀረን። በምድር እንጨቶችም ያድን ዘንድ የደዌያቸውን መድኀኒት ከማሳታቸው ጋር ለኖኅ ነገርነው። 8 ኖኅም በየመድኀኒቱ ዓይነት ሁሉ እንዳስተማርነው በመጽሐፍ ሁሉን ጻፈ። ክፉዎች አጋንንትም የኖኅን ልጆች እንዳይከታተሉ ተጋዙ። 9 ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ፈጽሞ እርሱን ይወደው ነበርና የጻፋቸውን መጻሕፍት ሁሉ ለታላቁ ልጁ ለሴም ሰጠው። ኖኅም እንደ አባቶቹ ሞተ፤ አራራት በሚባልም ሀገር በሉባር ተቀበረ፤ ኖኅም በሕይወቱ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ጨረሰ። ይህም ዐሥራ ዘጠኝ ኢዮቤልዩ ሁለት ሱባዔና አምስት ዓመት ነው። ፍጹም በሆነባት ሥራው በምድር የኖረው ሕይወቱ ከሄኖክ በቀር ከሰው ልጆች ይልቅ የከበረ ነበር። የሄኖክ ሥራ በፍርድ ቀን የትውልዱን ሁሉ ሥራ ይነግር ዘንድ ለዘለዓለም ትውልድ ምስክር ሊሆን ተፈጥሮአልና። 10 በሠላሳ ሦስተኛው ኢዮቤልዩ ከሁለተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ፋሌክ ስምዋ ሎምና የሚባል ሚስትን አገባ፤ ይህችውም የሴናዖር ልጅ ናት። በዚሁም ሱባዔ በአራተኛው ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት። ከአራራት ምድር ወደ ምሥራቅ ወደ ሰናዖር ሀገር ስለ ተሰደዱ በሰናዖር ሀገር ከተማንና አምባን ይሠሩ ዘንድ የሰው ልጆች በጽኑ ምክር እነሆ፥ ክፉዎችን ሆኑ ብሎአልና ስሙን ራግው አለው። ወደ ሰማይ እንወጣበታለን ሲሉ በዘመኑ ከተማንና ግንብን ሠርተዋልና፤ መሥራትም ጀምረዋልና። 11 በአራተኛውም ሱባዔ ጡቡን ሠርተው በእሳት ተኰሱ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው፤ የሚመርጉበት ጭቃውም ከባሕርና በሰናዖር ሀገር ከውኃዎች ምንጭ የሚወጣ የባሕርን አረፋ ሆነላቸው። 12 በአርባ ሦስት ዓመትም ሠሩት። እየሠሩም ነበሩ። ወርዱም ሁለት መቶ ሦስት ጡብ ነበር፤ የጡቡም ከፍታ የርዝመቱ አንድ ሦስተኛ ነበር። ቁመቱ አምስት ሺህ አራት መቶ ሠላሳ ሦስት ክንድ ከሁለት ስንዝር ወደ ላይ ወጣ። አቆልቋዩም ዐሥራ ሦስት ምዕራፍ ነበር። 13 አምላካችን እግዚአብሔርም እኛን እንዲህ አለን፥ “እነሆ፥ አንድ ቋንቋ የሆነ ሕዝብ ግንብ ይሠራ ጀመር፤ አሁንም ከእነርሱ ፈጽመን እንዳናጠፋ ኑ እንውረድ፤ የአንዱንም ቋንቋ አንዱ እንዳይሰማ፥ ቋንቋቸውን እንደባልቀው፤ በየከተማውና በየአሕዛቡ ይበተኑ፤ ከዚህ በኋላም እስከ ፍርድ ቀን ድረስ አንዲት ምክር በላያቸው አትኑር።” 14 እግዚአብሔርም ወረደ፤ እኛም የሰው ልጆች የሠሩትን ከተማውንና ግንቡን እናይ ዘንድ ከእርሱ ጋር ወረድን፤ ቋንቋቸውንም ደባለቀ፤ አንዱም የአንዱን ነገር አልሰማም። ከዚያም በኋላ ከተማውንና ግንቡን መሥራት ተዉ። 15 ስለዚህም አምላክ በዚያ የሰው ልጆችን ቋንቋ ሁሉ ደባልቆአልና የሰናዖር ሀገር ሁሉ ባቢል ተባለች፤ ከዚያም በየከተማቸውና በየቋንቋቸው፥ በየወገናቸውም ተበተኑ። 16 እግዚአብሔርም ታላቅ ነፋስን አምጥቶ ግንባቸውን በምድር ላይ ገለበጠ፤ እነሆ፥ እርሱም በሰናዖር ሀገር በአሦርና በባቢሎን መካከል ነው። ስምዋንም ድቀት አላት። በሠላሳ አራተኛውም ኢዮቤልዩ በአራተኛው ሱባዔ በአንደኛው ዓመት መጀመሪያ ከሰናዖር ሀገር ተበተኑ። 