ኢያሱ 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢያሱ መሰናበቻ ንግግር 1 እንዲህም ሆነ፤ ከብዙ ዘመን በኋላ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፈ በኋላ፥ ኢያሱ ሸመገለ፤ ዘመኑም ዐለፈ፤ 2 ኢያሱ የእስራኤልን ልጆች ሁሉ፥ ሽማግሌዎቻቸውንም፥ አለቆቻቸውንም፥ ፈራጆቻቸውንም፥ ሹሞቻቸውንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው፥ “እኔ እነሆ ሸምግያለሁ፤ ዘመኔም አልፎአል፤ 3 እናንተም አምላካችን እግዚአብሔር በፊታችሁ ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ስለ እናንተ ያደረገውን ሁሉ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነው። 4 እነሆ እኔ ካጠፋኋቸው አሕዛብ ሁሉ ጋር ከዮርዳኖስ ጀምሮ በፀሐይ መግቢያ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ለነገዶቻችሁ ርስት እንዲሆኑ የቀሩትን እነዚህን አሕዛብ በዕጣ ከፈልሁላችሁ። 5 አምላካችሁም እግዚአብሔር እርሱ ከፊታችሁ እስኪደመሰሱ ድረስ ያጠፋላችኋል፤ ከፊታችሁም እነርሱንና ንጉሦቻቸውን እስኪያጠፋቸው ድረስ የዱር አራዊትን ይሰድድባቸዋል፤ አምላካችን እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ። 6 በሙሴ ሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ትጠብቁና ታደርጉ ዘንድ በጣም በርቱ፥ ከእርሱም ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አትበሉ። 7 በእናንተም መካከል ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ አትግቡ፤ የአማልክቶቻቸውም ስሞች በእናንተ መካከል አይጠሩ፤ አትማሉባቸውም፤ አታምልኳቸውም፤ አትስገዱላቸውም፤ 8 ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጋችሁት አምላካችሁ እግዚአብሔርን ተከተሉ። 9 እርሱ እግዚአብሔር ታላላቆችንና ኀይለኞችን አሕዛብ ከፊታችሁ ያጠፋቸዋል፤ እስከ ዛሬም ድረስ የተቋቋማችሁ በፊታችሁ ማንም የለም። 10 አምላካችን እግዚአብሔር እንደ ነገረን ስለ እናንተ የሚዋጋ እርሱ ነውና ከእናንተ አንዱ ሰው ሺህ ሰውን ያሳድዳል። 11 አምላካችን እግዚአብሔርን ትወድዱት ዘንድ ለራሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ። 12 እናንተ ግን ተመልሳችሁ በመካከላችሁ ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ ብትጠጉ፥ ከእነርሱም ጋር ብትጋቡ፥ እናንተም ወደ እነርሱ፥ እነርሱም ወደ እናንተ ብትደራረሱ፥ 13 አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እስክትጠፉ ድረስ መውደቂያና ወጥመድ፥ በእግራችሁም ችንካር፥ በዐይናችሁም እሾህ ይሆኑባችኋል እንጂ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእንግዲህ ወዲያ እነዚህን አሕዛብ ከፊታችሁ እንዳያጠፋቸው ራሳችሁ ዕወቁ። 14 “እኔም በምድር እንዳሉት ሰዎች ሁሉ ዛሬ ወደ መንገድ እሄዳለሁ፤ እናንተም አምላካችን እግዚአብሔር ስለ እኛ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ፥ በነፍሳችሁም ሁሉ ዕወቁ፤ ሁሉ ደርሶናል፤ ከእርሱም ያላገኘነው የለም። 15 አምላካችሁ እግዚአብሔር የተናገረው መልካም ነገር ሁሉ እንደ ደረሰላችሁ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ ከዚህች ከመልካሚቱ ምድር እናንተን እስኪያጠፋችሁ ድረስ እግዚአብሔር እንዲሁ ክፉን ነገር ሁሉ ያመጣባችኋል። 16 አምላካችሁ እግዚአብሔር ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን ብታፈርሱ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ በዚያ ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ይነድድባችኋል፥ ከሰጣችሁም ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ ትጠፋላችሁ።” |