ኢያሱ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የአካን በደል 1 የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር ታላቅ በደል በደሉ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች ላይ ተቈጣ። 2 ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዊን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ልኮ፥ “ውጡ፤ ጋይንም ሰልሉ” ብሎ ተናገራቸው፤ ሰዎቹም ወጡ፤ ጋይንም ሰለሉ። 3 ወደ ኢያሱም ተመልሰው፥ “ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፤ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሁሉ ግን ወደዚያ አትውሰድ፤ ጥቂቶች ናቸውና” አሉት። 4 ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፤ የጋይም ሰዎች አባረሩአቸው፤ ከፊታቸውም ሸሹ። 5 የጋይ ሰዎችም ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ሰዎችን ገደሉ፤ ከበሩ ጀምረው እስከ አጠፉአቸው ድረስ አባረሩአቸው፤ በቍልቍለቱም ገደሉአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ደነገጠ፤ እንደ ውኃም ሆነ። 6 ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፤ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። 7 ኢያሱም አለ፥ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! በአሞሬዎናውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን፥ ታጠፋንም ዘንድ አገልጋይህ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገረ? በዮርዳኖስ ማዶ ተቀምጠን በኖርን ነበር እኮ! 8 ጌታ ሆይ! እስራኤል ጀርባውን ወደ ጠላቶቹ ከመለሰ እንግዲህ ምን እላለሁ? 9 ከነዓናውያንም፥ በምድሪቱም የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፤ ከምድርም ያጠፉናል፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው?” 10 እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፥ “ለምን በግንባርህ ተደፍተሃል? ተነሥ! 11 ሕዝቡ በድለዋል፤ ከእነርሱም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፤ እርም ከሆነውም ነገር ሰርቀው ወሰዱ፤ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። 12 ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፤ የተረገሙ ስለሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፤ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። 13 ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ እንዲህም በላቸው፦ ‘እስራኤል ሆይ! እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፤ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም’ ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና እስከ ነገ ራሳችሁን አንጹ። 14 ነገም በየነገዳችሁ ትቀርባላችሁ፤ እግዚአብሔርም የሚለየው ነገድ በየወገኖቹ ይቀርባል፤ እግዚአብሔርም የሚለየው ወገን በየቤተ ሰቦቹ ይቀርባል፤ እግዚአብሔርም የሚለየው ቤተ ሰብ በየሰዉ ይቀርባል። 15 ምልክት የታየበት ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ በደል አድርጎአልና፥ እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላሉ።” 16 ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፤ እስራኤልንም በየነገዶቻቸው ሰበሰባቸው፤ በይሁዳም ነገድ ላይ ምልክት ታየ፤ 17 የይሁዳም ወገኖች ተለዩ፤ በዛራም ወገን ምልክት ታየ፤ የዛራም ወገን በየቤተ ሰቡ ተለየ፤ 18 በዘንበሪም ወገን ምልክት ታየ፤ የዘንበሪም ቤተ ሰብ እያንዳንዱ ተለየ፤ ከይሁዳም ወገን በሆነ በከርሚ ልጅ በዘንበሪ ልጅ በዛራ ልጅ በአካን ላይ ምልክት ታየ። 19 ኢያሱም አካንን፥ “ልጄ ሆይ! ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፤ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝም” አለው። 20 አካንም መልሶ ኢያሱን፥ “በእውነት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ፊት በድያለሁ፤ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ። 21 በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ ካባ፥ ሁለት መቶ ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፤ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፤ ብሩም ከሁሉ በታች ነው” አለው። 22 ኢያሱም መልእክተኞችን ላከ፤ ወደ ሰፈርም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ እነሆም እርሱ በድንኳኑ ውስጥ ተደብቆ፥ ብሩም በበታቹ ነበረ። 23 ከድንኳኑም ውስጥ አውጥተው ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ አመጡት፤ በእግዚአብሔርምፊት አኖሩት። 24 ኢያሱም የዛራን ልጅ አካንን፥ ብሩንም፥ ልብሱንም፥ ልሳነ ወርቁንም ወደ አኮር ሸለቆ ወሰዳቸው፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹንም፥ በሬዎቹንም፥ አህያዎቹንም፥ በጎቹንም፥ ድንኳኑንም፥ ንብረቱንም ሁሉ ወደ ዔሜቃኮር ወሰደ። 25 ኢያሱም፥ “ለምን አጠፋኸን? ዛሬ እንዳጠፋኸን እግዚአብሔር ዛሬ ያጥፋህ” አለው፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ወገሩት፤ በእሳትም አቃጠሉት፤ በድንጋይም ወገሩአቸው። 26 በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩ፤ እግዚአብሔርም ከቍጣው መቅሠፍት ተመለሰ። ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ዔሜቃኮር ተብሎ ተጠራ። |