17 ካምና ልጆቹም ለእርሱ ወደ ተያዘች በደቡብ ሀገር በዕጣ ወዳገኛት ሀገር ሄዱ። ከነዓንም እስከ ግብፅ ውኃ መፍሰሻ ድረስ ያለችውን የሊባኖስን ሀገር እጅግ ያማረች እንደ ሆነች አየ። ወደ ርስቱም ሀገር ወደ ባሕሩ መግቢያ አልሄደም፤ እርሱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ በሊባኖስና በባህሩ ዙሪያ ምድር ኖረ። 18 አባቱ ካምና ወንድሞቹ ኩሳ፥ ሚጽራይምም፥ “የአንተ ዕጣ ባልሆነች ሀገር ኖረሃልና፥ በዕጣም አልወጣችልንምና እንዲህ አታድርግ አሉት። እንደዚህ ብታደርግ አንተና ልጆችህ በዚህ ምድር ትጠፋላችሁ፤ በክርክርም ኖራችኋልና በክርክር የተረገማችሁ ትሆናላችሁ፤ ልጆችህም በጠብ ይጠፋሉ፤ አንተም ለዘለዓለም ትጠፋለህ። 19 ለሴምና ለልጆቹ በዕጣቸው ወጥቶአልና በሴም ሀገር አትኑር፤ አንተም የተረገምህ ነህ። በአባታችን በኖኅና በቅዱሱ ፈራጅ ፊት ለመርገም በመሐላ ከተዘጋጀን ከኖኅ ልጆች ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ” አሉት። እርሱ ግን አልሰማቸውም፤ ከኤማት ጀምሮ እስከ ግብፅ መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ሀገር ኖረ፤ ልጆቹም እስከዚህ ቀን ድረስ በዚያ ኖሩ። ስለዚህ ያች ሀገር የከነዓን ሀገር ተባለች። 20 ያፌትና ልጆቹ ግን ወደ ባሕር ሄዱ፤ ድርሻቸው በሆነ ሀገርም ኖሩ። 21 ማዳይም ባሕር ያለባትን ሀገር አየ፤ ነገር ግን በፊቱ ደስ አላሰኘችውም፤ የሚስቱ ወንድሞች ከሆኑ ከኤላምና ከአሱር፥ ከአርፋክስድም ለምኖ እስከዚህች ቀን ድረስ የሚስቱ ወንድሞች አቅራቢያ በሚሆን በሜቄዶን ሀገር ኖረ። የእርሱን ቦታና የልጆቹን ቦታ ሜቄዶንንም በአባታቸው በማዳይ ስም ጠራው። 22 በሠላሳ አምስተኛውም ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ራግው ስምዋ ዑራ የምትባል ሚስትን አገባ፤ ይህችውም የኬሴድ ልጅ የዑር ልጅ ናት። ወንድ ልጅንም ወለደችለት፤ ስሙንም ሴሩግ ብሎ ጠራው። 23 በዚህ ኢዮቤልዩ በሰባተኛው ሱባዔ የኖኅ ልጆች ሰውን ለመማረክና ለመግደል፥ እያንዳንዱም ወንድሙን ለመግደል፥ የሰውንም ደም በምድር ላይ ለማፍሰስ፥ ደምንም ለመብላት፥ የጸኑ ከተማዎችንና አንባዎችን፥ ግንቦችንም ለመሥራት ሕዝብ በሕዝብ ላይ ለመነሣት፥ በመንግሥትም ላይ አስቀድሞ ለመሾም፥ ሕዝቡ በሕዝቡ ፊት፥ አሕዛቡም በአሕዛቡ ፊት ወደ ሰልፍ ለመሄድ፥ ከተማም ከከተማ ጋር ለመጣላት፥ ሁሉም ክፉ ሥራ ለመሥራት፥ የጦር መሣሪያንም ለመግዛት፥ ለልጆቻቸውም ሰልፍን ለማስተማር መዋጋት ጀመሩ። አንዱ አገር ሌላውን አገር ይማርክ፥ ሴት ባሪያንና ወንድ ባሪያንም ይገዙ ጀመር። 24 የኬሴድ ልጅ ዑርም በከላውዴዎን ያለች የዑርን ከተማ ሠራ፤ ስምዋንም በእርሱ ስምና በአባቱ ስም ጠራ። ጣዖቶችንም ሠሩ፤ እያንዳንዱም ለራሱ ቀርፆ ለሠራው ጣዖት ይሰግድ ነበር፤ ጣዖትንና ምስልን፥ ርኵሰትንም ይሠሩ ጀመር፤ ክፉዎች አጋንንትም ኀጢአትንና ርኵሰትን ይሠሩ ዘንድ ይረዱና ያስቱ ነበር። 25 አለቃው መስቴማም ይህን ሁሉ ለመሥራት ይበረታ ነበር፤ ኀጢአትንና በደልን ሁሉ፥ ፈጽሞም ለማጥፋትና ክህደትን ሁሉ ለማሠራት፥ በምድርም ደምን ለማፍሰስ ከእጁ በታች ያሉ የአጋንንትን እጅ ይልክ ነበር። 