ኢያሱ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እስራኤል የዮርዳኖስን ወንዝ እንደ ተሻገሩ 1 ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፤ እርሱና እስራኤልም ሁሉ ከሰጢም ተጕዘው ወደ ዮርዳኖስ መጡ፤ ሳይሻገሩም በዚያ አደሩ። 2 ከሦስት ቀንም በኋላ ጸሓፊዎች በሰፈሩ መካከል ገቡ። 3 ለሕዝቡም እንዲህ ብለው ዐወጁ፥ “የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ሌዋውያንና ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት። 4 በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን፤ በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሄዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ።” 5 ኢያሱም ሕዝቡን፥ “ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ራሳችሁን አንጹ” አለ። 6 ኢያሱም ካህናቱን፥ “የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክማችሁ በሕዝቡ ፊት ሂዱ” ብሎ ተናገራቸው፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው በሕዝቡ ፊት ሄዱ። 7 እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር መሆኔን ያውቁ ዘንድ በዚህ ቀን በእስራኤል ልጆች ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደርግህ ዘንድ እጀምራለሁ። 8 አሁንም አንተ የቃል ኪዳኑን ታቦት የሚሸከሙትን ካህናት በዮርዳኖስ ውኃ ዳር ስትደርሱ በዮርዳኖስ ውስጥ ቁሙ ብለህ እዘዝ” አለው። 9 ኢያሱም ለእስራኤል ልጆች፥ “ወደዚህ ቀርባችሁ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ” አለ። 10 ኢያሱም አለ፥ “ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደ ሆነ፥ እርሱም ከፊታችሁ ከነዓናዊውን፥ ኬጤዎናዊውንም፥ ኤዌዎናዊውንም፥ ፌርዜዎናዊውንም፥ ጌርጌሴዎናዊውንም፥ አሞሬዎናዊውንም፥ ኢያቡሴዎናዊውንም ፈጽሞ እንዲያጠፋቸው በዚህ ታውቃላችሁ። 11 እነሆ፥ የምድር ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በፊታችሁ ዮርዳኖስን ትሻገራለች። 12 አሁንም ከእስራኤል ነገዶች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ምረጡ፤ ከየነገዱ አንድ አንድ ሰው ይሁን። 13 እንዲህም ይሆናል፤ የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግር ጫማ በዮርዳኖስ ውኃ ውስጥ ሲቆም፥ የዮርዳኖስ ውኃ ይደርቃል፤ ከላይ የሚወርደውም ውኃ ይቆማል።” 14 እንዲህም ሆነ፤ ሕዝቡ ዮርዳኖስን ሊሻገሩ ከየድንኳናቸው በወጡ ጊዜ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር። 15 እንደ ክረምትና እንደ መከር ወራት ሁሉ ዮርዳኖስ እስከ ወሰኑ ሞልቶ ነበርና የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸካሚዎቹ ወደ ዮርዳኖስ በገቡ ጊዜ፥ ታቦቱን የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃዉ ዳር ሲጠልቁ፥ 16 ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ እስከ ቀርያትያርም አውራጃ እጅግ ርቆ እንደ ግድግዳ ቆመ፤ ወደ ዓረባ ባሕር ወደ ጨው ባሕር የሚወርደው ውኃም ፈጽሞ ደረቀ፤ ሕዝቡም በኢያሪኮ ፊት ለፊት ቆሙ። 17 የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ የእስራኤል ልጆች ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ። |