ኢያሱ 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኢያሱ በሴሎ ያደረገው የመጨረሻ ንግግር 1 ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴሎ ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፥ አለቆቻቸውንም፥ ጸሓፊዎቻቸውንም፥ ፈራጆቻቸውንም ጠራቸው። በእግዚአብሔርም ፊት አቆማቸው። 2 ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። 3 አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፤ ይስሐቅንም ሰጠሁት። 4 ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ የያዕቆብም ልጆች ወደ ግብፅ ወረዱ፤ በዚያም ታላቅ ሕዝብ ሆኑ፤ በዙም፤ በረቱም፤ ግብፃውያንም መከራ አጸኑባቸው። 5 ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፤ በእነርሱም ላይ ስላደረጉት ነገር ግብፃውያንን ቀሠፍኋቸው፤ 6 ከዚያም በኋላ አባቶቻችሁን ከግብፅ አወጣኋቸው፤ ወደ ባሕሩም ገባችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሶች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ ተከተሉአቸው። 7 ወደ እግዚአብሔርም በጮሃችሁ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ደመናንና ጭጋግን አደረግሁ፤ ባሕሩንም መለስሁባቸው፤ አሰጠማቸውም፤ ዐይኖቻችሁም በግብፅ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። 8 በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡት ወደ አሞሬዎናውያን ምድርም ወሰድኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፤ ሙሴም ተዋጋቸው፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፤ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። 9 የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። 10 እኔ ግን ላጠፋችሁ አልወደድሁም፤ መባረክንም ባረክኋችሁ፤ ከእጁም አዳንኋችሁ፤ 11 ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞሬዎናዊው፥ ፌርዜዎናዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጤዎናዊው፥ ጌርጌሴዎናዊው፥ ኤዌዎናዊው፥ ኢያቡሴዎናዊው ተዋጉአችሁ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። 12 በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፤ በሰይፍህም፥ በቀስትህም ሳይሆን ዐሥራ ሁለቱን የአሞሬዎናውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደድኋቸው። 13 ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፤ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።’ 14 “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩት፤ በእውነትና በቅንነትም አምልኩት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ፥ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን ሌሎች አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርንም አምልኩ። 15 እግዚአብሔርን ታመልኩ ዘንድ ባትወድዱ ግን፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት፥ ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞሬዎናውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እርሱ ቅዱስ ነውና።” 16 ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፥ “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፤ 17 እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዐይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ፥ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። 18 እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱም የተቀመጡትን አሞሬዎናውያንን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን።” 19 ኢያሱም ሕዝቡን፥ “እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ ብታስቀኑት መተላለፋችሁንና ኀጢአታችሁን ይቅር አይልም። 20 እግዚአብሔርን ትታችሁ ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካምን ባደረገላችሁ ፋንታ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችሁማል” አላቸው። 21 ሕዝቡም ኢያሱን፥ “እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት። 22 ኢያሱም ሕዝቡን፥ “እንድታመልኩት እናንተ እግዚአብሔርን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” አላቸው፤ እነርሱም፥ “ምስክሮች ነን” አሉ። 23 እርሱም፥ “አሁን እንግዲህ በእናንተ ዘንድ ያሉትን ሌሎች አማልክት አርቁ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አቅኑ” አላቸው። 24 ሕዝቡም ኢያሱን፥ “አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ ቃሉንም እንሰማለን” አሉት። 25 በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ በሴሎም በእስራኤል አምላክ ድንኳን ፊት ሕግንና ፍርድን ሰጣቸው። 26 ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈው፤ ኢያሱም ታላቁን ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት በነበረችው በአሆማ ዛፍ በታች አቆማት። 27 ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ፥ “ይህች ድንጋይ በእናንተ ላይ ምስክር ናት፤ እርስዋ፥ ዛሬ እንደ ነገራችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ የተባለውን ሁሉ ሰምታለችና በኋላ ዘመን አምላኬን እግዚአብሔርን ብትክዱት ይህች ድንጋይ ምስክር ትሆንባችኋለች” አላቸው። 28 ኢያሱም ሕዝቡን አሰናበተ፤ ሁሉም ወደየቦታቸው ገቡ። የኢያሱና የአልዓዛር ሞት 29 እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ ነገር በኋላ የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ። 30 በተራራማውም በኤፍሬም ሀገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሴራ ቀበሩት። በዚያም ከግብፅ በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በገልገላ የገረዘባቸውን የድንጋይ ባልጩቶችን እርሱን በቀበሩበት መቃብር ከእርሱ ጋር ቀበሩ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ አሉ። 31 ኢያሱ ባለበት ዘመን ሁሉ፥ ከኢያሱም በኋላ በነበሩት ለእስራኤልም ያደረገውን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባወቁት በሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ እስራኤል እግዚአብሔርን አመለኩ። 32 የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ያወጡትን የዮሴፍን አፅም ያዕቆብ በሰቂማ ከሚኖሩ ከአሞራውያን በመቶ በጎች በገዛው ለዮሴፍ ድርሻ አድርጎ በሰጠው እርሻ በአንዱ ክፍል በሰቂማ ቀበሩት። 33 የአሮንም ልጅ ሊቀ ካህናቱ አልዓዛር ሞተ፤ በተራራማውም በኤፍሬም ሀገር ለልጁ ለፊንሐስ በተሰጠችው በጊብዓት መሬት ቀበሩት። 34 የዚያን ጊዜ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት ከእነርሱ ጋር ይዘዋት ሄዱ። ፊንሐስም እስከ ሞተና በቦታቸው በጊብዓት እስከ ቀበሩት ድረስ በአባቱ በአልዓዛር ፋንታ ሊቀ ካህናት ሆነ። 35 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ከተሞቻቸውና ወደ ቤታቸው ገቡ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ልጆች አስጠራጢንንና አስጣሮትን፥ በዙሪያቸውም የነበሩትን የአሕዛብን አማልክት አመለኩ። እግዚአብሔርም በሞዓብ ንጉሥ በኤግሎም እጅ ጣላቸው፤ ዐሥራ ስምንት ዓመትም ገዛቸው። |