26 ስለዚህም ሰው ሁሉ በደልንና ኀጢአትን ሁሉ ወደ መሥራት ተመልሶአልና፥ የሴሩሕ ስም ሴሩግ ተባለ። እርሱም አደገ፤ ለሚስቱም እናት አባት አቅራቢያ በሆነ በከላውዴዎን ዕጣ በዑር ኖረ። ጣዖትንም ያመልክ ነበር፤ እርሱም በሠላሳ ሰባተኛው ኢዮቤልዩ በአምስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ሚስትን አገባ፤ ስምዋም ሜልካ ይባላል፤ ይህችውም የአባቱ የእኅት ልጅ የካቤር ልጅ ናት፥ በዚህ ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ናኮርን ወለደችለት። 27 እርሱም አደገ፤ በከላውዴዎን ዕጣ በዑርም ኖረ። አባቱም በሰማይ ምልክት ለማምዋረትና ለመጠንቆል የከዋክብትን ምርምር አስተማረው። 28 በሠላሳ ሰባተኛው ኢዮቤልዩ በስድስተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ሚስትን አገባ፤ ስምዋም ኢዮስካ ይባላል። ይህችም የከለዳውያን ወገን የኔስቴግ ልጅ ናት። በዚህ ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት ታራ የሚባል ወንድ ልጅን ወለደችለት። 29 አለቃው መስቴማም ምድርን ለማጥፋት፥ በምድር ላይ የተዘራውን ዘር ይበሉ ዘንድ ወፎችንና ቁራዎችን ሰደደ። ቁራዎችም ሳያርሱ የሰው ልጆች አዝመራን ይቀሙ ዘንድ ከምድር ላይ ዘሩን ይለቅሙ ጀመር። ስለዚህም አሞራዎችና ወፎች ያስቸግሩአቸው ነበርና፥ ዘራቸውንም ይበሉባቸው ነበርና ስሙን ታራ አለው። 30 ከወፎቹም ፊት የተነሣ ዓመቶች ድርቅ ይሆኑ ጀመር፤ የእንጨቱንም ፍሬ ሁሉ ከዛፎቹ ላይ እየለቀሙ ይበሉ ነበር፥ በዘመናቸው ከምድር ፍሬ ሁሉ ጥቂት ማዳን ቢችሉም በታላቅ ኀይል ነበር። በሠላሳ ዘጠነኛውም ኢዮቤልዩ በሁለተኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ታራ ሚስት አገባ፤ ስምዋም ኤድና ይባላል፤ ይህችውም የአባቱ የእኅት ልጅ የምትሆን የአብራም ልጅ ናት። በዚህም ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት። የልጁ ልጅ ሳይፀነስ ሙቶአልና ስሙን በእናቱ አባት ስም አብራም አለው። 31 ያም ልጅ ሰው ሁሉ ጣዖታቱን በመከተልና ኀጢአትን በመሥራት እንደሚስት የምድርን ስሕተት ያውቅ ጀመር። 32 አባቱም መጽሐፍን አስተማረው፤ የሁለት ሱባዔ ዓመት ልጅም ነበረ። ከእርሱም ጋር ለጣዖት እንዳይሰግድ አባቱን ከመከተል ተለየ። 33 ከሰዎች ልጆች ስሕተትም ያድነው ዘንድ፥ ዕጣውም ርኵሰትንና ፌዝን በመከተል ወደ ስሕተት እንዳይሆን ሁሉን ወደ ፈጠረ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ጀመር። 34 በምድርም ዘርን ለመዝራት ጊዜው ደረሰ፤ ዘራቸውንም ከአሞራዎች ይጠብቁ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ወጡ። 35 አብራምም ከወጡ ልጆች ጋር ወጣ። እርሱም የዐሥራ አራት ዓመት ልጅ ነበረ፤ ብዙዎች ቁራዎችም ዘርን ይለቅሙ ዘንድ መጡ። አብራምም በምድር ላይ ሳያርፉ በፊታቸው ይሮጥ ነበር፤ ዘርንም ለመልቀም በምድር ላይ ሳያርፉ፥ “ወደ መጣችሁበት ቦታ ተመለሱ እንጂ ወደ ምድር አትውረዱ” እያለ ይጮኽ ነበር፤ እነርሱም ተመለሱ። 