ኢያሱ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር በኩል የነበሩት የአሞራውያን ነገሥት ሁሉ፥ በባሕሩም አጠገብ የነበሩ የፊኒቃውያን ነገሥት ሁሉ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት የዮርዳኖስን ውኃ እስኪሻገሩ ድረስ እንዳደረቀ በሰሙ ጊዜ፥ ልባቸው ቀለጠ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ አእምሮአቸውን ሳቱ። የእስራኤል ልጆች በጌልጌላ እንደ ተገረዙ 2 በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር ኢያሱን፥ “ከሻፎ ድንጋይ የባልጩት መቍረጫ ሠርተህ የእስራኤልን ልጆች ዳግመኛ ግረዛቸው” አለው። 3 ኢያሱም የባልጩት መቍረጫ ሠርቶ የግርዛት ኮረብታ በተባለ ስፍራ የእስራኤልን ልጆች ገረዘ። 4 ኢያሱ ሕዝቡን ሁሉ የገረዘበት ምክንያት ይህ ነው፤ ከግብፅ የወጡ ወንዶች ተዋጊዎች ሁሉ ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ ላይ በምድረ በዳ ሞቱ፤ የወጡትም ወንዶች ሁሉ ተገርዘው ነበር። 5 ነገር ግን ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመንገድ፥ በምድረ በዳ የተወለዱ ሕዝብ ሁሉ አልተገረዙም ነበርና፥ ኢያሱ እነዚህን ሁሉ ገረዛቸው። 6 እግዚአብሔርም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻችን የማለላቸውን ምድር እንደማያሳያቸው የማለባቸውን፥ ከግብፅ የወጡ የእግዚአብሔርንም ቃል ያልሰሙ፥ እነዚያ ተዋጊዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች አርባ ዓመት በመድበራ ምድረ በዳ ይዞሩ ነበር። 7 ልጆቻቸውን በእነርሱ ፋንታ አስነሣ፤ እነዚህንም ኢያሱ ገረዛቸው፤ በመንገድ ስለተወለዱ አልተገረዙም ነበርና። 8 በተገረዙም ጊዜ እስኪድኑ ድረስ በሰፈር ውስጥ ተቀመጡ። 9 እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “ዛሬ የግብፅን ተግዳሮት ከእናንተ ላይ አስወግጃለሁ” አለው፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ጌልገላ ተብሎ ተጠራ። 10 የእስራኤልም ልጆች በጌልገላ ሰፈሩ፤ ከወሩም በዐሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ ምዕራብ ፋሲካን አደረጉ። 11 ከምድሪቱም ፍሬ ቂጣና አዲስ እህል በዚያው ቀን በሉ። 12 በነጋውም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ዳግመኛ መና አላገኙም፤ በዚያው ዓመት የፊኒቆንን ምድር ፍሬ ሰበሰቡ። ኢያሱና ባለ ሰይፉ ሰው 13 እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ፤ እነሆም፥ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ አየ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፥ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?” አለው። 14 እርሱም፥ “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ፤ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ” አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና፥ “በባሪያህ ዘንድ ምን አቁሞሃል?” አለው። 15 የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን፥ “አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” አለው። ኢያሱም እንዲሁ አደረገ። |