ኢያሱ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኢያሱ ወደ ኢያሪኮ ጉበኞችን እንደ ላከ 1 የነዌም ልጅ ኢያሱ፥ “ውጡና ምድሪቱን ኢያሪኮን እዩ” ብሎ ከሰጢም ሁለት ጐልማሶች ሰላዮችን በስውር ላከ። እነዚያም ሁለት ጐልማሶች ሄዱ፤ ወደ ኢያሪኮም ደረሱ፤ ረዓብ ወደሚሉአትም ዘማ ቤት ገቡ፤ በዚያም ዐደሩ። 2 ለኢያሪኮም ንጉሥ፥ “እነሆ፥ ከእስራኤል ልጆች ሰላዮች ሀገራችንን ሊሰልሉ ወደዚህ በሌሊት ገቡ” ብለው ነገሩት። 3 የኢያሪኮም ንጉሥ፥ “ሀገራችንን ሁሉ ሊሰልሉ መጥተዋልና ወደ አንቺ የመጡትን በዚችም ሌሊት ወደ ቤትሽ የገቡትን ሰዎች አውጪ በሉአት” ብሎ ወደ ረዓብ ላከ። 4 ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርስዋም፥ “አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፤ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላወቅሁም፤ 5 በሩም ሲዘጋ፥ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፤ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፤ ፈጥናችሁ ተከተሉአቸው፤ ምንአልባት ታገኙአቸው ይሆናል” አለቻቸው። 6 እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታ በተከመረ እንጨት መካከል በቀርከሃ ጠቅልላ ደብቃቸው ነበር። 7 ሰዎቹም ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ በሚወስደው መንገድ ተከተሉአቸው፤ በሩም ተቈለፈ። 8 እነዚህም ሳይተኙ ሴቲቱ ወደ እነርሱ ወደ ሰገነቱ ወጣች። 9 ሰዎቹንም እንዲህ አለቻቸው፥ “እግዚአብሔር ምድሪቱን አሳልፎ እንደ ሰጣችሁ ዐወቅሁ፤ እግዚአብሔር እናንተን መፍራትን በላያችን አምጥትዋልና፥ በምድሪቱም የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ የተነሣ ቀልጠዋልና። 10 ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፥ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት፥ እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፥ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። 11 ይህንም ነገር ሰምተን በልባችን ደነገጥን፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከእኛ የአንዱም እንኳን ነፍስ አልቀረም። 12 አሁንም፥ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፤ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ አደረግሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድታደርጉ፥ በእውነት ምልክት ስጡኝ። 13 የአባቴን ቤት፥ እናቴንም፥ ወንድሞቼንና ቤቴንም ሁሉ፥ ያላቸውንም ሁሉ አድኑ፤ ሰውነታችንንም ከሞት አድኑ።” 14 ሰዎቹም፥ “ሕይወታችንን ስለ እናንተ አሳልፈን ለሞት እንሰጣለን” አሉ፤ እርስዋም አለች፥ “እግዚአብሔር ምድሪቱን በሰጣችሁ ጊዜ ቸርነትንና ጽድቅን ታደርጉልናላችሁ።” ሰዎቹም፥ “ይህን ነገራችንን ባትገልጪ እግዚአብሔር ሀገራችሁን በእውነት አሳልፎ ከሰጠን ከአንቺ ጋር ቸርነትን እናደርጋለን” አሏት። 15 ቤቷም በከተማ ቅጥር የተጠጋ ነበረና፥ እርስዋም በቅጥሩ ላይ ተቀምጣ ነበርና በመስኮቱ በገመድ አወረደቻቸው። 16 እርስዋም፥ “የሚከተሉአችሁ እንዳያገኙአችሁ ወደ ተራራው ሂዱ፤ የሚከተሉአችሁም እስከሚመለሱ ድረስ በዚያ ሦስት ቀን ተሰውራችሁ ተቀመጡ፤ በኋላም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ” አለቻቸው። 17 ሰዎቹም አሉአት፥ “እኛ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሓን እንሆናለን። 18 እነሆ፥ እኛ ወደ ሀገሩ በገባን ጊዜ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት በኩል እሰሪው፤ አባትሽንም፥ እናትሽንም፥ ወንድሞችሽንም፥ የአባትሽንም ቤተ ሰብ ሁሉ ወደ አንቺ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ። 19 ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ሁሉ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ እኛም ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሓን እንሆናለን፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤትሽ ውስጥ ያለ ቢሞት ደሙ በእኛ ላይ ነው። 20 ነገር ግን ይህን ነገራችንን ብትገልጪ ከዚህ ካማልሽን መሐላ ንጹሓን እንሆናለን።” 21 እርስዋም፥ “እንደ ቃላችሁ ይሁን” አለች፤ አሰናበተቻቸውም፤ እነርሱም ሄዱ፤ ቀዩንም ፈትል በመስኮቱ በኩል አንጠለጠለችው። 22 እነርሱም ወጥተው ወደ ተራራው ሄዱ፤ የሚከተሉአቸውና የሚፈልጉአቸውም እስኪመለሱ ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጡ፤ በመንገዱም አላገኙአቸውም። 23 ሁለቱም ጐልማሶች ተመለሱ፤ ከተራራውም ወርደው ተሻገሩ፤ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ መጡ፤ የደረሰባቸውንም ሁሉ አወሩለት። 24 ኢያሱንም፥ “በእውነት እግዚአብሔር ሀገሩን ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአል፤ በዚያች ምድር የሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ከእኛ የተነሣ ደነገጡ” አሉት። |