ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ኩፋሌ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የእስራኤል ልጆች ከግብፅ በወጡበት በመጀመሪያው ዘመን እንዲህ ሆነ። በሦስተኛው ወር፥ ያ ወር በባተ በዐሥራ ስድስተኛው ቀን፥ እግዚአብሔር፥ “ከእኔ ዘንድ ወደዚህ ተራራ ውጣ፤ በጻፍኸውም መጠን ልብ ታስደርጋቸው ዘንድ ሕጉና ሥርዐቱ የተጻፉባቸውን ሁለቱን የዕንቍ ጽላት እሰጥሀለሁ” ብሎ ለሙሴ ተናገረ። 2 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። የእግዚአብሔርም ብርሃን በደብረ ሲና ተገለጠ። ስድስት ቀንም ደመና ጋረደው። 3 በሰባተኛዪቱም ቀን በደመና መካከል ሆኖ ሙሴን ጠራው፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በተራራው ራስ ላይ እንደ እሳት ሲነድድ አየ። 4 ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተቀመጠ። እግዚአብሔርም ያለፈውንና የሚመጣውን፥ ሕጉ የሚጠበቅበትንና አምልኮቱ የሚነገርበትን፥ የዘመኑን ሁሉ አከፋፈል ነገር አመለከተው። 5 እንዲህም አለው፥ “በዚህ ተራራ ላይ እኔ በምነግርህ ነገር ሁሉ ልብህን አኑር። በአንተና በእኔ መካከል በደብረ ሲና ዛሬ ለልጆቻቸው የሚደረገውን፥ እኔ የምሠራውን ሥርዐት ለማስፈረስ ስለ ሠሩት ኀጢአት ሁሉ እንደ ተለየሁአቸው ልጆቻቸው ይሰሙ ዘንድ በመጽሐፍ ጻፈው።” 6 ይህ ሁሉ ነገር በእነርሱ ላይ በመጣባቸው ጊዜ እንዲህ ይናገራል። በፈረድሁባቸው ሁሉ፥ በሥራቸውም ሁሉ ከእነርሱ ይልቅ እኔ እውነተኛ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ከእነርሱም ጋር ያለሁ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7 አንተም እኔ ዛሬ የነገርሁህን ይህን ሁሉ ነገር ጻፍ። እኔ ቍጣቸውን አውቃለሁና፥ ማርና ወተትን የምታስገኝ ሀገርን ለልጆቻችሁ እሰጣለሁ ብዬ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደማልሁላቸው ሀገር ሳላገባቸው አንገታቸው ደንዳና እንደ ሆነ አውቃለሁና፥ በልተውና ጠግበው ከመከራቸው ሁሉ ወደማያድናቸው ወደ ልዩ ጣዖት ይመለሳሉና። 8 ይህች መጽሐፍ በእነርሱ ላይ ሥርዐት ትሁንባቸው። እኔ የማዝዛቸውን ትእዛዜን ሁሉ ይዘነጋሉና፥ አሕዛብንም ተከትለው ወደ ኀጢአታቸው ይሄዳሉና፥ ለጣዖቶቻቸውም ይገዛሉና፤ በእነርሱም መከራንና ጭንቅን፥ ጦርንም ለማምጣት መሰናክል ይሆንባቸዋል። 9 “ብዙ ሰዎች ይጠፋሉ፥ ተይዘውም በጠላቶቻቸው እጅ ይወድቃሉ። ሥርዐቴንና ትእዛዜን፥ የቃል ኪዳኔንም በዓላት፥ ሰንበታትንም፥ በመካከላቸውም የለየሁትን ቅድሳቴን፤ ስሜ በእርሱ ይጠራ ዘንድ፥ ያድርበትም ዘንድ በምድር መካከል ያከበርሁትን ድንኳኔንና መቅደሴን ትተዋልና። 10 በዓላትን፥ መስገጃ ዛፍንና ጣዖትን ሠርተው ለመሳት እየራሳቸው ይሰግዳሉ። ልጆቻቸውንም ለአጋንንት፥ በልቡናቸው ስተው ለሠሩትም ጣዖት ሁሉ ይሠዋሉ፤ አዳኝባቸውም ዘንድ ወደ እነርሱ ምስክሮችን እልካለሁ። ነገር ግን አይሰሙም፤ ምስክሮችንም ይገድላሉ። 11 ሕግን የሚሹ ሰዎችንም ይገድሉአቸዋል፤ ከሀገርም አስወጥተው ይሰድዱአቸዋል፤ ሁሉንም ያቦዝናሉ፤ በዐይኖችም ፊት ክፉ ሥራ መሥራትን ይጀምራሉ። 12 ከእነርሱም ፊቴን እመልሳለሁ፤ ለመበዝበዝና ለመማረክ፥ ለመዘረፍም ይሆኑ ዘንድ በአሕዛብ እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከኢየሩሳሌምም መካከል አርቃቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል እበትናቸዋለሁ። 13 “ሕጌን ሁሉ፥ ትእዛዜንም ሁሉ፥ ፍርዴንም ሁሉ፥ ሥርዐቴንም ሁሉ ይዘነጋሉ። የወሩን መባቻና ሰንበትን፥ በዓሉንና ኢዮቤልዩን፥ ሥርዐቱንም፥ ይዘነጋሉ። 