36 በዚያችም ቀን ብዙዎች ቁራዎችን ለመከላከል ሰው አስቀመጡ። አብራምም ባለበት በዚያ እርሻ ሁሉ ከቁራዎች ሁሉ አንድም ቁራ አላረፈም። 37 በእርሻዎቹ ውስጥ ከእርሱ ጋር ያሉት ሰዎች ሁሉ ሲጮኽና አሞራዎችን ሁሉ፦ ተመለሱ ሲላቸው ይሰሙት ነበር፤ ስሙም በከላውዴዎን ምድር ሁሉ ከፍ ከፍ አለ። 38 የሚዘሩም ሰዎች ሁሉ በዚህ ዓመት ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። የዘሩ ወራትም እስኪፈጸም ድረስ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር። ምድራቸውንም ዘሩ፤ በዚያም ዓመት የሚበቃ እህልን አገቡ፤ በልተውም ጠገቡ። 39 አብራምም በአምስተኛው ሱባዔ በአንደኛው ዓመት የበሬ ዕቃ ለሚሠሩት ሰዎች እንጨት መጥረብን አስተማረ። 40 በምድርም ላይ የበሬ ዕቃ ሠሩ፤ በላዩም ዘርን ያኖር ዘንድ በድግሩ አንጻር እርፍን ሠራ፤ ዘሩም በእርፉ ጫፍ ወርዶ በምድር ይሸፈን ነበር። ከዚህም በኋላ ከአሞራዎቹ ፊት የተነሣ አልፈሩም ነበር፤ በእርፉም ድግር ሁሉ ላይ እንዲህ አደረጉ፤ በምድርም ላይ የእርፉን ድግር አኖሩ። 41 ዘርንም ዘሩ፤ ሰዎችም ሁሉ አብራም እንዳዘዛቸው ሁሉን አደረጉ። ከዚያ በኋላ ከአሞራዎቹ የተነሣ አልፈሩም። 42 በስድስተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት አብራም አባቱ ታራን፥ “አባ አባቴ፥” ብሎ ጠራው። እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ እነሆኝ፥” አለው። እርሱም፥ “ምንም እስትንፋስ የላቸውምና አንተ ከምታመልካቸውና በፊታቸው ከምትሰግድላቸው ከእነዚህ ከጣዖታቱ ለእኛ ምን ረድኤትና ደስታ አለን? ድዳዎች ናቸውና፥ ልቡናንም የሚያስቱ ናቸውና አታምልኩአቸው። 43 ሰማይን የፈጠረ፥ በምድርም ላይ ዝናብንና ጠልን የሚያወርደውን፥ በምድር ላይ ሁሉን የሚያደርገውን፥ ሁሉንም በቃሉ የፈጠረውን፥ ሕይወትም ሁሉ ከእርሱ የሚገኘውን የሰማይን አምላክ አምልኩ። 44 እስትንፋስ የሌላቸው ጣዖታቱን እናንተ ለምን ታመልካላችሁ? እነርሱ የሰው ሥራ ናቸውና፥ እናንተ በጫንቃችሁ ትሸከሙአቸዋላችሁና፥ ለሚሠሩአቸው ሰዎች ታላቅ ተዋርዶ ናቸው እንጂ ከእነርሱ ረድኤት አይገኝምና፥ ለሚያመልኩአቸውም ሰዎች የልቡና ስሕተት ናቸውና አታምልኩአቸው።” 45 አባቱም፥ “ልጄ ሆይ፤ እኔም አውቃለሁ፤ ነገር ግን በፊታቸው እንዳገለግል ላደረጉኝ ለሕዝቡ ምን አደርጋለሁ? እውነት ነገርንም ብነግራቸው፥ ያመልኩአቸውና ያመሰግኑአቸው ዘንድ ልቡናቸው እነርሱን ተከትላለችና ይገድሉኛል፤ ልጄ ሆይ፥ እንዳይገድሉህ ዝም በል” አለው። 46 ለሁለቱ ወንድሞቹም ይህን ነገር ነገራቸው፤ እነርሱም ተቈጡት፤ እርሱም ዝም አለ። 47 በአርባው ኢዮቤልዩ በሁለተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት አብራም ሚስት አገባ፤ ስምዋም ሶራ ይባላል፤ ይህችውም የአባቱ ልጅ ናት፤ ሚስትም ሆነችው። 48 ወንድሙ አራንም በሦስተኛው ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ሚስት አገባ። በዚህም ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም ሎጥ አለው። ወንድሙ ናኮርም ሚስትን አገባ። |