14 ከዚህም በኋላ በፍጹም ልባቸው፥ በፍጹም ነፍሳቸው፥ በፍጹም ኀይላቸውም ከአሕዛብ መካከል ወደ እኔ ይመለሳሉ። እኔም ከአሕዛብ ሁሉ መካከል እሰበስባቸዋለሁ። 15 እገለጥላቸው ዘንድ ይፈልጉኛል። በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸውም በፈለጉኝ ጊዜ፥ እኔ በእውነት ብዙ ሰላምን እገልጥላቸዋለሁ፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ ወደ ቀና ሕግ እመልሳቸዋለሁ። 16 ለበረከት ይሆናሉ፤ ለመርገምም አይደለም፤ ራስ ይሆናሉ፤ ጅራትንም አይደለም፤ በመካከላቸውም መቅደሴን እሠራለሁ፤ ከእነርሱም ጋር እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም በሚገባ በእውነት ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝና አልተዋቸውም፤ አልለያቸውምም።” 17 ሙሴም በግንባሩ ተደፍቶ ጸለየ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ አምላኬ፥ በልቡናቸው ስሕተት ይሄዱ ዘንድ ርስትህ የሆኑ ወገኖችህን አትተው። ይገዙአቸውም ዘንድ፥ አንተንም እንዲበድሉ ያደርጓቸው ዘንድ በጠላቶቻቸው በአሕዛብ እጅ አትጣላቸው። 18 አቤቱ፥ ይቅርታህ በወገኖችህ ላይ ከፍ ከፍ ይበል፤ የቀና ልቡናንም ፍጠርላቸው። በፊትህ ለማጣላት ፥ ከባለምዋልነትህም ይጠፉ ዘንድ ከእውነተኛ ሥራ ሁሉ ለማሰነካከል የዲያብሎስ መንፈስ አይሠልጥንባቸው። 19 እነርሱስ በታላቅ ኀይልህ ከግብፅ ሰዎች እጅ ያዳንኻቸው ወገኖችህና ማደሪያዎችህ ናቸው። ንጹሕ ልቡናን ፍጠርላቸው። የተቀደሰ መንፈስንም አሳድርባቸው፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በኀጢአታቸው አይሰነካከሉ።” 20 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፥ “እኔ ክርክራቸውንና አሳባቸውን አውቃለሁ፤ አንገታቸው ደንዳና ነው። ኀጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኀጢአት እስኪያውቁ ድረስ አይሰሙም። 21 ከዚህም በኋላ በፍጹም ቅንነት፥ በፍጹም ልቡናና በፍጹም ሰውነት ወደ እኔ ይመለሳሉ። የልቡናቸውን ቈላፍነትና የዘራቸውን ልቡና ቈላፍነት እቈርጣለሁ። ንጹሕ ልቡናንም እፈጥርላቸዋለሁ። 22 ከዚያች ቀን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ እኔን ከመከተል ወደ ኋላ እንዳይመለሱ አነጻቸዋለሁ፤ ልቡናቸውም እኔን ትከተላለች፤ ትእዛዜንም ሁሉ ይፈጽማሉ። 23 አባት እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ልጆች ይሆኑኛል፤ ሁሉም የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ። መልአክ ሁሉ፥ ሰውም ሁሉ ያውቃቸዋል። እነርሱ ልጆች እንደ ሆኑ፥ እኔም በሚገባና በእውነት አባታቸው እንደ ሆንሁ፥ እንደምወድዳቸውም ያውቋቸዋል። 24 አንተም በዚህ ተራራ ላይ እኔ የምነግርህን ይህን ነገር ሁሉ፥ የፊቱንና የኋላውን፥ ይመጣ ዘንድ ያለውንም፥ ሕጉና አምልኮቱም በሚነገሩበት በዓመቱ ቍጥር እስከ ዘለዓለም ድረስ የሚሆነውን የዘመኑን አከፋፈል ሁሉ፥ እኔም ወርጄ በዘመኑ ሁሉ ከእነርሱ ጋር እስክኖር ድረስ የሚደረገውን ሁሉ ጻፍ።” 25 መልአከ ገጹንም እንዲህ አለው፥ “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለዘለዓለም የምመሰገንበት ቤተ መቅደስ በመካከላቸው እስኪሠራ ድረስ እግዚአብሔርም ለሁሉ እስኪታይ ድረስ የሚሆነውን ለሙሴ ጻፍለት። 26 እኔ የእስራኤል አምላክ እንደ ሆንሁ፥ ለያዕቆብ ልጆች ሁሉ አባት እንደ ሆንሁ፤ በደብረ ጽዮንም ለዘለዓለም ንጉሥ እንደ ሆንሁ ሁሉ ያውቃል፤ ጽዮን ኢየሩሳሌምም የከበረች ትሆናለች።” |